በአካል እና በንግግር የሚገለፁ የአምልኮ ተግባራት የእስልምና ምሰሶዎች ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህም አምስቱ የእስልምና ምሰሶዎች ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡-
የእምነት ምስክርነት ቃል (ሸሐደተይን)
ይህ የእምነት ምስክርነት ቃል ‹‹ከአሏህ በቀር በሃቅ ሊያመልኩት የሚገባ የለም፡፡ ሙሐመድ የአሏህ ባሪያና መልዕክተኛ ነው›› የሚል ነው፡፡ ይህን የምስክርነት ቃል አንድ ሰው በማለቱ ሙስሊም የሚሆንበት ቁልፍ ነው፡፡
‹‹ከአሏህ ውጭ በሃቅ ሊያመልኩት የሚገባ የለም›› የሚለው የመጀመሪያው የምስክርነት ቃል የሚከተሉትን ትርጉም ይይዛል፡፡

- አሏህ የፍጥረተ አለሙ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡
- አሏህ የፍቱሩ ጌታና አስተዳዳሪ የነገሮች ሁሉ አስተናባሪ ነው፡፡
- ሊመለክ የሚገባው አሏህ ብቻ ነው፡፡
ከአሏህ በቀር በሃቅ ሊያመልኩት የሚገባ የለም፡፡ ሙሐመድ ባሪያውና መልዕክተኛው ነው፡፡
ሁለተኛው የምስክርነት ክፍል ‹‹ሙሐመድ ባሪያው እና መልዕክተኛው ነው›› የሚለው ክፍል የሚከተሉትን ትርጉም ይይዛል፡-

- መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ያዘዙትን ነገር መታዘዝ ነው፡፡
- የተናገሩትን ሁሉ ማመን ነው፡፡
- ካስጠነቀቁት እና ከከለከሉት ነገር ሁሉ መራቅ ነው፡፡
- መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) አሏህን በተገዙበት መንገድ አሏህን ማምለክ ነው፡፡
የእስልምና መልዕክተኛ ማን ነው?
እሱ ሙሐመድ ነው፤ የአብዱሏህ ልጅ ፣ የአብዱል ሙጦሊብ ልጅ ፣ የሐሽም ልጅ፡፡ ቅፅል ስማቸው አበልቃሲም ነው፡፡
ከቁረይሽ የአረብ ጎሳ ሲሆኑ የዘር ግንዳቸው የአሏህ መልዕክተኛ የሆነው የእስማኤል ልጅ እስከ አድናን ድረስ ይሄዳል፡፡
ነብዩ ኢስማኤል የአሏህ መልዕክተኛ የሆነው የኢብራሂም ልጅ ነው (ሰላም በእነሱ ላይ ይሁን)፡፡
የተወለዱት በተከበረው መካ ውስጥ በ624ዓ.ሂ ሲሆን በአብርሃም እና በልጁ ኢስማኤል የተገነባው ካዕባ መናገሻ በሆነችው ከተማ ነው፡፡ መካ የአረቢያ ባህረሰላጤ የሃይማኖት ማዕከል ነበር፡፡
የአሏህን ወህይ (ራዕይ) ከመቀበላቸው በፊት እንኳ በህዝባቸው ዘንድ አል-አሚን (ታማኙ) በመባል ይታወቁ ነበር፡፡
ጉዞ ለመሄድ ባሰቡ ጊዜ ንብረቶቻቸውን በአደራ መልክ ለእሳቸው ይሰጡ ነበር፡፡
እንዲሁም ‹‹እውነተኛው›› በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ፈፅሞ ዋሽተው ወይም የክህደት ተግባር ፈፅመው አያውቁም፡፡ ሁልጊዜም ለሌሎች መልካም ነገር ይመኛሉ፡፡
የመጀመሪያውን ራዕይ የተወቀበሉት በአርባ አመታቸው ሲሆን ለሚስታቸው ኸድጃ (ረ.ዐ) አሳወቋት፡፡
‹‹በእርግጥ ለእራሴ እፈራለሁ አሏት፡፡ እሷም (ረ.ዐ) ‹‹አይሆንም! በአሏህ ይሁንብኝ አሏህ ፈፅሞ አያዋርድህም፡፡ በእርግጥ ዝምድናን ትቀጥላለህ ፣ የሌሎችን ሰዎች ችግር ትሸከማለህ ፣ ለሌላቸው ትሰጣለህ ፣ እንግዶችን ታከብራለህ ትመግባለህም ፣ በአደጋ ጊዜ ድጋፍህን ትሰጣለህ አለቻቸው፡፡›› (ቡኻሪ)
ከዚያም በኋላ ሰዎች በአሏህ አንድነት እንዲያምኑ ጥሪ በማድረግ መካ ውስጥ 13 አመት ቆይተዋል፡፡
ከዚያም ወደ መዲና ከተማ ተሰደው ነዋሪዎቿን ወደ እስልምና ተጣሩ፤ ተቀበሏቸውም፡፡ እዚያው እያሉ አሏህ ቀሪውን የሃይማኖቱን ህግጋት ገለፀላቸው፡፡
ከተሰደዱ ከስምንት አመት በኋላ ወደ መካ ተመልሰው መካን ተቆጣጠሩ፡፡
የሞቱት አሏህ ሙሉ ቁርአንን ከገለፀላቸው በኋላ በ63 አመታቸው ነው፡፡ የሃይማኖቱ ህግጋት ሙሉ እና ፍፁም ነው። አብዘሃኛው የአረቢያ ባህረሰላጤ እስልምናን ተቀበለ፡፡
ስለ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ምን ይላሉ?
ጆርጅ በርናርድ ሾው0 ‹‹እውነተኛ እስልምና›› በተሰኘው መጽሐፉ ‹‹የሙሐመድን ሃይማኖት ሁልጊዜም ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ ምክኒያቱም ህያውነት ስላለው ነው፡፡

