ሐጅ አምስተኛው የእስልምና ምሰሶ ሲሆን በገንዘቡ እና በአካሉ የአሏህን ቤት መጎብኘት የሚችል ሰው በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ይህን የማድረግ ግዴታ አለበት። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ኢምራን 3፡97)
“ለአሏህ ሐጅ ወደ ቤቱ ጉብኝት (ለማድረግ) ወጭውን መሸፈን በሚችሉ ሰዎች ላይ ሁሉ ግዴታ ነው።”


ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በገለፁበት እና ሰርተው ባሳዩበት መንገድ የሐጅ ተግባራትን ለመፈፀም ፣ አሏህን ለማላቅ ፣ ለማስታወስ ፣ ምህረቱን ለመለመን በመፈለግ ከሁሉም ሐገር ፣ ጎሳ ፣ ቀልም የሆኑ ሙስሊሞች በእምነታቸው የሚሰባሰቡበት ትልቁ አመታዊ ስብስብ ነው።
በዚህ ስብሰባ ወቅት እርስ በእርሳቸው ይተዋወቃሉ፤ በጋራ ጉዳያቸው ዙሪያ ይወያያሉ። ሐጅ የኢስላም አለም አቀፋቀዊነት እና የሙስሊሞች አንድነት እና እኩልነት ማሳያ ነው።
እንዲሁም ሐጅ ሙስሊሞች ለፈጣሪያቸው ሲሉ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን በመተው ለአሏህ አገልግሎት መዘጋጀታቸውን የሚያረጋግጡበት ነው።
ሐጅ ለአሏህ ሲሉ አለማዊ ነገሮችን ሀብት ፣ ቤተሰብ ፣ ጓደኛ ፣ ባህል ፣ ዘር፣ ጎሳ በመተው እራሳቸውን ወደ አሏህ የሚያቀርቡበት ነው።
ሁላቸውም በልብሳቸው እና መስራት ባለባቸው ነገር እኩል ናቸው። ልክ በፍርዱ ቀን ከአሏህ ፊት ሁሉም እኩል ሆነው እንደሚቆሙት ማለት ነው።
በእርግጥ የሙስሊሞችን አንድነት የሚያጠክር ከዚህ አመታዊ ትልቅ ስብሰባ የበለጠ ምንም ነገር የለም። ምክኒያቱም ከተለያየ የአለም ክፍል የሆኑ ሙስሊሞች ኢማናቸውን ለመሙላት አንድ ላይ ይሰባሰባሉና።

ሐጅ ከተለያየ የአለም ክፍል የሆኑ ሰዎች በአንድ አሏህ ብቻ በማመናቸው ወደ አንድነት የሚያመጣና በመንድማማችነት ገመድ የሚያስተሳስር መሆኑ ድንቅ ማሳያ ምስል ነው።
ነፍስን ያጠራል፤ ታላቅ ባህርያት ለምሳሌ ልክ እንደ ደግነት ፣ ትሁትነት ፣ ጠንካራነት እና ይሉኝታ ያሉ ባህርያት ያሳያል።
ሁጃጆች ሁሉንም መጥፎ እና የክፋት ተግባራት እንዲያስወግዱ ፣ እንዲታገሱና ተግተው እንዲፈፅሙ አሏህ አዟቸዋል። አሏህ በቁርአን እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡197)
ሐጅ በሚታወቁ ወራቶች ውስጥ ነው። ሐጅ ማድረግ ያሰበ ሰው በሐጅ ወቅት ግብረስጋ ግኑኝነት አይፈፅም ፣ ሃጢያትም አይፈፅም ፣ አይጨቃጨቅ አይከራከርም።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ሐጅ ታላቅ ትሩፋቶች ተናግረዋል። በላጩ ስራ ምንድን ነው ተብለው በተጠየቁ ጊዜ “በአሏህ እና በመልዕክተኛው ማመን ነው። ከዛስ ቀጥሎ ተብለው ተጠየቁ። በአሏህ መንገድ በጀሐድ መሳተፍ ነው ሲሉ መለሱ። በድጋሚ ከዛስ ቀጥሎ ተብለው ተጠየቁ። እሳቸውም ሐጅ መብሩር ማድረግ ነው ሲሉ መለሱ። (ቡኻሪ)

