ዘመናዊው ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አሁን የደረሱበትን ደረጃ የሚያስተውል ማንኛውም ሰው፣ ይህ በከፊል የእስልምና ስልጣኔ ባስተላለፈው እና ባስተዋወቀው ሰፊ የእውቀት መጠን እና ባፈራው ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ምክንያት እንደሆነ በእርግጠኝነት ይስማማል።

ሲ.ኤች. አስኪንስ(1) እንዲህ ብለዋል፡- “በስፔን የነበሩ አረቦች ለምዕራብ አውሮፓ የአዲሱ ትምህርት ዋና ምንጭ እንደነበሩ በሰፊው ይታወቃል።”
እነሱ የዘመናዊ ሥልጣኔ መሠረቶች ያኖሩ ናቸው። የአየር እና የጠፈር ቴክኒካል መዝገበ ቃላትን(2) የሚመለከት ማንኛውም ሰው ስልሳ በመቶ የሚሆኑት የታወቁ ከዋክብት ከአረብኛ የተገኙ ስሞች እንደተሰጣቸው በእርግጠኝነት ይደመድማል።
የቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት መጽሐፍት እና ሥራዎች በተለይም በአውሮፓውያን የህዳሴ ዘመን ምዕራባውያን የተጠቀሙባቸው ዋና ዋና የማጣቀሻ ጽሑፎች ነበሩ።
እነዚህ ጽሑፎች በአብዛኛው በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውለዋል።
(1) ሲ.ኤች. ሀስኪንስ፣ ቻርልስ ሆሜር፣ 1870–1937፣ አሜሪካዊ የታሪክ ምሁር፣ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ባለሙያ።(2) ዊልያም ኤች. አለን፣ የኤሮስፔስ የቴክኒክ ቃላት መዝገበ ቃላት፣ የመጀመሪያ እትም።

የዱፈሪን እና አቫ ማርከስ እንዲህ ብለዋል፡- “አውሮፓ ከመካከለኛው ዘመን ድቅድቅ ጨለማ ለመውጣት በከፍተኛ ደረጃ የሙስሊም ሳይንስ ፣ የሙስሊም ጥበብ እና የሙስሊም ሥነ-ጽሑፍ ዕዳ አለባት።”(3)
(3) በህንድ የተሰጡ የዱፈሪን ንግግሮች፣ ለንደን 1890፣ ገጽ 24።
ጄ.ኤች. ዴኒሰን እንዲህ ብለዋል፡-

“በአምስተኛው እና በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ የነበረው የዓለም የውድቀት አፋፍ ላይ ቆሞ ነበር።
ሥልጣኔ እንዲኖር ምክንያት የሆኑት እና ለሰዎች አንድነት እና ለአስተዳዳሪዎቻቸው የአክብሮት ስሜት የሰጡት የቀድሞ ስሜታዊ ባህሎች ተዳክመው ምንም ሊተካቸው የሚችል ነገር አልተገኘም።
ያኔ አራት ሺህ ዓመታት የፈጀው ታላቅ ሥልጣኔ የመፍረስ አፋፍ ላይ ነበር። የሰው ልጅም እያንዳንዱ ጎሣ እና ኑፋቄ ከሌላው ጋር በሚጣላበት ፣ ሕግ እና ሥርዓትም በማይታወቅበት ወደዚያ የጭካኔ ሁኔታ የመመለስ ዕድሉ ሰፊ ነበር።
የቀድሞ ጎሣዊ ማዕቀቦች ሃይላቸውን አጥተዋል። በክርስትና የተፈጠሩት አዳዲስ ማዕቀቦች አንድነትን እና ሥርዓትን ከማምጣት ይልቅ መከፋፈልን እና ጥፋትን እያስከተሉ ነበር።
በአሳዛኝ ሁኔታዎች የተሞላ ጊዜ ነበር። ቅጠሎቹ ዓለምን የሸፈኑና ቅርንጫፎቹም የወርቅ ፣ የሥነ ጥበብ ፣ የሳይንስ እና የስነ-ጽሑፍ ፍሬዎችን ያፈራ ግዙፍ ዛፍ መስሎ የነበረው ሥልጣኔ እየተንገዳገደ እና ከውስጡም እየበሰበሰ ነበር።
የሰው ልጅን እንደገና ወደ አንድነት ሊያመጣና ሥልጣኔን ሊያድን የሚችል ስሜታዊ ባሕል ነበርን? መላውን የምሥራቅ እና የደቡብ ዓለም አንድ የሚያደርግ ሰው ሙሐመድ የተወለዱት በእነዚህ ሰዎች መካከል ነበር።”(1)
(1) ጄ.ኤች. ዴኒሰን፣ አሜሪካዊ የሥነ ልቦና ባለሙያ እና የEmotion as the Basis of Civilization ደራሲ፣ ለንደን፣ 1928፣ ገጽ 265, 269።

