ክፍልሁለት
ህልሟ የደስደስ ያለው ነበርና ህልሟን በሰማ ጊዜ ፈገግ አለና ስጋት አይግባሽ ከሰማይ ወርዳ ወደ አጥር ግቢሽ ስትገባ ያየሻት ፀሀይ በተውራት እና በኢንጅል ወደፊት የመጨረሻ ነብይ ሁነው እንደሚላኩ የተተነበየላቸው ነብይን የሚያመላክት ነውና በህይወት ዘመንሽ ታገኝዋለሽ ቤትሽንም ባለሟል ያደርግልሻል አላት።
ወረቃ ኢብን ነውፈል ጋር ከተገናኘች ብኋላ ሙሐመድን(ሰ.ዐ.ወ) የማግባት ፍላጎቷ በጣም ጨመረ። ነገርግን እንዴት ሃሳቧን መግለፅ እንዳለባት አሁንም ከራሷ ጋር ሙግት ዉስጥ ገባች።
በጣም የቅርብ ጓደኛዋ የሆነችው ነፊሳ መንባህ ዝንባሌዋን አወቀች። እናም አንድ ቀን ለኸድጃ (ረ.ዐ) “ይህ ሰላም የነሳሽ ነገር በጣም የሚያስጨንቅ ነገር አይደለምና ችግሩን እኔ ራሴ እፈታዋለሁ” አለቻት።
ነፊሳ ያለምን ፍርሃት ቀጥ ብላ ወደ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሄደችና የግል ጥያቄ ትጠይቃቸው ዘንድ ፍቃደኝነታቸውን ጠየቀቻቸው። እንድትጠይቃቸው በፈቀዱላት ጊዜ ለምን እንዳላገቡ ጠየቀቻቸው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሃብት ስለሌለኝ አሉ።
ከመኳንንትና ከሃብታም ቤተሰብ የሆነች ውብ ቆንጆ ሴት አንቱን ማግባት ትፈልጋለችና እሷን ለማግባት ፍቃደኛ ነሁን? ስትል ጠየቀቻቸው። ማንነቷን ጠይቀዋት ኸድጃ እንደሆነች ከተረዱ ብኋላ ፍቃደኛ መሆናቸውን ነገሯት።
ኸድጃ (ረ.ዐ) ይህን ስትሰማ በጣም ተደሰተች። ያኔ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) 25 ዓመታቸው ሲሆን ኸድጃ (ረ.ዐ) ደግሞ 40 ዓመቷ ነበር።
ሁለቱ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አጎቶች ሐምዛ (ረ.ዐ) እና አቡጧሊብ ወደ አጎቷ ኡመር ቢን አሰድ ሄደው የጋብቻ ጥያቄያቸውን አሳወቁት። ጥያቄያቸው መልስ አግኝቶ የሰርጋቸውን ቀን ወሰኑ። ሁለቱም ቤተሰቦች ለጋብቻው ቀን ዝግጅታቸውን ጀመሩ።
ሆኖም ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው በተሰባሰቡበት የጋብቻ ቀናቸውን አከበሩ። ያኔ ነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) በህፃንነታቸው ተንከባክባ ያሳደገቻቸው ሃሊማ ሰአዲያ በልዩ እንግድነት ነበር የተጋበዘችው።
ከበአሉ ብኋላ ወደ ቤቷ ስትመለስ ኸድጃ (ረ.ዐ) ሙሐመድን በህፃንነታቸው ተንከባክበሽ ስላሳደግሻቸው ብላ ለውለታዋ የቤት እቃዎችን ፣ ግመል እና 40 ፍየሎችን በስጦታ መልክ ሰጠቻት።
ኸድጃ በትዳሯ የተባረከች ስትሆን ስድስት ልጆችም ነበሯት። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወንድ ልጆቿ ቃሲምና አብዱሏህ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ዘይነብ ፣ ሩቅያ ፣ ኡሙ-ኩልሱም ፣ ፋጢማ (ረዲየሏሁ አንሁም) ሴት ልጆቿ ነበሩ።
ልጆቿ ጀግና ፣ ጎበዝ ፣ ብልህ ልጆች ሲሆኑ ቤቷ በደስታ ፣ በሰላም ፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ የተሞላ ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ በቂ አይመስልም። ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የሆነ ነገር ያጡ ይመስል እጅግ በጣም እረፍት አልነበራቸውም።
በአመት አንዴ ወደ ኺራ ዋሻ ሂደው በተመስጦና በሶላት ለወር ያህል ያሳልፋሉ።
