ለምድነው ሶላታችነን የማንሰግደው?

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።

በወጣቱ ተልዕኮ (አህመድ የሱፍ)


ሶላት ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር ወይም ግንኙንነት የምናጠነክርበት ፣ ለኒዕማዎቹ ሁሉ የምናመሰግንበትና ልቅናውን የምናወሳበት ቢሆንም ብዙ ሙስሊሞች ግን አይሰግዱም። ልክ አካላችን ምግብና ውሃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ነፍሳችነም መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያስፈልገው ራሳችነን በአምልኮት ተግባራት ልናንፅ ይገባል። ከነዚህ የአምልኮት ተግባራት መካከል አንደኛውና ወሳኙ የሆኑ ነው ደግሞ ሶላት ነው።

በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገበው ሐዲስ መሠረት
ረሱል(ሰ.ዐ.ወ): አሏህን የሚያወሳና የሚያወሳ ሰው ንፅፅሩ ልክ ህያው እንደሆነ(በህይወት እንዳለ ሰው)ና በሙት ይመሰላል (ልክ እንደሞተ ሰው ነው) ብለዋል።

            =<({አል-ቁርአን 8:24})>=

{24} እናንተ ያመናችሁ ሆይ! መልዕክተኛው ህያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ ለአሏህና ለመልዕክተኛው ታዘዙ። አሏህም በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መሆኑን ወደ እርሱም የምትሰበሰቡ መሆናችሁን እወቁ።

  • ሶላት ከአሏህ ጋር በቀጥታ የምንገናኝበት ነው 

አንድ ሰው ወደ ጌታው በጣም የበለጠ የሚቀርበው ሱጁድ ላይ በሆነ ጊዜ ነው። የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ): ከናንተ መካከከል አንዳችሁ ለሶላት በቆመ ጊዜ ከአሏህ ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

  • የእስልምና ምሶሶ

ሶላት በሙስሊሞች ህይወት ውስጥ ግዴታ የሆነ የዘወትር ተግባር ሲሆን ከ5ቱ የእስልምና ምሶሶዎች ውስጥ ሁለተኛውና ወሳኙ የአምልኮት ተግባር ነው። በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሁነን ቢሆን እንኴ ቢያንስ በቀን አምስት ጊዜ ልንሰግድ ይገባል። እነዚያ ብርቅየ ሶሃቦች ጦርነት ላይ ሁነው በነበረ ጊዜ እንኴ አሏህ ከሶላት ነፃናችሁ አልነበረም ያላቸው። ይልቁንም እንዲህ ሲል ነበር ያዘዛቸው፦

        =<({አል-ቁርአን 2:238-239})>=

{238} ሶላቶቻችሁን ተጠባበቁ በተለይ የመካከለኛይቱ ሶላት (አስር ሶላትን)። ታዛዦች ሁናችሁም ለአሏህ ቁሙ።

{239} ብትፈሩም እግረኞች ወይም ጋላቢዎች ሆናችሁ ስገዱ።

ታዲያ እነዚያ ብርቅየ ሶሃቦች የጦርሜዳ ላይ ሁነው ስገዱ ከተባሉ እኛስ በሰላም ጊዜ እንዴት ብላችሁ ስገዱነው የምንባለው?

  •  ስኬት ያለው ሶላት ላይ ነው 

ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ): የሰው ልጅ በዕለተ ትንሳኤ ከስራዎቹ መካከል በመጀመሪያ የሚጠየቀው ስለ ሶላት ነው። ሶላቱ ከተስተካከለ ይሳካለታል። ሶላቱ ያልተሟላ ከሆነ በዕጦት ይሰቃያል (ከከሳሪዎች ይሆናል)፤ ይዋረዳልም ብለዋል።

  • ሶላት የመጥፎ ነገሮች መከላከያ ጋሻ ነው 

የአሏህን እርዳታ ሳንሻ ከወንጀል ተግባራትቶች ልንርቅ አንችልም። እንዲሁም ለአሏህ ካለን ፋራቻ ፣ ውዴታና ታዛዥነት የተነሳ ሶላቶቻችነን በወቅቱና በሁሹእ የምንሰግድ ከሆነ ሃራም ነገሮችን አንፈፅምም።

         =<({አል-ቁርአን 29:45})>=

{45} ከመፅሐፉ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ። ሶላት ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ሁሉ ትከለቀክላለችና።

        ሶላት መንፈሳችነን ያበለፅጋል

ሶላት መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችነን በማርካት ሰላምና ደስታ እንዲሁም መረጋጋትን ያስገኛል። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱል አልረዕድ አንቀፅ 28 ላይ እንዲህ ይላል፦

         =<({አል-ቁርአን 13:28})>=

{28} እነዚያ ያመኑ ልቦቻቸው አሏህን በማውሳት የሚረኩ (የሚረጋጉ) ናቸው። ንቁ! አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉና።

