ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።
የተውባ የቃል በቃል ትርጉሙ መመለስ ማለት ሲሆን አሏህን ወደ ማስታዋስ እና ወደ መታዘዝ መምጣት ማለትም ነው።
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። ምስጋና ለአለማት ጌታ ለሆነው ለአሏህ ይገባው።
የአሏህ ሰላምና እዝነት በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ፣ በቤተሰቦቻቸው ፣ በሶሃቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ እስከ የውመልቂያማ ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኑር 24፡31)
ተውባ (ንሰሃ) አሏህ ዘንድ ታላቅ እና ተወዳጅ የሆነ እሱን የመታዘዝ ተግባር ነው። በእርግጥ አሏህ ሙእሚኖች ወደ እሱ በተውበት እንዲመለሱ አዟል። ሙእሚኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አሏህ ቶብቱ (ተመለሱ)።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሳወቁን በረሃ ውስጥ ስንቁን እና ምግቡን የያዘች ግመል የጠፋችበት ፣ አገኛታለሁም ብሎ ተስፋው ተሟጦ ያለቀ ሰው ከዚያም ሲያገኛት ከሚደሰተው በላይ አሏህ በባሪያው ተውበት የበለጠ ይደሰታል።
ተውባ በማድረግ ሐጢያተኞች ከሐጢያታቸው ይማራሉ። ምክኒያቱም አሏህ (ሱ.ወ.ተ) እጅግ በጠም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ መሃሪ ነውና።
አሏህ ከኛ ሙሉእነትን አይጠብቅም፤ ከኛ የሚጠብቀው ስተት በሰራን ወቅት ከአመፀኝነት ፣ ከወንጀለኝነት እና ካለመታዘዝ ወጥተን አሏህን ያዘዘንን ነገር ሁሉ ለመታዘዝ ፣ የከለከለንን ሁሉ ለመከልከል በተውባ ወደ እርሱ መመለስ ብቻ ነው።
ነገርግን ለብዙ ጊዜ ወንጀል እየሰራን፤ ከአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ምህረትና ከለላን ካልሻትን ምህረቱንም ካለመን ነፍሳችንም መወንጀሏን ትቀጥላለች፤ በወንጀላችነም ብዛትና ፅናት ትበሰብሳለች፤ መመለሻችንም የከፋ ይሆናልና ይህ ከመከሰቱ በፊት የአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ፍራቻ በልባችን ውስጥ ማኖር ይኖርብናል።
የአሏህን መብት ወይም ትዕዛዝ በመተላለፍ ወንጀል የሰራ ሰው ለመቶበት የሚከተሉትን ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች መፈፀም አለበት።

- ወንጀሉን ወዲያውኑ መተው
- ወንጀሉን በመፈፀሙ መፀፀት
- ደግሞ ላለመፈፀም ከልብ መወሰን
ሁለት የበደል አይነቶች
- በአሏህ (ሱ.ወ.ተ) እና በባሪያው መካከል ያለ
ለምሳሌ:- ሽርክ ፣ ዚና ፣ ግድያ ፣ አስካሪ መጠጥ መጠጣት ወ.ዘ.ተ - በሌሎች ሰዎች ላይ ያደረስነው መጥፎ ስራ ለምሳሌ፡- ሐሜት ፣ መስረቅ ፣ ዋሽቶ ማጣላት ወ.ዘ.ተ
ወንጀሉ በሌላ ሰው ላይ የተፈፀመ ከሆነ ከነዚህ ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ አራተኛ ቅድመ ሁኔታ መሟላት አለበት። ለምሳሌ አንድ ሰው የሆነ ነገር ቢሰረቅ የሰረቀውን ለሰረቀው ሰው መመለስ አለበት።
ደስ የማይል ፣ ጥሩ ያልሆነ ነገር የተናገረ ሰው ምህረቱን (ይቅርታውን) መጠየቅ አለበት። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“ወንድሙን የበደለ ሰው (ከመሞቱ በፊት) ምህረቱን ይለምን። በመጭው አለም ዲናርም ፣ ዲርሃምም አይኖረውምና። ከመልካም ስራው ተወስዶ ለወንድሙ ከመከፈሉ በፊት ወይም የሰራው መልካም ስራ ከሌለው የወንድሙ መጥፎ ስራ ከእሱ ላይ ሳይጫንበት በፊት (በዚህ አለም ህይወት) ምህረቱን ይያዝ።
እንደ ሙስሊም ተውበትን ማዘግየት አይኖርብንም። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኒሳዕ 4፡18)
ተውበት መጥፎ ስራን መስራት ለቀጠሉ አይደለችም። ሞት በአንዳቸው ላይ በመጣች ጊዜ በእርግጥ አሁን ቶበትኩ ለሚልና ካሃዲ ሆነው ለሞቱትም አይደለችም። ለእነዚያ ለእነሱ አሳማሚ ቅጣት አዘጋጅቷል።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም)
“አሏህ የባሪያውን ተውበት ይቀበላል። ነፍሱ ከጉሮሮው እስካልደረሰች እና ፀሐይ በምዕራብ እስካልወጣች ድረስ።”
በደል ወይም ወንጀል ከሰራን እና በሰራ ነው ነገር ላይ ከተፀፀትን ወንጀላችን ጉምን አልፎ ሰማይን የሚነካ ቢሆን እንኴ ከልባችን ከቶበትን አሏህ ይምረናል።
ከዚህም በላይ አሏህ መጥፎ ስራዎቻችነን በመልካም ነገር ሊቀይርልን ቃል ገብቶልናል። ይህም በአሏህና በባሪያው መካከል ላለ በደል ወይም ወንጀል ነው።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ፉርቃን 25 : 70)
“እነዚያ የተፀፀቱት ፣ ያመኑትና መልካም ስራን የሰሩት ሲቀሩ። ለነሱም አሏህ መጥፎ ስራዎቻቸውን ሃጢያታቸውን በመልካም ስራ ይቀይርላቸዋል። አላህም እጅግ መሃሪ አዛኝ ነው።”
በሌሎች ሰዎች ላይ ላደረስነው በደል አሏህ ይቅር አይለንም። የበደልናቸውን ሰዎች ከልባቸው አውፍ እንዲሉን መጠየቅ ወይም ሃቃቸውን መክፈል ይኖርብናል። ያ ሲሆን አሏህም ይቅር ይለናል።
ስለሆነም ስራችንን ፣ ንግግራችንን እና ልባችንን ለማፅዳትና አሏህን ወደ መታዘዝ ጎዳና ለመምጣት ተውባ እና እስቲግፋር ማዘውተር ይኖርብናል።