አንድ ቀን ጅብሪል (ዐ.ሰ) በቅፅበት መቶ በእጆቹ ጥብቅ አድርጎ ከአቀፋቸውና አንብብ! አላቸው። ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያልተማሩ እንደሆኑና ማንበብ እንደማይችሉ ነገሩት። ይህ ፍጡር ደግሞ እቅፍ ካደረጋቸው ብኋላ ደጋግሞ አንብብ! አላቸው። በመጨረሻም የመጀመሪያውን የቁርአን ራዕይ ክፍል የሆኑትን አያቶች(አንቀፆች) አነበበ።
“አንብብ! ያሁሉን በፈጠረው ጌታህ ስም። ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው አንብብ! ጌታህ በጣም ቸር ነውና ያ በብዕር ያስተማረ ሰው ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ(በሆነው ጌታህ ስም አንብብ!)።”
{አል-ቁርአን 96: 1-5}
እናም እነዚህን ቁርአናዊ አንቀፆች ካነበበ ብኋላ ጠፋ። ይህ ክስተት በጣም የሚያስፈራ ነበርና ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እየተንቀጠቀጡና ላብላብ እያላቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሆኖም ለተወሰነ ጊዜ ከተኙ ብኋላ ተረጋጉ። ትንሽ ሲታገስላቸው ለሚስታቸው ለህይወቴ እፈራለሁ አሉና ያጋጠማቸውን ክስተት ሁሉ ተረኩላት።
ኸድጃ (ረ.ዐ) በእርግጥ አሏህ ከማንኛውም አይነት አደጋ ይጠብቅሃል። የጓደኝነት እጅህን ለሁሉም ሰው የምትዘረጋ ፣ በፍፁም ዋሽተህ የማታውቅ ፣ እንግዳ ተቀባይ ፣ የሌሎችን ሸክም (ችግር) የምትሸከም ፣ በችግር ላይ ያሉንና የተበደሉን የምትረዳ የሰላም ሰው ነህና አሏህ ማንም እንዲያጠቃህ አያደርግም አለቻቸው።
እነዚህን የሚያፅናኑና የሚያበረታቱ የኸድጃ (ረ.ዐ) ቃላቶች ሊለካ የማይችል ጥንካሬን እና በራስ መተማመንን ፈጠረላቸው። ወዲያውም የአጎቷ ልጅ ወደ ሆነው ወረቃ ኢብን ነውፈል ወሰደቻቸው።
ወረቃ ኢብን ነውፈል ወዲያኑ ነብዩን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳያቸው ዋሻው ውስጥ ከሳቸው ጋር የነበረው ፍጡር ወደ ነብዩ ሙሳ (ዐ.ሰ) ህዝቦቼ የተላከው ጅብሪል (ዐ.ሰ) እንደሆነ ገመተ።
ወረቃ በጊዜው በጣም ሸምግሎ ነበርና ህዝቦችህ እስገድደው ከሐገር ሲያባርሩህ(ሲያሰድዱህ) በህይወት ብኖርና ክስተቱን ባይ እንዲሁም ልረዳህ ብችል ስል ተመኘሁ አላቸው።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በጣም ተገርመው በእርግጥ ይህን በእኔ ላይ ያደርጉታልን? ሲሉ ጠየቁት። ወረቃም ይህ የሰው ልጅ ባህሪ ነው። ሰዎች ከመካከላቸው የተነሳን ነብይ በፍፁም አይደግፉም አይከተሉም ሲል አረጋገጠላቸው። ነገር በምሳሌ እንዲሉ “ነብይ ባገሩ አይከበርም” አላቸው።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከኸድጃ ስድስት ልጆች የነበሯቸው ሲሆን አራቶቹ ሴቶች ሁለቶቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ሴቶቹ ዘይነብ ፣ ሩቅያ ፣ ኡሙ-ኩልሱም እና ፋጢማ (ረዲየሏሁ አንሁም) ናቸው። ታዲያ ሁሉም ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ወደ መዲና ተሰደዋል።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና ሚስታቸው ኸድጃ (ረ.ዐ) ሴት ልጆቻቸውን ለሶሃባዎች ድረዋል። ከነዚም መካከል ዘይነብን ለአቡል አስ ፣ ፍጢማን ለአሊ ቢን አቡጧሊብ ፣ ሩቅያን ለኡስማን ኢብኑ አፍን የዳሩ ሲሆን ኡስማን ኢብኑ አፍን ሩቅያ በሞተችበት ጊዜ ኡሙ ኩልሱምን ደግመው ዳሩለት።
ታዲያ ኡስማን ኢብኑ አፋን ሁለቱን የነብዩን ልጆች በማግባቱ ምክኒያት ዙል ኑረይን (የሁለት ብርሃን ባለቤት) እየተባለ ይጠራል።