      ሶላት ሃጢያቶቻችነን ያብሳል

እንደሚታወቀው በዚህ ውስብስብ አለም ውስጥ ወንጀል ከመፈፀም የታቀበ ንፁህ የሆነ ሰው የለም። ደረጃው ይለያያል እንጅ ሁሉም የአደም ልጅ ወንጀል ይሰራል። ከሰው ልጅ ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም አይደል የሚባለው። ሆኖም አሏህ(ሱ.ወ.ተ) በሶላት ጎዳና ወንጀላችነን የምናሳብስበትን መንገድ አስገኘን። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱ ሁድ አንቀፅ 114 ላይ እንዲህ ይላል፦

        =<({አል-ቁርአን 11:114})>=

{114} ሶላትንም በቀን በሁለቱ ጫፎች ፣ ከሌሊትም ክፍሎች ፈፅም በእርግጥ መልካም ስራዎች ሃጢያቶችን ያስወግዳልና። ይህ ለተገሳጮች ግሳፄ ነው።

የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ): ለሶሃቦቻቸው እንዲህ ባሉ ጊዜ ምርጥ ምሳሌ ሰተው ነበር። ከእናንተ መካከል አንዳችሁ በቀን አምስት ጊዜ የሚታጠብበት የሆነ በበራፉ በኩል የሚያልፍ ወንዝ ቢኖረው በሱ ላይ ቆሻሻ ይቀራልን? አሉ። እነርሱም አይቀርም አሉ። እናም የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ): ልክ እንደዚሁ አሏህ በአምስት አውቃ ሶላቶች ሃጢያትን ያብሳል ሲሉ መለሱ።

ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ግኑኝነት ባጠነከርን ቁጥር አሏህ በማንኛውም ነገር ያግዘናል፤ የበለጠም ወደ እሱ ያቀርበናል፤ ችግሮቻችነንም ይፈታልናል። አሏሁ አዘወጀል በቅዱስቃሉ በሱረቱል በቀራ አንቀፅ 153 ላይ እንዲህ ይላል፦

          =<({አል-ቁርአን 2:153})>=

{153} እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትዕግስትና በሶላት እርዳታን ሻቱ በእርግጥ አሏህ ከታጋሾች ጋር ነው።

        ሙስሊሞችን አንድ ያደርጋል

የጀመአ ሶላት ለብቻችን ከምንሰግደው በ25 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በመካከላችን ወንድማማችነት ፣ እኩልነት እና መተናነስ እንዲያብብ ያደርጋል። ለሶላት በቆምን ጊዜ ዘር ፣ ብሔር ፣ ቀለም ፣ ጎሳ ወ.ዘ.ተ ሳይለያየን አንድ አካል ሁነን ትከሻ ለትከሻ ፣ እግር ለእግር ገጥመን ለአምላካችን አሏህ እናጐበድዳለን።

                 ሶላትን መተው

            =<({አል-ቁርአን 82:6})>=

{6} አንተ ሰው ሆይ! በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ?

የመኖራችን ሚስጥር፤ የመፈጠራችን አላማ አሏህን በብቸኝነት መገዛት ሆኖ ያለ እኛ ግን ስሜታችነን በመከተል አምላካችነን አመፅነው። አሁን መስገድ አለብኝ ከማለት ይልቅ ነገ እሰግዳለሁ ማለትን ስንቅ አድርገን ያዝን። ነገ በህይወት ስለመኖራችን ዋስትናችን ምንድ ነው? ውድ እህት ወንድሞቼ ሆይ! ቆም ብለን እናስብ እባካችሁ! እስኪ በሚከተለው የቁርአን አያ ልብ ብለን እናስተንትን። አሏህ(ሱ.ወ.ተ) በቁርአኑ በሱረቱል መርየም አንቀፅ 59 ላይ እንዲህ ይላል፦

          =<({አል-ቁርአን 19:59})>=

{59} ከእነሱም በኋላ ሶላትን የተው ፍላጎቶቻቸውንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች(ትውልዶች) ተተኩ። በእርግጥ የጀሃነምን ሸለቆ ያገኛሉ።

        =<({አል-ቁርአን 74:42-43})>=

{42} በሰቀር ውስጥ(በጀሃነም ውስጥ) እንድትገቡ ያደረጋችሁ ምንድነው? ይባላሉ።

{43} እነሱም ከሰጋጆች አልነበርንም ይላሉ።

አሏሁ አዘወጀል ብዙ ዕልቆቢስ የሆኑ ኒዕማዎችን በዙርያችን ሰጠን፤ አስታውሱኝ አስታውሳችኋለሁና አለን፤ ለኔም አመስግኑ አትክዱኝም ሲለን እኛ ግን ፊታችነን ዘወር አድርገን ሶላትን ተውን፤ የአሏህን በረካዎች በልተን እንዳልበላን ሆን። በእርግጥም ይህን በማድረጋችን ከአሏህ ጋር ያለንን ግኑኝነት አቇረጥን።