በየትኛውም ዘመን ማራኪ የሆነ ከህይወት ለውጦች ጋር ተስማምቶ የመሄድ አቅም ያለው ብቸኛው ሃይማኖት ነው፡፡
የሙሐመድ ሃይመኖት በአውሮፓ ቅቡልነት የማግኘት ጅማሮ ላይ ቢሆንም ነገ በስፋት ተቀባይነት እንደሚያገኝ እተነብያለሁ፡፡
የመካከለኛው ዘመን ሃይማኖት ሰዎች በግንዛቤ ማነስ ወይም አግባብ በሌለው ጥላቻ ምክኒያት እስልምናን የማጠልሸት ስራ ሰርተዋል፡፡
በእርግጥ ሙሐመድን እና ሃይማኖቱን ለመጥላት ተምረዋል፡፡ ለእነሱ ሙሐመድ ፀረ-ክርስቶስ ነበር፡፡ እኔ ግን ህይወቱን አጥንቸዋለሁ እጅጉን የሚደነቅ ሰው ነው፡፡
በእኔ አስተያየት ፀረ-ክርስቶስ ከሚባል ይልቅ ‹‹የሰው ልጅ ሁሉ አዳኝ›› ተብሎ መጠራት አለበት፡፡
አኒ ቤንሳንት ‹‹የሙሐመድ ህይወት እና አስተምህሮት›› በተሰኘው መጽሐፉ የታላቁን የአረቢያ ነብይ ህይወትእና ባህሪ ያጠና ፣ እንዴት እንዳስተማረ ፣ እንዴት እንደኖረ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ከታላላቅ መልዕክተኞች አንዱ ታላቅ መልዕክተኛ መሆኑን በመመስከር አክብሮት ከመስጠት በቀር ሌላ ስሜት ሊሰማው አይችልም፡፡
ለእናንተ ብዙ የተለመደ ነገር ልናገር እችላለሁ መላልሸ ሳነባቸው ግን ለዚያ ታላቅ የአረቢያ መምህር አዲስ የአድናቆት እና የአክብሮት ስሜት ይሰማኛል፡፡
ሶላት (ስግደት)
ሶላት የአሏህ ባሪያ ከጌታው ጋር የሚገናኝበት መንገድ ነው፡፡ በሶላት ወቅት ሰው ከጌታው ጋር በግል ይነጋገራል፤ ይቅርታውን ይለምናል ፣ እርዳታ እና መመሪያውን ይጠይቃል፡፡
በየእለቱ መፈፀም ያለባቸው አምስት ሶላቶች አሉ፡፡ ትክክለኛ ምክኒያት ካላቸው በስተቀር በህብረት መስጅድ ውስጥ ይሰግዳሉ፡፡
በዚህ አጋጣሚም ሙስሊሞች እርስ በእርሳቸው ይተዋወቃሉ ፣ ይዋደዳሉ እና አንድነትን ያጎለብታሉ፡፡ የሌሎች ሙስሊሞችን ሁኔታ በየእለቱ ያውቃሉ፡፡
የሆነ ሰው ካልተገኘ እና አሞት እንደሆነ ካሰቡ ሂደው ይጠይቁታል፡፡ በአንዳንድ የግዴታ ተግባራት ላይ ከተሳነፈ ምክር ይሰጡታል፡፡