ሐጅ መብሩር ማለት የአሏህን ውዴታ በመፈለለግ ብቻ እና በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና መሰረት የተፈፀመ ሐጅ ነው። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“ለአሏህ ሲል ሐጅ ያደረገ እና እንቶ ፈንቶ ያላወራ ወይም ከግብረገብ ውጭ የሆነ ነገር ያልሰራ ሰው ልክ እንደተወለደበት ቀን ንፁህ ሆኖ ይመለሳል።”
ሶስት የሐጅ አይነቶች

- ሐጅ አተመቱ፡ በሐጅ ወራት ወቅት በማንኛውም ጊዜ መጀመሪያ ኡምራ ማድረግ እና ከኡምራ ቡኋላ የኢህራም አልባሳትን ማውለቅ። በዛው አመት በስምንተኛው የዙልሂጃ ቀን ሐጅ ለማድረግ በድጋሚ ኢህራሙን መልሶ ማድረግ አጠቃሎ ይይዛል።
- ሐጅ አል-ኢፍራድ፡ ለሐጅ ብቻ ኢህራም ማድረግ እና ሐጁ እስኪያበቃ ድረስ በዛው ሁኔታ ላይ መቆየትን የሚይዝ ሲሆን ኡምራ ማድረግ አያስፈልግም።
- ሐጅ አል-ቂራን፡ ለኡምራም ለሐጅም ኢህራም ማድረግን ይይዛል።
ሐጅ ተመቱ እና ሐጅ አል-ቂራን ባደረጉ ሰዎች ላይ ብቻ የእርድ እንስሳ መስዋዕት ማድረግ ግዴታ ነው። ሐጅ አል-ኢፍራድ ያደረጉ ሰዎች ግን የእርድ እንስሳ መስዋዕት ማድረግ አይጠበቅባቸውም።
ሐጅ እንዴት እንፈፅም?
የተርዊያ ቀን ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ቀን ሁጃጆች ወደ ሚና ያቀናሉ። ሐጅ አተመቱ እያደረጉ ከሆነ ኢህራማቸውን በድጋሜ አድርገው መካን ትተው ይሄዳሉ። እናም “ለበይከሏሁመ ሐጁን” (አሏህ ሆይ! ለአገልግሎተ ሐጅ ላደርግ እዚኸው ነኝ) ይላሉ።
ሐጅ አል-ቂራን ወይም ሐጅ ኢፍራድ የሚያደርጉ ከሆነ ኢህራሙን ደግመው ሳያደርጉ ሚናን ለቀው ይሄዳሉ።
በዙልሂጃ በዘጠንኛው ቀን ፀሐይ ከወጣች ቡኋላ ደስ በሚል አኳኋን ሌሎች ሁጃጆችን ሳይጎዱ ወደ አረፋ ያቀናሉ። እስከቻሉት ድረስ ተልቢያውን ደጋግመው ይላሉ። የዙሁር እና የአስር ሶላት ለእያንዳንዱ ሁለት ረከአ አሳጥረው ወይም ቀጥለው አንድ ላይ ይሰግዳሉ።
በአረፋ ክልል ውስጥ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና ፀሐይዋ እስክትጠልቅ ድረስ መቆየት ይኖርባቸዋል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳረጉት ወደ ቂብላ ዞረው እጃቸውን አንስተው ሃያሉ አሏህን በማመስገን እና ዱአ በማድረግ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