ይህ ምስል ከአስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን የፀሐይ ሥርዓት ሞዴል ከበግዳድ ያሳያል። (2) ሳቻው፣ ኢ. (1879)። የጥንት ብሔሮች የዘመን አቆጣጠር፤ የአልቢሩኒ “የቀሩት ቅርሶች” ወይም “ያለፉት ምልክቶች” የአረብኛ ጽሑፍ የእንግሊዝኛ ትርጉም፣ ለንደን፡ በታላቋ ብሪታንያ እና አየርላንድ የምስራቃውያን ትርጉም ፈንድ በደብሊው ኤች. አለን የታተመ።
የአውሮፓን የጨለማ ዘመን ማብራት
- ከህንድ፣ ከቻይና እና ከሄለናዊው ዓለም የመነጨው ሳይንሳዊ እውቀት በሙስሊም ሊቃውንት ተፈልጎ የተተረጎመ፣ የተጣራ፣ የተዋሃደ እና የተሻሻለ ሲሆን በእስልምናው ዓለም በተለያዩ የትምህርት ማዕከላት እውቀቱ ወደ ምዕራብ አውሮፓ ተሰራጭቷል። (የሕክምና ታሪክ፣ የአውሮፓ ሕክምና የአረብ ሥሮች፣ ዴቪድ ደብሊው. ቻንዝ፣ ኤም.ኤስ.ፒ.ኤች.፣ ፒኤችዲ። እንዲሁም ይመልከቱ፡ www.hmc.org.qa/hmc/heartviews/H-V-v420%N29/.htm ) በተጨማሪም የሙስሊም ሊቃውንት ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ የትምህርት ዘርፎችን መስርተዋል።
ይህ የሚያሳየው እስልምና በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደነበረውና ለዘመናዊው ዓለም ዕውቀት እድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ነው።
በእርግጥም ሙስሊሞች በሁሉም የቴክኒክ ፣ የሳይንስ እና የአእምሮ ዘርፎች ከፍተኛ እድገት አሳይተዋል።
ከእነዚህም መካከል በተለያዩ ዘርፎች ከላቁ ምሁራን ጥቂቶቹን እዚህ ላይ እንጠቅሳለን።
አል-ኸዋሪዝሚ (780-850 እ.ኤ.አ) በሂሳብ ፣ በአልጀብራ ፣ በሎጋሪዝም እና በጂኦሜትሪ ዘርፎች ታላቅ ምሁር ነበር።
ምናልባትም ከኖሩት ታላላቅ የሂሳብ ሊቃውንት አንዱ ነበር። እንዲያውም የበርካታ የሂሳብ ቅርንጫፎች እና መሰረታዊ ፅንሰ-ሀሳቦች መስራች ነበር። የአልጀብራም መስራች እሱ ነው።
አል-ቢሩኒ (973–1050 እ.ኤ.አ.) በብዙ ዘርፎች ታላቅ ምሁር ነበር። ከሥነ ፈለክ እስከ ሂሳብ ፣ ከሂሳባዊ ጂኦግራፊ እስከ መካኒክስ ፣ ከፋርማኮሎጂ እስከ ታሪክ ድረስ ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽፏል።
አል-ቢሩኒ ምድር በራሷ ዘንግ ላይ ትሽከረከራለች የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ከጋሊልዮ ስድስት መቶ ዓመታት በፊት ተወያይተውበታል!
ጀርመናዊው የምስራቃውያን ምሁር ኢ. ሳቻው ስለ አል-ቢሩኒ እንዲህ ብሏል፡- “እሱ ለሰው ልጅ ከታወቁት ታላላቅ የአእምሮ ባለቤቶች አንዱ ነበር።”(2)
እኛ ሙስሊሞች ደግሞ ለሰው ልጅ ከታወቁ ታላላቅ የአእምሮ ባለቤቶች የእኛ ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንደሆኑ እንናገራለን።
በሕክምና እና በፋርማሲ ዘርፍ የሙስሊም ሊቃውንት በሥራዎቻቸው ዘመናዊ ሕክምናን ለማሳደግ ጥቅም ላይ የዋለ ብዙ እውቀት ትተውልን አልፈዋል። ከእነዚህ ምሁራን መካከል፡-

- ኢብን ሩሽድ (አቬሮስ 1126-1198 እ.ኤ.አ.) የአንዳሉሺያ (ስፔን) ፈላስፋና ሐኪም ፣ የፍልስፍና እና የእስልምና ሕግ ፣ የሂሳብ እና የሕክምና ባለሙያ ነበር።