ውድ እህት ወንድሞቼ እናስተውል! እኛ ስለሰገድን ስላልሰገድን ፣ ስላመሰገነው ስላላመሰገነው አሏህ የሚጎልበት ነገር የለም። እኛ የምንጎዳ ብንሆን እንጅ።

           =<({አል-ቁርአን 67:23})>=

{23} እሱ ያ የፈጠራችሁ ለእናንተም መስሚያና ማያዎችን ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው። ጥቂትንም አታመሰግኑም በላቸው።

ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ለረጅም ጊዜ ለሶላት በመቆም እግራቸው ያብጥ ነበር። አንዴ ስለዚህ ነገር ተጠይቀው “ለጌታየ አመስጋኝ ባርያ መሆን የለብኝምን?” ሲሉ መለሱ። እኛ ግን አይደለም ቂያመለይል የግዴታ ሶላቶቻችን እንኴ ከብደውናል። እስኪ በልቦቻችን ውስጥ ያለውን ነገር እንፈትሽ!

              ደካሞች እየሆንነው

የሰማያትና የምድር እንዱሁም የፍርዱ ቀን ባለቤት ለሆነው አምላካችን አሏህ ሶላትን ምን ብለን ተውን ነው የምንለው? አሏህ(ሱ.ወ.ተ) 24 ሰዓቶችን ሰቶን ባረባ ነገር ብዙ ጊዜያችነን እያጠፋን ታዲያ ለሶላት እንዴት 15 ደቂቃ አጣንለት? የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ): በትንሳኤ ቀን የአደም ልጅ ስለአምስት ጉዳዮች ሳይጠየቅ እግሮቹን አያንቀሳቅስም። ህይወቱን በምን እንዳሳለፈ ፣ ምን በመስራት ወጣትነቱን እንዳሳለፈ ፣ ሃብት ንብረቱን የትእንዳገኘውና በምንላይ እንዳወጣው እንዲሁም ባወቀው ነገር ላይ ምን እንደሰራ ሳይጠየቅ ብለዋል።

ሌላው ማወቅ ያለብን ነገር ብዙ ኡለማዎች ሶላትን የተወ ሰው ከሐዲ ነው ሲሉ ፈትዋዎችን ሰተዋል። ይህም የሚከተለውን ሐዲስ በመጥቀስ ነው።

ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ): በከሐዲዎችና በእኛ መካከል የሚለየን ሶላት ነው። እሷን ችላ ያለ በእርግጥ ካደ ብለዋል።

ሶላት ለመተዋችን የምናቀርባቸው የተለመዱ ምክኒያቶች

  • ጥናቴ/ስራየ/ተጨናንቂያለሁ

ብዙ የሚያረይረብ ነገሮችን እየሰራን፤ ከአንድ ሰዓት በላይ በወሬ እየጨረስን፤ ከአንድ ሰዓት በላይ ሶሻል ሚድያዎችን እየተጠቀምን እንዲሁም ለአንድ ሰዓት ያህል ቻት እያደረግን ለሶላት ጊዜ አጣን? ከሶላት በላይ ጥናታችነን እና ስራችነን እንዴት እናስቀድማለን?

እህት ወንድሞቼ ከማንኛውም ስራ በላይ ሶላትን ነው ማስቀደም ያለብን። ያኔ ሶላታችን ከማንኛውም ነገር በላይ ባስቀደምን ጊዜ አሏህ ሰዓታችነን ይባርክልናል፤ በጥናታችንም ሆነ በስራችን ብቁና ስኬታማ ያደርገናል።

  • አላርም ስላልቀጠርኩ ነው

ኒያችነን በማስተካከል በረሱል(ሰ.ዐ.ወ) መንገድ እንተኛ።

  • ልቤ ንፁህ ነው

ልባችን የፈለገ ያህል ንፁህ ቢሆንም አሏህ እንድንሰግድ ይፈልጋል። ምክኒያቱም የተፈጠርንበት አላማ ይህነውና። በእርግጥ ተግባራችን ወይም ስራችን በልባችን ውስጥ ላለው ነገር ነፀብራቅ ነው። ከረሱል(ሰ.ዐ.ወ) በላይም ንፁህ ልብ ያለው የለም።

  • ብዙ ሃጢያት ወይም ወንጀል እየሰራሁ ነው

በአሏህ ፈቃድ ሶላታችን ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ሁሉ ይከለክለናል። ዋናው ከኛ የሚጠበቀው ከልብ በመነጨና ቅን በሆነ ተውባ ወደ አሏህ መመለስ እንዲሁም ሶላት ከመጥፎ ነገር የሚከለክል መሆኑን ከልባችን ማመንናና ሶላቶቻችንን በወቅቱ ከኹሹእ ጋር መስገድ ነው።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top