በእስልምና ውስጥ በብዛት ሰዎች ከሚሳሳቱባቸው ቃላት አንዱ “ጅሃድ” የሚለው ነው።
በሚያሳዝን ሁኔታ “ጅሃድ” የሚለው ቃል አላግባብ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ከጦርነት እና ከአሸባሪነት ጋር ያያይዙታል።
በቋንቋ ደረጃ ጅሃድ ማለት ለበጎ ነገር መጣር ወይም በክፉ ነገር ላይ መታገል ማለት ነው። ጅሃድ በብዙ መንገዶች ይገለጻል።
ነገር ግን በአጠቃላይ ከራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ራስን መቃወም እና መታገል ማለት ነው።
እንዲሁም ጭቆናን ፣ ስደትን ፣ በደልን መቋቋም ወይም ከጨቋኞች እራስን መከላከል ማለት ነው።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ኢብኑ ሐባን)
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ሙጃሂድ (ጅሃድ የሚያደርግ ሰው) ማለት ለአሏህ ሲል የራሱን ፍላጎት እና ስሜት የሚቆጣጠር ነው።”
ጅሃድ ሊገለጽባቸው ከሚችሉ ጥቂት መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሙስሊም ላልሆኑ ሰዎች የእስልምና ሃይማኖት ማሳወቅ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ማስረጃዎችን ከቅዱስ ቁርአን በመጥቀስ ወይም ደጋፊ ማብራሪያዎችን ከማስረጃዎች ጋር በማቅረብ ለእነሱ ግልጽ ማድረግ ነው፡፡
እንዲሁም ትችቶቻቸውን ወይም ክሶቻቸውን በትዕግስት ማዳመጥ እና መልስ መስጠት ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ፉርቃን 25፡52)
“በከሐዲዎችም አትታዘዝ፡፡ በእሱም (በቁርአን) ታላቅን ጅሃድ ታገላቸው፡፡”
በበጎ ማዘዝ እና ከክፉ ነገር መከልከል የነብያት እና የተከታዮቻቸው ተግባር ነው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም)
“አላህ ከእኔ በፊት ነቢይ አላከም ከሕዝቡ መካከል መንገዱን የሚከተሉና ትእዛዙን የሚታዘዙ ደቀ መዛሙርት እና ወዳጆች የነበሩት ቢሆን እንጅ። ከዚያም የማይሠሩትን የሚናገሩና ያልታዘዙትን የሚሠሩ አዳዲስ ትውልዶች መጡ። በእጁ የነበረ ኃይልን በመጠቀም በእነሱ ላይ የታገለ አማኝ ነው። በምላሱ በእነሱ ላይ የታገለ አማኝ ነው። በልቡ በእነሱ ላይ የታገለ አማኝ ነው። ከዚህም ውጭ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እንኳ እምነት የለውም።”

- በአመፀኛ ገዥ ላይ እውነትን መናገር፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ከጅሃድ ሁሉ በላጩ ጅሐድ በአመፀኛ ገዥ ፊት እውነትን መናገር ነው።” (አቡ ዳውድ)
ወላጆችን በአክብሮት መያዝ
አንድ ሰው ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመምጣት በአንድ ጦርነት ላይ ለመሳተፍ ፈቃድ ጠየቃቸው። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰውየውን “ወላጆችህ በህይወት አሉ?” ብለው ጠየቁት። ሰውየውም “አዎ” ሲል መለሰ። ከዚያም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) “እነሱን በመንከባከብ ጅሃድ አድርግ” አሉት። (ቡኻሪ)
እውቀት መፈለግ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ማንኛውም ሰው ወደዚህ መስጊዴ ቢመጣ ፣ የሚመጣውም ለመማር ወይም ለማስተማር ለመልካም ዓላማ ብቻ ከሆነ ደረጃው በአላህ መንገድ ላይ ጅሃድ ከሚያደርግ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ሌላ ዓላማ ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሰው ደረጃው የሌሎችን ንብረት ከሚጠብቅ ሰው ጋር ይመሳሰላል (ማለትም ምንም መልካም ነገር አያገኝም)።” (ኢብኑ ማጃህ)
- እውቀት ለማግኘት መጓዝ የጂሃድ ዓይነት ነው
