መግቢያ
በታሪክ ውስጥ እንደ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በወዳጅም በጠላትም ብዕር በስፋት የተዘገበላቸው ፣ ስብዕናቸው የተተነተነና ተጽእኗቸው የተመሰከረላቸው ታላቅ መሪ ይኖር ይሆን?
ብዙ ጊዜ ስለ እሳቸው የሚነገረው ከተከታዮቻቸው አንደበት ቢሆንም ከእስልምናው ዓለም ውጪ ያሉ ታላላቅ ፈላስፎች ፣ የታሪክ ምሁራንና ጸሐፍት ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች የሳቸውን ታላቅነት በሌላ መነጽር ያሳዩናል።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የዓለማችን ስመጥር ምሁራን ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች ቀርበዋል።
እነዚህ ገለልተኛ እይታዎች ስለ እርሳቸው ልዩ ባህሪ ፣ አመራር ጥበብና በዓለም ላይ ስላመጡት ዘላቂ ለውጥ ጥልቅ ግንዛቤ በመስጠት ያስደምሙዎታል።
ከወዳጆች ብዕር ባሻገር
የአንድን ሰው ታላቅነት ለመለካት ከሚረዱ ዋነኛ መንገዶች አንዱ ፣ ተከታዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ፣ ሌላው ቀርቶ ተቀናቃኞቹ እንኳ ስለ እርሱ የሚሰጡት ምስክርነት ነው።
የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ህይወትና አስተምህሮ ባለፉት 14 ክፍለ ዘመናት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሙስሊሞች የብርሃን ምንጭ ሆኗል።
ነገር ግን የእሳቸው ተጽዕኖ በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም።
ከእስልምና ውጪ የነበሩና ያሉ በርካታ የዓለማችን ምሁራን ፣ የታሪክ ሰዎችና ፈላስፎች ስለ እሳቸው ስብዕና ፣ አመራርና በታሪክ ላይ ስለፈጠሩት የማይፋቅ አሻራ በጥልቀት መዝግበዋል።
ይህ ጽሑፍ ከእነዚያ ምስክርነቶች ጥቂቶቹን በመሰብሰብ ያቀርባል።
ከፈረንሳይ ምሁራን የተሰጡ ምስክርነቶች
- “እሱ ፈላስፋ ፣ አንደበተ ርቱዕ አስተማሪ ፣ መልክተኛ እና ሕግ አውጪ ነው፤ ለአዳዲስ አስተሳሰቦች በር ከፋች እና ለምክንያታዊ እምነቶች ዋቢ ነው፡፡ በምድር ላይ የሃያ ኢምፓየሮች እና የአንድ መንፈሳዊ ኢምፓየር መስራች ነው፡፡ እሱም ነብዩ ሙሐመድ ነው! በሰው ልጅ ታላቅነት መለኪያ መስፈርቶች ሁሉ ቢለካ፤ ‘ከእሱ የበለጠ ታላቅ ሰው አለን?’ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል።”
አልፎንስ ዴ ላማርቲን ፣ “የቱርክ ታሪክ”፣ ቅጽ 1፣ ገጽ 276-280
- “የዓላማ ታላቅነት ፣ የመሳሪያዎች ትንሽነት እና የተገኘ ትልቅ ውጤት የሰውን ልጅ ብልህነት የሚለኩ ሦስት መስፈርቶች ከሆኑ፤ በታሪክ ውስጥ ከታላላቅ ሰዎች መካከል ከሙሐመድ ጋር ሊወዳደር የሚደፍር ማን ነው?! የታወቁ ታላላቅ ሰዎች የፈጠሩት የጦር መሳሪያዎችን ፣ ህጎችን እና ኢምፓየሮችን ብቻ ነው። የሆነ ነገር መሥርተው ከሆነም፤ በአብዛኛው በዓይናቸው እያዩ የሚፈርሱ ቁሳዊ ኃይሎችን ብቻ ነው የመሠረቱት።”
አልፎንስ ዴ ላማርቲን፣ “የቱርክ ታሪክ”
- “እንደ ሙሐመድ እጅግ በጣም በደከሙ መንገዶች ከሰው ልጅ አቅም ያለፈ ሥራ የሰራ ማንም የለም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ታላቅ እጣ ፈንታ ለመፀነስም ሆነ ለማሳካት ከራሱ በስተቀር ምንም የሚረዳው አልነበረውም፡፡ በበረሃ ዳርቻ ከነበሩ ጥቂት የገጠር ሰዎች ውጭ የሚረዳው አልነበረም።”
“የቱርክ ታሪክ፡ “አልፎንስ ዴ ላማርቲን
