ሽርክ የተውሂድ ተፃሪ ነው። ከአሏህ ውጭ ያሉ ነገሮችን ማምለክ የሚገልፅ ነው። እንዲሁም ከአሏህ ውጭ ላሉ ነገሮች መለኮታዊ ባህርያትን መስጠት ነው።
በአምልኮት ለአሏህ ባላንጣ ማበጀት ነው። ይቅርታ (ምህረት) የሌለውን የሽርክ ሃጢያት መፈፀምን አሏህ አስጠንቅቋል።

አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሉቅማን 31፡13)
በአሏህ አታጋሩ። ማጋራት ትልቅ በደል ነውና።
ሶስት የሽርክ አይነቶች
- አሽርኩል አክበር (ትልቁ ማጋራት)

ይህ አይነቱ ሽርክ ማንኛውንም የአምልኮ ተግባር ከአሏህ ውጭ ላለ ነገር ማድረግ ነው። በእርግጥ ይህ በጣም ከባዱ የሽርክ አይነት ነው። ለምሳሌ ጸሎትን ፣ ስግደትን ፣ ስለትን ፣ መሃላን ወ.ዘ.ተ ለጣኦት ማድረግን የያዘ ነው።
እንዲሁም የአምልኮ ተግባርን ወይም የበጎ ስራ ሃሳብ (ኒያ) ለሌሎች ማድረግ ፣ የአሏህን ትዕዛዛት የሚፃረር ማንኛውም ነገር መታዘዝ እና ለእነሱም ውዴታን ማሳየት አብሮ የያዘ ነው።
ለአሏህ ባላንጣን ያበጀ ሰው ይህን ሃጢያት በመፈፀሙ አይማርም፤ መኖሪያውም ዘላለምዊ እሳት ነው። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኒሳዕ 4፡48)
በእርግጥ አሏህ በእሱ ላይ ማጋራትን አይምርም። ከዛ ውጭ ያለን ለሻው ሰው ይምራል።
- አሽርኩል አስገር (ትንሹ ማጋራት)
ይህ አይነቱ ሽርክ በንግግር ወይም በተግባር የሚገለፅ ሲሆን ነገርግን አንድን ሰው ከኢስላም አያስወጣም። ይህም ከአሏህ ውጭ ባለ ነገር መማል ፣ የአምልኮት ተግባራትን ምስጋና አድናቆትን ለማግኘት ወይም ለዩዩልኝ ሲሉ መፈፀምን አጠቃሎ የሚይዝ ነው።
ይህ አይነቱ ሽርክ ለዘላለማዊ ቅጣት አይዳርግም። ነገርግን የተውሂድን ሙሉነት ያጓድላል። ይህ ደግሞ ግዴታ ነው።

- አሽርኩል ኸፊይ (ድብቁ ማጋራት)
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(አህመድ)
ከመሲሁ ደጃል በላይ የምፈራላችሁን ነገር አላሳውቃችሁምን (ሶሃባዎች) ‹አሳውቀን የአሏህ መልዕክተኛ› ሲሉ መለሱላቸው። አሽርኩል ኸፊይ (ድብቁ ማጋራት) ነው። አንድ ሰው ለሶላት ይቆማል፤ ሶላትን የሚያሳምረው ግን ለሚያዩት ሰዎች ነው” ሲሉ መለሱላቸው።
ድብቁ ሽርክ በአንድ ሰው ልቡ ውስጥ እንዳለው የሽርክ አይነት ከሽርከል አክበር ወይም ከሽርከል አስገር ውስጥ ሊሆን ይችላል።
ልክ ሙናፊቆች የውሸት እምነታቸውን ደብቀው እስልምናን እያሳዩ ሽርክን እንደሚፈፅሙት አይነት ትልቁ ሽርክ ሊሆን ይችላል። ከትንሹ የሽርክ አይነትም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ሪያእ (ይዩልኝ)።

በአንድ ወቅት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) “ሰዎች ሆይ! ሽርክን ፍሩ። በጨላማ ጥቁር ድንጋይ ላይ ከምትሄድ ጥቁር ጉንዳን በላይ ድብቅ ነው አሉ። ሶሃባዎች እንዴት እናስወግደው ብለው በጠየቋቸው ጊዜ
‹አሏሁመ ኢኒ ናኡዙ ቢከ ሚን ኑሽሪከ ቢከ ሸይአን ነዕለሙህ፤ ወነስተግፊሩከ ሊማላ ነእለሙ (አሏህ ሆይ! እያወቅን ሽርክ ከመፈፀም ጠብቀን፤ (ሳናውቅ በፈፀምነው) በማናውቀው ምህረትህን እንጠይቃለን።” ሲሉ መለሱላቸው። (አህመድ የዘገበው ሲሆን ሸህ አልባኒ ሐዲሱ ሐሰን ነው ብለዋል)
አሏሁመ ኢና ናኡዙቢከ ሚን ኑሽሪከ ቢከ ሸይአን ነዕለሙሁ ወነስተግፊሩከ ሊማላ ነዕለሙሁ



Share