በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
በወጣቱ ተልዕኮ(አህመድ የሱፍ)
ክፍል 1
ልኡል ሃያል ስለሆነው አሏህ ያለ እውቀት ስለ እሱ መናገር የከፋ የአሏህን ቅጣት የሚያመጣ ሲሆን ከወንጀሎችም ሁሉ የከፋ ወንጀል ነው። በዚህም ምክኒያት በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሁነን ቢሆን እንኳ ያለ እውቀት ስለ አሏህ መናገር አይኖርብንም። አሏሁ አዘወጀል በሱረቱል አዕራፍ ከሌሎች ከባባድ ወንጀሎች ጋር እያወዳደረ የወንጀሉን ከባድነት ገልፆልናል።
አምላካችን አሏህ በሱረቱል አዕራፍ አንቀፅ 33 ላይ እንዲህ ይላል፦
"በእርግጥ ጌታየ የከለከላቸው ነገሮች አልፈዋሂሽ (በግልፅም ይሁን በድብቅ የሚፈፀሙ መጥፎ ነገሮች) ፣ ወንጀሎች ፣ ፍትህ የተጓደለበት ጭቆና ፣ በእርሱም ማስረጃ ያልወረደበትን ጣዖት በአሏህ ላይ ማጋራት እና ስለ አሏህ ያለ እውቀት መናገር ናቸው በላቸው።" {አል-ቁርአን 7:33}
ከዚህ አያ ላይ እንደተገነዘብነው አሏህ ከከለከላቸው ነገሮች አንዱ በግልፅም ይሁን በድብቅ የሚሰሩ መጥፎ ነገሮች እንደሆኑ ከገለፀ ቡኋላ ከዚህ በላይ የከፋ የሆነው ነገር “ወንጀል እና ፍትህ” የተጓደለበት ጭቆና እንደሆነ ገልፃል።
በማስከተልም ከዚህ በላይ የከፋ የሆነው ሃጢያት ወይም ወንጀል በአሏህ ላይ ማሻረክ ሲሆን ከዚህም በማስከተም በአሏህ ላይ ያለ እውቀት ስለ እሱ መናገር መሆኑን ገልፆልናል።
የመጀመሪያው ወንጀል በራስ ነፍስ ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው። ሁለተኛው ፍትህ የተጎደለበት ጭቆና ደግሞ በሌሎች ላይ የሚፈፀም ወንጀል ወይም በደል ነው። ከዚህም በላይ የከፋ የሆነው ደግሞ በአሏህ ላይ ማሻረክ ሲሆን የአላህን መብት ለሌላ አሳልፎ መስጠት ነው። ከዚህም የከፍ የሆነው ያለ እውቀት ስለ እሱ መናገር ነው።
ውድ ሙስሊም እህት ወንድሞቼ ይህ ሸይጧን መሃይማኖችን ፣ እብሪተኞችን እንዲሁም ቲፎዞ እና አጨብጫቢ ፈላጊዎችን የሚያበረታታበት በጣም የከፋ ሃጢያት ነውና ልንጠነቀቀው ይገባል።
አምላካችን አሏህ በቅዱስ ቃሉ በሱረቱል በቀራ አንቀፅ 169 ላይ እንዲህ ብሏል።
"ሸይጧን) የሚያዛችሁ መጥፎና የተጠላ በሆነ ነገር ላይ እንዲሁም በአሏህ ላይ የማታውቁትን ነገር እንድትናገሩ ብቻ ነው።" {አል-ቁርአን 2:169}
በላይኛው አያ መሰረት አሏሁ አዘወጀል ሸይጧን የሚያዘው መጥፎና የተጠላ በሆነ ወንጀል ላይ እንደሆነ ገልፆ ከዚህም ውስጥ አንዱ በአሏህ ላይ የማናውቀውን ነገር ስለ እሱ መናገር እንደሆነ አሳውቆናል።
ያለ እውቀት ስለ አሏህ ልንናገርባቸው የምንችላቸው ነገሮች
- በሃያሉ አሏህ ላይ መዋሸት
- ለአሏህ ተገቢ ያልሆነን ነገር ወደ እሱ ማስጠጋት
- ቢድአ መስራት(አሏህ ሃይማኖታችነን ሙሉ ካደረገልን ብኋላ ከራሳችን ስሜትና ፍልስፍና በመነሳት ያልነበሩ ነገሮችን ወይም በእምነቱ ያልተደነገጉ ነገሮችን በሃይማኖታችን ላይ መቀነስ ወይም መጨመር ነው።
- አሏሁ አዘወጀል ያረጋገጠውን ነገር መቃረን
- አሏህ የሻረውን ነገር ማረጋገጥ
- በእሱ መንገድ አሸናፊ የሆኑትን ወይም ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱትን መጥላት
- ጠላቶቹን መርዳት
- የሚጠላቸውን መውደድ እና የሚወዳቸውን መጥላት
- አሏህ የማይገባው በሆነ ነገር እርሱን መግለፅ (ይህም በስምና በባህርያቶቹ ወይም አሏህ በገለፀው ነገርና በተግባሩ ሊሆን ይችላል።
ያለ እውቀት ስለ አሏህ መናገር እነዚህን ሁሉ ወንጀሎች አቅፎ የሚይዝ ሲሆን ከዚህ ወንጀል ነው ሽርክም ይሁን ሁሉም የኩፍር(የክህደት) አይነቶች የሚፈጠሩት። እንዲሁም ማንኛውም የቢድአ አይነቶች መሰረታቸው በአሏህ ላይ የማያውቁትን ነገር በመናገር የሚፈጠሩ ናቸው።
