(ስግደት) በሁሉም ወንድና ሴት ሙስሊሞች ላይ ግዴታ ነው። ሶላት የሃይማኖቱ መሰረት እንደሆነ እስልምና ያስተምራል። ከሸሃዳ (የእምነት ምስክርነት ቃል) ቀጥሎ ሁለተኛው የእስልምና ምሰሶ ነው።
በፍርዱ ቀን የሰው ልጆች ከስራዎቻቸው መካከል በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠየቁት ስለ ሶት ነው። ሶላቱ ያማረለት ሰው ይሳካለታል፤ ይቀናዋልም። ሶላቱ የተበላሸበት ሰው ግን ይከስራል፤ ይጠፋልም።

ሶላት በሙስሊሞች እና በከሃዲዎች ፣ በአማኞችና በሙናፊቆች መካከል ላይ የምትገኝ ወሳኝ መመዘኛ ናት። ሶላትን የማይሰግድ ሰው ካፊር (ከሃዲ) ነው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(አህመድ ፣ ትርሚዚ እና ነሳኢ)
“በእኛ እና በእነሱ (በከሃዲዎች) መካከል ያለ መለያ ሶላት ነው። እሱን የተወ ሰው ክዷል።”
እንዲህም ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም ፣ አቡዳውድ እና ነሳኢ)
“በአንድ ሰው ጣኦት አምልኮና በኩፍር መካከል ያለው ሶላት መተው ነው” ብለዋል።
ሶላት አሏህ የሚወደው ፣ ብዙ ትሩፋቶች እና ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑ ምክኒያት ጤናማ አዕምሮ ባላቸው እና ለአካለ መጠን በደረሱ ሙስሊሞች ላይ ሁሉ በቀን አምስት ጊዜ ቀን እና ማታ መስገድ ግዴታ አድርጎ ደንግጎታል። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኒሳዕ 4፡103)
ሶላትን ስገዱ። በእርግጥ ሶላት በሙዕሚኖች ላይ በጊዜያት ተወስና የተደነገገች ናት።
ስለ ጀሐነም ነዋሪዎች አሏህ ሲያሳውቀን እንዲህ አለ፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ሙደሲር 74፡42-48)
በሰቀር (በጀሐነም ሸለቆ) ውስጥ ምን አስገባችሁ ይባላሉ። እነሱም ከሰጋጆች አልነበርንም ይላሉ። ድሆችንም የምናበላ አልነበርንም። ከዘባራቂዎችም ጋር እንዘባርቅ ነበር። እርግጠኛው (ሞት) እስከመጣብን ጊዜ ድረስ በፍርዱ ቀን እናስተባብል ነበር። የአማላጆች ምልጃ አይጠቅማቸውም።
አንድ ወቅት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሶላትን ሲገልፁ እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(አህመድ ፣ ጦበራኒ እና ኢብን ሂባን)
“እሷን የጠበቀ ሰው በትንሳኤው ቀን ብርሃን ፣ ማስረጃ እና መድህን ትሆንለታለች። ነገርግን እሷን ካልጠበቃት በተትንሳኤው ቀን ብርሃንም ማስረጃም መድህንም አትሆነውም። ያን ቀን ከቃሩን ፣ ከፊርአውን ፣ ከሐማን እና ከኡበይ ኢብኑ ኸለፍ ጋር ይዛመዳል” ብለዋል።
ይህ ማለት ከአሏህ መጥፎ ፍጡራኖች ጋር በጀሐነም ውስጥ ይኖራል ማለት ነው። ቃሩን አሏህ በሰጠው እልቆቢስ ፀጋ አመስጋኝ ያልነበረ ነው።
ፈርኦን እኔ እራሴ አምላክ ነኝ ያለ የግብፅ ንጉስ ሲሆን ሐማን ደግሞ የፈርኦን ክፉ አማካሪ ነበር። ኡበይ ኢብኑ ኸለፍ ደግሞ ከቁረይሾች መካከል የሆነ የእስልምና ጠላት ነበር።
አሏህ እኛ የሰው ልጆችን የፈጠረበት አላማ እሱን ብቻ እንድንገዛ ነው። በመሆኑም አለማዊ ስራ ላይ ብንሆን እንኳ የፈርድ (ግዴታ) ሶላቶችን ወቅት ልንረሳ አይገባም።
አምስቱ የፈርድ (ግዴታ) ሶላቶች

1 ሶላተል ፈጅር የጎህ ሶላት ጊዜው የሚጀምረው ጎህ ሲቀድ ጀምሮ ፀሐይ እስከ ምትወጣበት ጊዜ ድረስ ነው። በሰአቱ ቀደምብሎ መስገድ የተወደደ ነው።

2 ሶላቱ ዙሁር የቀትር ሶላት የሚጀምረው ፀሐይ ሜሪዲያንን ካቋረጠች ጊዜ ጀምሮ የአንድ ነገር ጥላው ከእራሱ ርዝመት ጋር እኩል እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ነው።

3 ሶላቱል አስር የቀትር በኋላ ሶላት የሚጀምረው ከቀትር በኋላ የአንድ ነገር ጥላው ከእራሱ ርዝመት ጋር እኩል ከሚሆንበት ጊዜ አንስቶ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ነው።

4 ሶላቱል መግሪብ የጥልቀተ ፀሐይ ሶላት የሚጀምረው ፀሐይ ከአድማሱ ከጠፋበት ጊዜ አንስቶ ቀዩ የብርሃን ወጋግን እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ ነው።

5 ሶላቱል ኢሻ የምሽት ሶላት የሚጀምረው ቀዩ የብርሃን ወጋግን ከጠፋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ግማሽ ድረስ ነው።
የሶላት ትሩፋት ከንፅፅር በላይ ነው። ፀጋዎቹ ወሰን የለሽ ናቸው። ሶላታቸውን በጥሩ ሁኔታ የሰገዱ ሰዎች የአሏህን ታላቅነት የተቀበሉ ፣ ልቦቻቸው በእሱ ፍራቻ እና ተስፋ የተሞሉ ናቸው። በቀን አምስት ጊዜ ከጌታቸው ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ። ይህም ከሃጢያት አይነቶች ሁሉ እንዲርቁ ይረዳቸዋል። ቅዱስ ቁርአን እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል አንከቡት 29፡45)
ሶላትን ስገዱ፤ በእርግጥ ሶላት ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና። አሏህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው።
ሶላት በጊዜ ተወስና የተደነገገች በመሆኑ ሙስሊሞች ሰአት አክባሪ እንዲሆኑ ታስተምራለች።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ኒሳዕ 4፡103)
ሶላት በሙስሊሞች ላይ በጊዚያት ተወስና የተደነገገች ናት።

ሶላት የጀግንነት እና የትዕግስት ምንጭ ናት። በችግር እና በጭንቀት ጊዜ እርዳታ የማግኛ መንገድም ነው። አሏህ በቁርአኑ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡45)
እርዳታን በትዕግስት እና በሶላት ፈልጉ።
ሙስሊሞች ዘወትር የአሏህን ሽልማት ፈልገው በፈፀሟት ጊዜ ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ ይከለከላሉ። መልካም ነገሮችን መስራት ይበልጥ ይተጋሉ። በጀመአ አብረው በሰገዱ ጊዜ ደግሞ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን ይፈጥራሉ። ይህን ወንድማዊ እና እህታዊ ትስስር እንደ ውዴታ ፣ ደግነት ፣ መከባበር እና ትብብር ባሉ ባህሪያት ይጠነክራል።
ኢስላምን ተመልከቱ




Share