ፀሐይዋ በጠለቀች ጊዜ ደስ በሚል ሰላም በተሞላበት አኳኋን ወደ ሙዝደሊፋ ይሄዳሉ። እዛ በደረሱ ጊዜ የመግሪብና የኢሻ ሶላት አሳጥረው እና ቀጥለው ይሰግዳሉ። ሙሉ ለሊቱንም ሙዝደሊፋ ውስጥ ያሳልፋሉ።
በዙል ሂጃ አስረኛው ቀን ላይ የፈጅር ሶላት ከሰገዱ ቡኋላ ሁጃጆች ወደ ቂብላ ዞረው በመቆም እና ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያደርጉት እንደነበረው እጃቸውን ከፍ በማድረግ እስከቻሉት ድረስ ብዙ ዱዘዎችን ያደርጋሉ። ፀሐይዋ ከመውጣቷ በፊት አድማሱ ፈገግ ማለት ሲጀምር ወደ ሚና ይሄዳሉ።
ሙዝደሊፋ ወይም ሚና ውስጥ በሰበሰቡት ሰባት ጠጠሮች ሚና ውስጥ የሚገኘውን የአቀባን ምሰሶ ይመታሉ። ሐጅ አል-ቂራን ወይም ሐጅ አተመቱ እያደረጉ ከሆነ ደግሞ የእርድ እንስሳ መስዋዕት ያደርጋሉ። ወንዶች ፀጉራቸውን ይላጫሉ ወይም ደግሞ ያሳጥራሉ።
ሴቶች ከፀጉራቸው የሚቆርጡት የጣታቸውን ጫፍ እርዝመት ታህል ብቻ ነው። እነዚህን ተግባራቶች በቅደም ተከተል መስራቱ በላጭ ነው። ነገርግን ቅደምተከተሉን ሳይጠብቁ በሚያመች መልኩ መስራትም ችግር የለውም።
እነዚህን ሶስት ተግባራት ከፈፀሙ ቡኋላ ሁጃጆች ኢህራሙን ማውለቅ ይችላሉ። አሁን ሁሉም ገደቦች ተነስተውላቸዋል፤ ከሚስት ወይም ከባል ጋር ግብረ ስጋ ግኙኝነት ማድረግ ሲቀር።
ከዚህ በኋላ ጠዋፍ አል-ኢፍዷ እና ሰኢ ለመፈፀም ወደ መካ ከተማ ይሄዳሉ። ሁጃጁ የሚፈፅመው ሐጅ አል-ቂራን ወይም ሐጅ አል-ኢፍራድ ከሆነና መካ ውስጥ እንደደረሰ በመጀመሪያው ጠዋፍ ጋር ሰኢውን ቀድሞ ከመፈፀመ ከእሱ የሚጠበቀው ሰኢውን ሳይፈፅም ጠዋፍ አል-ኢፍዷ ብቻ ማድረግ ነው።
ጠዋፍ አል-ኢፍዷ እና ሳኢውን ከፈፀሙ ቡኋላ ሁሉም የኢህራም ክልከላዎች ይነሳሉ፤ ሁጃጆችም የተለመደው ተግባራቱን መቀጠል ይችላሉ።
ሁጃጆች ወደ ሚና ተመልሰው ሶስት ለሊቶችን እዛው ያሳልፋሉ። ነገርግን በሶስት ሌሊቶች ፈንታ ሁለት ሌሊቶችን ማሳለፍ ይፈቀዳል።
በእያንዳንዱ በእነዚህ ሁለት ወይም ሶስት ቀናት ከቀትር ቡኋላ በማንኛውም ጊዜ ሁጃጆች ሶስቱን ምሰሶዎች ማለትም መጀመሪያ ትንሹን ምሰሶ (ጀምራህ) ፣ በመቀጠል መካከለኛውን ምሰሶ እና በመጨረሻም ትልቁን ምሰሶ በጠጠር ይመታሉ።
በእነዚህ በእያንዳንዱ ምሰሶዎች ላይ አንድ በአንድ አሏሁ አክበር እያሉ ሰባት ጠጠሮችን ይረውራሉ። የመጀመሪያውን ምሰሶ በድንጋይ ከመቱ በኋላ ወደ ቀኙ የምሰሶ ክፍል በመሄድ ወደ ቂብላ ዙረው እስከቻሉት ድረስ ዱአ ያደርጋሉ።
ሁለተኛውን ምሰሶ በጠጠር ከመቱ በኋላ ደግሞ በግራ በኩል ወደ ሚገኘው ምሰሶ ይሄዱና ወደ ቂብላ ዞረው በመቆም እስከቻሉት ድረስ ዱአ ያደርጋሉ። ሶስተኛውን ምሰሶ በጠጠር ከመቱ በኋላ ምንም ዱአ ሳያደርጉ ይሄዳሉ።

የመካ ነዋሪ ያልሆኑ ሁጃጆች የሐጅ ተግባራትን ከፈፀሙ ቡኋላ ወደየ መጡበት አካባቢ ከመመለሳቸው በፊት ወደ መካ ተመልሰው በመሄድ ጧፍ አል-ወዷእ (የስንብት ጠዋፍ) ያደርጋሉ። ሐይድ (የወርአበባ) ወይም የወሊድ ደም ላይ የሆኑ ሴቶች ብቻ ከእንዲህ አይነቱ ጠዋፍ ነፃ ናቸው።
በእርግጥ ሁጃጆች ይህን ጠዋፍ ካደረጉ ቡኋላ ለረዥም ጊዜ መካ ውስጥ መቆየት የለባቸውም አሳማኝ ምክኒያት እና በጣም አሰስፈላጊ ነገር ሆኖ ካልሆነ በቀር።
አረፋት ፣ ኢህራም ፣ ሚና ፣ ሙዝደሊፋ ፣ ሰኢ እና ጠዋፍ ተመልከቱ




Share