ስለ አሏህ ያለ እውቀት ልንናገርባቸው የምንችላቸው ነገሮች እንደሚከተለው ተብራርተው ተገልፀዋል።
- በአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ላይ ወይም በመልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ላይ መዋሸት
ምንም እይነት ነገር ያለ እውቀት መከተል እንደሌለብን ሃያሉ አሏህ አሳውቆናል። አሏሁ አዘወጀል በሱረቱል ኢስራ አንቀፅ 36 ላይ እንዲህ ብሎናል፦
"እውቀት በሌለህ ነገር ላይ አትከተል። በእርግጥ በመስሚህ ፣ በማያህ እና በልብህ በእያንዳንዳቸው ትጠየቃለህ።" {አል-ቁርአን 17:36}
አምላካችን አሏህ(ሱ.ወ.ተ) እኛ ሙስሊሞች ሰለ እሱ ያለ እውቀት መናገር እንደሌለብን አሳውቆናል። ስለ አሏህ ያለ እውቀት መናገርንም ከልክሎናል። በአሏህ ላይ መዋሸትም ይህን ከምናደርግበት መንገድ አንዱ ነው። በአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ላይ የዋሸ ሰው ያለ እውቀቱ ስለሱ ስለተናገረ ወንጀለኛ ወይም ጥፋተኛ ብቻ ሳይሆን አሏህ እንደገለፀው ከበዳዮች መካከል ነው።
"በአሏህ ላይ ከዋሸ ወይም በአንቀፆቹ ላይ ከዋሸ (አንቀፆቹን ከካደ) ሰው በላይ ይበልጥ በዳይ ማን አለ?" {አል-ቁርአን 7:37}
ከዚህ በተጨማሪ ጥበበኛው አሏህ በዚህ አደገኛ ተግባር እራሳቸውን ለዘፈቁ ሰዎች በትንሳኤ ቀን ቅጣታቸው ምን እንደሆነ ገልፃል።
"እናም በትንሳኤ ቀን እነዚያ በአሏህ ላይ የዋሹ ሰዎች ፊቶቻቸው የጠቆረ ሆኖ ታየዋለህ። በጀሃነም ውስጥ ለእብሪተኞች መኖሪያ የለምን?" {አል-ቁርአን 39:60}
ኢብን አልጀውዚ በተፍሲራቸው ብዙ ኡለማዎች በአሏህ እና በመልዕክተኛው ላይ መዋሸት ኩፍር(ክህደት) እንደሆና ከኢስላም ያስወጣል የሚል አቋም እንዳላቸው ገልፀዋል። በመልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ላይ መዋሸት በተመሳሳይ መልኩ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ምክኒያቱም በተዘዋሪ በአሏህ ላይ መዋሸት ነውና። መልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) በእሳቸው ላይ የመዋሸትን አደገኝነት እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል፦
"አውቆ (ሆንብሎ) በእኔ ላይ የዋሻ መቀመጫውን የጀሃነም እሳት ውስጥ ያድርግ" ብለዋል።"{ቡኻሪ እና ሙስሊም}
ብዙዎቻችን መስረቅ ፣ ዝርፊያ ፣ ማጭበርበር ፣ ግድያ ፣ ዝሙት ወዘተ ክልክል ወይም ሃራም እንደሆኑ እንናገራለን። ነገር ግን በአሏሁ አዘወጀል ላይ መዋሸት ሲባል እንዲህ አይነት ወንጀል ስለመኖሩም ጠንቅቀን የማናውቅ ብዙዎቻችን ነን።
ይህን በተመለከተ በእኛ በሙስሊሞች መካከል የሚገኝበት ምክኒያት የአሏህን መብት እና የመልዕክተኛውን(ሰ.ዐ.ወ) መብት ጠንቅቀን ስለ ማናውቅ እና ሃጢያት ውስጥ የመዘፈቃችን አስከፊ ውጤት ምን እንደሆነ ስለማናውቅ ነው። ሙስሊም ሆኜ እውነት በጀሃነም እቀጣ ይሆን ብለን የምናስብ ብዙዎች ነን።
በአሏህ እና በመልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ላይ መዋሸት የሚገለፅባቸው መንገዶች
- ካለ ቁርአን ወይም ካለ ሰኺህ ሱና ማስረጃ አሏህን መግለፅ
- ለምሳሌ አሏህ የትም ቦታ እንደሚገኝ መግለፅ አሏህ(ሰ.ዐ.ወ) ከፍጥሮቹ በላይ እንጅ ከፍጥረቶቹ ጋር የትም ቦታ አይደለም፣ የነሱም አካል እንዳልሆነ ቁርአናዊና ሐዲሳዊ ማስረጃዎች አሉ። የሚከተለውም ሐዲስ ይህን በግልፅ ያመላክታል።