የነብዩ ሙሐመድ ታሪክ 1

Author picture

Table of Contents

የትውልድ ቦታ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱት የመጀመሪያው ሰው አደም (ዐ.ሰ) የመጀመሪያውን የአምልኮት ቤት የቆመባት የጥንት የሰው ልጅ መኖሪያ ከሆነችው መካ ከተማ ነው።

ይህ ከተማ አረቢያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በአንፀባራቂ አሸዋና ገላጣ ኮረብታዎች የተሸፈነና በቀይ ባህር እና በሶሪያ መካከል የሚገኝ ትልቅ የበረሃ መሬት ነው። ይሁንእንጂ በሂጃዝ ክልል ውስጥ ትንሽ ለምለም ቦታ ይገኛል።

የሙስሊሞች የስልጣኔ መፍለቂያ ፣ የአለም የከተሞች እናት የሆኑት መካ ፣ መዲና ጅዳ የሚገኙት በዚሁ ክልል ውስጥ ነው።

የዘር ሐረግ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱት የአብዱል ሙጦሊብ ልጅ ከሆነው አብዱሏህ ነው። አብዱል ሙጦሊብ የሐሽም ልጅ ፣ የአብድ መናፍ ልጅ ፣ የቁሰይ ልጅ ፣ የቂላብ ልጅ ፣ የሙራህ ልጅ ፣ የካእብ ልጅ ፣ የሉዋእ ልጅ ፣ የጋሊብ ልጅ ፣ የፋህር ልጅ ፣ የማሊክ ልጅ እያለ እስከ አድናን ልጅ ድረስ ይደርሳል።

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የዘር ሐረግ ከነብዩ ኢብራሂም ልጅ (ዐ.ሰ) ታላቅ ልጅ ከሆኑት ከነብዩ ኢስማኢል(ዐ.ሰ) እንደሚጀምር ሁሉም ሙስሊሞች እና ትክክለኛ የታሪክ ፀሃፊያኖች የሚስማሙበት ነው።

የነብዩ ሙሐመድ አባት

የተከበሩት አባታች ስም አብዱላህ ሲሆን ትርጉሙም የአሏህ ባሪያ ማለት ነው። እሳቸውም መልከ መልካም ፣ የትልቅ ስብዕና ባለቤት ግንባራቸው ጥልቅ የሆነ ብርሃን የሚያንፀባርቅ የነበሩ የአብዱል ሙጠሊብ ልጅ ናቸው።

የሞቱትም በሃያ አምስት አመታቸው ሲሆን በዚያን ጊዜ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከናታቸው ማህፀን ነበሩ።

የነብዩ ሙሐመድ እናት

የእናታቸው ስም አሚና ነው። አሚና የወሐብ ልጅ ሲሆኑ ወሐብ ደግሞ የሐሽም ልጅ ናቸው። እናታቸው በቁንጅናቸው ፣ በደግነታቸው ፣ በትሁትነታቸው ፣ በቅዱስነታቸው ይታወቃሉ።

እሳቸውም ሲሞቱ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የ6 አመት እድሜ ልጅ ነበሩ።

የነብዩ ሙሐመድ ውልደት

የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ውልደት በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ለነበረው አለም ብርሃን ሆኗል። የአረቢያ ምድር በሃጢያትና በጥንቆላ ፅልመት ተዘፍቆ በነበረው በዚህ በሚያስጠላ ዘመን የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በመካ ከተማ ውስጥ መወለድ ለአለም ብርሃን ሆኗል።

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱት በመጀመሪያው አመል ፊል (የዝሆኖች) ጦርነት አመት በ12ኛው ረቢኡል አወል እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 570 በተወለዱ በሰባተኛው ቀን በማለዳ ፀሀይዋ ከመውጣቷ በፊት ለአሏህ ምስጋና ለማድረስ የእርድ ስነ-ስርአት ተካሄደ።

ሁሉም የቁረይሽ ማህበረሰብ ወደ ድግሱ ተጠራ ፤ ሰዎቹም የልጁ ስም ማነው? ብለው በጠየቁ ጊዜ አያታቸው አብዱል ሙጠሊብ ሙሐመድ ሲሉ መለሱላቸው።

ከተለመደው ስም አፈንግጠው ይህን ቅዱስና ልዩ የሆነ ስም ለዚህ ልጅ ለምን እንደተሰጠው ጠየቇቸው። እሳቸውም የኔ ልጅ የሙሉ አለም ምስጋና አድናቆት ይገባዋል ሲሉ መለሱላቸው።

ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ማለት በጣም ምስጉን ማለት ነው። የመካ እምነተ ቢሶች ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከአንድ ንጉስ መወለድ አለበት ሲሉ ተቃወሙ። የአሏህ ምርጫ ግን ሙሐመድ ቢን አብዱ ሏህ ነበሩ።

የጠቡባቸው ቀናቶች

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በጣም ደግ ለሆነችው ሐሊማ እንድታጠባቸው በአደራ መልክ ተሰጠች። ህፃኑንም ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ማጥባት በጀመረች ጊዜ የቻለችውን ያህል በሁለቱም ጡቶቿ ለማጥባት ስትሞክር እሳቸው ግን በግራ ጡቷ በፍፁም ጠብታ ታህል አይጠቡም።

ይህ ነው እንግዲህ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዴት የሐሊማን ልጅ መብት ገና በህፃንነት እድሜያቸው የጠበቁት። ሁለት አመት ያህል ካጠባቻቸው ቡሃላ መልሳ ወደ እናታቸው መለሰቻቸው።

ነገር ግን እናታቸው መልሰው እንደገና እስከ ስድስት አመታቸው ድረስ በዚያ ንፁህ በሆነው የአረብ ጐሳቸው ማህበራዊ አድርጋ እንድታሳድጋቸው በድጋሚ በአደራ መልክ ተሰጣት።

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top