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
“እውቀትን ፍለጋ ምንገድ የጀመረ ሰው እስኪመለስ ድረስ በአላህ መንገድ ላይ እንደታገለ (ጅሃድ እንዳደረገ) ይቆጠራል።” (ቲርሚዚ)
የአምልኮ ተግባራት መፈፀም
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ተብለው ተጠየቁ፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ኢብኑ ማጃህ)
“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ጅሃድ በሴቶች ላይ ግዴታ ነውን?” እርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- “አዎ። በእነርሱ ላይ ውጊያ የሌለበት ጅሃድ አለባቸው፤ እሱም ሐጅ ወይም ኡምራ ነው።”
- እንዲህም ብለዋል፡- “ኃጢአቶችን ወደ መማር እና መልካም ሥራዎችን ወደ መጨመር የሚያደርሱ ተግባራት አላሳያችሁምን? በአስቸጋሪ ሁኔታዎች (በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ወቅት) ውዱእ ማድረግ ፣ ወደ መስጊድ በሚሄዱበት ጊዜ ብዙ እርምጃዎችን መራመድ እና በመስጊድ ውስጥ ሶላትን መጠባበቅ ነው። በእርግጥ እነዚህ ተግባራት ድንበሮችን ከጠላት ከመጠበቅ ጋር እኩል ናቸው።” (ሙስሊም)
- ሙስሊሞች በህብረተሰባቸው ውስጥ የሞራል ልዕልናን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን የሚሰጡ ጅሃድ እየፈጸሙ እንደሆነ ይቆጠራል።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“ባልቴትን ወይም ድሃን የሚረዳ በአላህ መንገድ ላይ ጅሃድ እንደሚያደርግ ወይም ሌሊቱን ሙሉ ቆሞ እንደሚሰግድ እና ቀኑን ሙሉ እንደሚጾም ሰው ነው።”
ጅሃድ የጦርነት ትግልን ያመለክታል። ይህ ማንኛውንም የጥቃት ድርጊት ለማስቆም የመጨረሻ ሙከራ ተደርጎ ይታያል።
አንዳንድ ጊዜ የፍትህ ሰይፍ የጭቆናን ሰይፍ ለመከላከል አስፈላጊ ነው። ልክ እንደ ፖሊስ ሁኔታ ማለት ነው።
ሆኖም በጦርነት ጊዜ እንኳን ሙስሊሞች ስነ ምግባርን እንዲጠብቁ ታዘዋል።
ሰዎችን ማሰቃየት ፣ እንዲሁም በጦርነት ጊዜ ሲቪሎችን ፣ ሴቶችን ፣ ህጻናትን ወይም አረጋውያንን መጉዳት በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ህጋዊ ጅሃድ ማወጅ የሚችለው የመንግስት አካል ብቻ ነው፤ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አይደሉም።
የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም)
“በአላህ ስም እና በአላህ መንገድ ላይ ተዋጉ… ቃል ኪዳንን አታፍርሱ ፣ አካልን አታጉድሉ፣ ህጻናትንም አትግደሉ።”
እስልምና የአምልኮ ቦታዎችን ማፍረስ ወይም ማርከስ ፣ እንስሳትን መግደል ወይም መጉዳት እና ዛፎችን መቁረጥን ይከለክላል።
በሙስሊሞች እና ሙስሊም ባልሆኑት መካከል በተደረገው ውጊያ ወቅት ከነበብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በኋላ የመጀመሪያው ኸሊፋ የሆኑት አቡበክር አሲዲቅ (ረ.ዐ) ታዛዦቻቸውን እንዲህ በማለት መክረዋቸው ነበር፡-
“አሥር ነገሮችን አዛችኋለሁ። በልባችሁ ያዙአቸው፡ አትክዱ ፣ (የጦር ምርኮን በመስረቅ) አታጭበርብሩ፣ ቃል ኪዳንንም አታፍርሱ። አካልን አታጉድሉ፣ ሴቶችን፣ ህጻናትን ወይም አረጋውያንን አትግደሉ። የዘንባባ ዛፎችን አትነቅሉ ወይም አታቃጥሉ። ፍሬያማ የሆኑ ዛፎችን አትቁረጡ፣ በጎችን፣ ላሞችን ወይም ግመሎችን ለመብላት ካልሆነ በስተቀር አትረዱ። እንዲሁም በገዳማት ውስጥ ተወስነው የሚኖሩ ሰዎችን ታገኛላችሁ፣ ስለዚህም እነርሱንና አምልኳቸውን ተዋቸው።” (ጦበሪ፣ ጥራዝ 3)
አላህ እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
(ሱረቱል አንአም 6:151)
“… አላህ እሱ መግደልን እርም ያደረገውን ነፍስ በህግ ካልሆነ በስተቀር አትግደሉ። ይህን ታውቁ ዘንድ አዘዛችሁ።”

Share