- ኢብን አን-ነፊስ (1213-1288 እ.ኤ.አ.) የደም ዝውውርን በሳንባ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በመግለጽ በዋነኝነት የሚታወቅ ሐኪም ነበር። ከእንግሊዛዊው ሃርቪ እና ከስፔናዊው ሚካኤል ሰርቬተስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የደም ዝውውርን አግኝቷል።
- አማር ኢብን አሊ አል-ሞሲሊ ኢብን ኢሳ አል-ካሃል በዓይን ሕክምና ከፍተኛ ችሎታ ነበረው። በቀዶ ጥገና ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ ልዩ መሣሪያዎችን ፈጥሯል። ለምሳሌ “መርፌ” (injection syringe) ፣ ባዶ መርፌ።
- አል-ሐሰን ኢብኑ አል-ሐይተም (አልሃዘን 965-1040 አ.ሂ) ታላቅ የሂሳብ ሊቅ ነበር። በኦፕቲክስ ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሥነ ፈለክ ፈር ቀዳጅ ነበር። እንደ ጂያምባቲስታ ዴላ ፖርታ ገለፃ አል-ሐሰን ጨረቃ እና ፀሐይ ከአድማስ ሲቃረቡ የሚታየውን የትልቅነት መጨመር ለመጀመሪያ ጊዜ ያብራራ ሰው ነው። ስለ ኦፕቲክስ የጻፉት ሰባት ጥራዝ ያለው መጽሐፍ ኪታብ አል-መናዚር (የብርሃን መጽሐፍ) ሳይንሳዊ ዘዴን የተጠቀመ የመጀመሪያው ሥራ ሊሆን ይችላል። ንድፈ ሐሳቦችን ለመፈተሽ የሙከራ ውጤቶችን ይጠቀም ነበር።

- አል-መንሱሪ እና አቡበክር አራዚ ታዋቂና ሁለገብ ሐኪሞች ነበሩ። በሕክምናና በፍልስፍና ዘርፎች መሠረታዊና ዘላቂ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

- ሙወፋቅ አል-በግዳዲ እና አቡል-ቃሲም አዛህራዊ የጥርስ ሕክምና ባለሙያዎች ነበሩ። በዚህ ዙሪያ መጽሐፍት የፃፉ ሲሆን በቀዶ ጥገና ሥራዎች ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሣሪያዎችን እና የአጠቃቀም ዘዴዎቻቸውን የሚያሳዩ ሥዕሎችን አስፍረዋል።

አስትሮላብ፡ በሙስሊሞች ለመጓጓዣነት የተፈለሰፈ ጠቃሚ መሣሪያ።
በፊት በኩል ባለው የተጠማዘዘ ሾጣጣዎች ጫፎች ላይ እጅግ ብሩህ የሆኑ ከዋክብትን ቦታዎች ያመለክታሉ።
የእያንዳንዱ ኮከብ ስም በእያንዳንዱ ሾጣጣ ግርጌ ላይ ተጽፏል። የኋላው ሳህን ወይም ማተር በታቀዱ አስተባባሪ መስመሮች የተቀረጸ ነው። ከካምብሪጅ የሳይንስ ታሪክ ዊፕል ሙዚየም።
በጂኦግራፊና በጂኦሎጂ መስክ ብዙ ታዋቂ ምሁራን ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-

ሸሪፍ አል-ኢድሪሲ (1100-1165 አ.ሂ) ካርቶግራፈር ፣ ጅኦግራፈር እና ተጓዥ ነበር። በላቀ የዓለም ካርታ ስራው ይታወቃል። እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያዎችን ፈጥሯል።
ሥልጣኔን በማሳደግ ላይ የተሳተፉ እና አስተዋጽኦ ያደረጉ ብዙ ሙስሊም ምሁራን አሉ።
የበለጠ ማወቅ የሚፈልግ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሕፍትን መመልከት ይኖርበታል። ብዙ ጊዜ በሙስሊሞች የተጻፉ የምርምር ሥራዎች ተሰርቀው በሌሎች ስም በሐሰት ተመዝግበዋል።
ሜጀር አርተር ግሊን ሊዮናርድ(1) እንዲህ ብሏል፡-
“እኛ አሁን በባህል እና በሥልጣኔ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረስን የምናስብ ሰዎች ፣ የአረቦች ከፍተኛ ባህል ፣ ሥልጣኔ ፣ የአእምሮ ብልጫ እና ማህበራዊ ግርማ እንዲሁም የስርዓታቸው ጥንካሬ ባይኖር ኖሮ ፣ ዛሬም አውሮፓ በድንቁርና ጨለማ ውስጥ ተዘፍቃ እንደምትቀር አንገነዘብምን?”


Share