ማህበራዊ ልዩነቶች ለምሳሌ ዘር ፣ ነገድ ፣ ጎጥ ወ.ዘ.ተ ሁሉም እዚህ ላይ ቦታ የላቸውም፡፡
ሙስሊሞች ወደ አንድ የመካ አቅጣጫ ዞረው ጎን ለጎን ተሰልፈው በተመሳሳይ ጊዜ ይቆማሉ፡፡ ሁሉም አሏህ ፊት ሲቆሙ እኩል ናቸው፡፡
ዘካ (ምፅዋት)
ይህ በጎ አድራጎት ዘካ ማውጣት ያለበት ሙስሊም ሰው ካለው ገንዘብ ትንሹን ፐርሰንት ለተቸገሩ ወንድም እና እህቶቹ የሚሰጥበት ነው፡፡ የሚሰጥበት ቅድመ ሁኔታዎችም አሉ፡፡
አንድ ሙስሊም ሰው የሚሰጠው በፈቃደኝነት እና በመስጠቱ የአሏህን ትዕዛዝ ለመፈፀም ነው፡፡
ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር ግዴታ የሆነበት ምክኒያት በሙስሊሞች መካከል ማህበራዊ መረዳዳትን የሚያጎልበት በመሆኑ ነው፡፡
እንዲሁም ድህነትን እና ድህነት የሚያስከትለውን አደጋ የሚያስቀር ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክኒያት የሃብታም ሰው ልቡ ከስስት ይነፃል፡፡
የደሐ ሰው ልብ ደግሞ ከጥላቻ እና ከቅናት ይነፃል፡፡ ሃብታሞች ከገንዘባቸው አሏህ የደነገገውን ያክል ገንዘብ ሲሰጡ እና ፍላጎቶቻቸውን ሲያሟሉ ያያሉና ነው፡፡
የረመዷን ፆም (ሲያም)

በአመት አንድ ጊዜ የረመዷን ወር ሙሉ መፆም በሁሉም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፡፡ ከንጋት አንስቶ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ሙስሊሞች ፆማቸውን ከሚያፈርሱ ማንኛውም ነገር መቆጠብ አለባቸው፡፡
ለምሳሌ ምግብ ፣ መጠጥ ፣ የግብረስጋ ግኙኝነት ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ፆም በእስልምና አንዱ የአምልኮ ተግባር ነው፡፡ በቀደምት ሃይማኖቶችም የተደነገገ የአምልኮ ተግባር ነበር፡፡
አሏህ እንዲህ ይላል፡
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ፆም ከእናንተ በፊት በነበሩት ህዝቦች ላይ እንደተደነገገው በእናንተም ላይ ተደነገገ፡፡ አሏህን ልትፈሩ ይከጀላልና፡፡”
(አል-ቁርአን 2፡183)
ሐጅ
ሐጅ ማለት አንድ ሰው የተወሰኑ መንፈሳዊ ስነ-ስርአቶችን በተወሰኑ ቦታዎች እና ጊዚያት ለመፈፀም ወደ ቅዱስ የአሏህ ቤት (ካዕባ) የሚደርገው ጉዞ ነው፡፡
ይህ የእስልምና ምሶሶ አዕምሮው ጤናማ የሆነ ፣ የጉርምስና እድሜ ላይ የደረሰ እና በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ማድረግ የሚችል አካላዊ እና የገንዘብ አቅም ያለው ሙስሊም ወንድ እና ሴቶች ላይ ሁሉ ግዴታ ነው፡፡
አሏህ እንዲህ ይላል፡-
“በውስጡ ግልፅ የሆኑ ተአምራቶች የኢብራሂምም መቆሚያ አለ፡፡ ወደ ውስጡ የገባ ሰው ፀጥተኛ ይሆናል፡፡ ለአሏህም በሰዎች ላይ ወደ እሱ መሄድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው፡፡ የካደም ሰው አሏህ ከአለማት ሁሉ የተብቃቃ ነው፡፡”
(አል-ቁርአን 3፡97)

ሐጅ ትልቁ እስላማዊ ስብሰባ ሲሆን አለም ላይ ካሉት ትላልቅ ስብሰባዎች አንዱ እና ትልቁ ነው፡፡ ከመላው አለም የመጡ ሙስሊሞች በአንድ ቦታ እና በአንድ ጊዜ ይሰበሰባሉ፡፡
ሁሉም አንድና ብቸኛ ጌታቸውን ይጠራሉ፤ ተመሳሳይ ልብስም ይለብሳሉ፡፡ እንዲሁም አንድ አይነት መንፈሳዊ ስርአትን ይፈፅማሉ፡፡
በሃብታም እና በድሃ ፣ በነጭ እና በጥቁር ፣ በአረብ እና አረብ ባልሆኑ መካከል ምንም አይነት ልዩነት የለም፤ ሁሉም በአሏህ ፊት እኩል ናቸው አሏህን በመፍራታቸው (በተቅዋቸው) ደረጃ ካልሆነ በቀር፡፡
ሐጅ የሙስሊሞችን ወድማማችነት እና የተስፋቸውን አንድነት የሚያሳይ ክስተት ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው – የአይሪሽ የተውኔት ፀሃፊ እና የለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መስራች ነው፡፡ ‹‹እውነተኛ እስልምና›› ለተሰኘው መጽሐፉ የኦስካር እና የኖቤል ሽልማት በአንድ ጊዜ የተሸለመ ብቸኛው ሰው ነው፡፡


Share