- “በፍጡርና በፈጣሪ መካከል እንቅፋት የነበሩ አጉል እምነቶችን ማፍረስ ፣ የአምላክ ግንኙነት ከሰው ጋር እና የሰውንም ከአምላክ ጋር መመለስ ፣ በዚያን ጊዜ በነበረው የጣዖት አምልኮ ውስጥ በነበሩ ቁሳዊ አማልክትን በማስወገድ ምክኒያታዊና ቅዱስ የሆነውን አምልኮት ሐሳብ እንደገና ሟቋቋም – ይህ ከሰው አቅም በላይ የሆነ ክቡር አላማ ነው፡፡ እንደ እሱ ያለ ማንም ሰው በፍላጎቱም ይሁን ያለ ፍላጎቱ እንዲህ ያለን ታላቅ አላማ ለእራሱ አላስቀመጠም።”
አልፎንስ ዴ ላማርቲን፣ “የቱርክ ታሪክ”
- “ይህ ሰው በዚያን ጊዜ በሦስተኛው የዓለም ክፍል ውስጥ የነበሩ ሰራዊቶችን ፣ ህጎችን ፣ ኢምፓየሮችን ፣ ህዝቦችን ፣ ገዢ ሥርወ-መንግሥታትን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያንቀሳቀሰ ብቻ አልነበረም፤ ከዚያም በተጨማሪ ቅዱሳን ቦታዎችን ፣ አማልክትን ፣ ሃይማኖቶችን ፣ አስተሳሰቦችን ፣ እምነቶችን እና ነፍሶችን አንቀጥቅጧል።”
አልፎንስ ዴ ላማርቲን፣ “የቱርክ ታሪክ”
- “በዓለም ላይ እንደዚህ ያለ ግዙፍ እና ቀጣይነት ያለው አብዮት ማምጣት የቻለ ማንም ሰው የለም፤ እስልምና ከተገለጠ ከሁለት መቶ ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በእምነቱና በሰራዊቱ ተስፋፍቶ የአረብ ባሕረ ገብ መሬትን በሙሉ ተቆጣጠረ፤ በአሏህ አንድነትም የፋርስን ፣ የኹራሳንን ፣ የትራንዞክሲያናን (የአሁኗ ኡዝቤኪስታን እና አካባቢዋን) ፣ የምዕራብ ህንድን ፣ ሶሪያን ፣ ግብጽን ፣ ኢትዮጵያን ፣ በሰሜን አፍሪካ የሚታወቀውን አህጉር በሙሉ ፣ በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ያሉ በርካታ ደሴቶችን ፣ ስፔንን እና የጋል (ፈረንሳይ) ክፍልን ከፍቷል።”
“የቱርክ ታሪክ፡ “አልፎንስ ዴ ላማርቲን
ከአየርላንድ ምሁራን የተሰጡ ምስክርነቶች
- “እንደ እሱ ያለ ሰው ዘመናዊውን ዓለም በአንባገነንነት ቢቆጣጠር፤ ለዓለም ሰላምንና ደስታን በሚያመጣ መንገድ ችግሮቿን ሁሉ በመፍታት እንደሚሳካለት አምናለሁ። የሙሐመድ ሃይማኖት ወደፊት በአውሮፓ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተንብዬ ነበር፤ አሁን በአውሮፓ ተቀባይነት ማግኘት ጀምሯል።”
ጆርጅ በርናርድ ሻው፣ “እውነተኛው እስልምና” በተሰኘ መጽሐፉ
- “ሁልጊዜም የሙሐመድን ሃይማኖት በሚያስደንቅ ህያውነቱ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ አየዋለሁ። በእኔ እምነት፤ በዚህ ተለዋዋጭ የሕይወት ምዕራፍ ውስጥ እራሱን በማዋሃድ ለእያንዳንዱ ዘመን ማራኪ የመሆን ችሎታ ያለው ብቸኛው ሃይማኖት ነው። ያንን ታላቅ ሰው አጥንቼዋለሁ፤ በእኔ አስተያየት እሱ ፀረ-ክርስቶስ ከመሆን የራቀ ነው፡፡ ይልቁንም ‘የሰው ልጅ አዳኝ’ ተብሎ መጠራት አለበት።”
ጆርጅ በርናርድ ሻው፣ “እውነተኛው እስልምና” በተሰኘ መጽሐፉ
ከህንድ ምሁራን እና መሪዎች ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች
- “ሙሐመድ ከእሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከነበሩት ነብያት ሁሉ በሁሉም መስፈርቶች በላቀ ደረጃ ላይ ያለ፤ የነብያቶች ሁሉ ታላቅ ነው። የእስልምና መስፋፋት እጅግ አስደናቂ ሲሆን የተአምራቶች ሁሉ ተአምር ነው።”
ማናቤንድራ ናዝ ሮይ፣ “የእስልምና ታሪካዊ ሚና”
- “የህይወቱ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል፤ ነገርግን የአምላክ ነብይ አልተለወጠም። በድልም ሆነ በሽንፈት ፣ በሃይልም ሆነ በፈተና ፣ በምቾትም ሆነ በችግር ጊዜ እሱ ያው ሰው ነው፤ ስብዕና ያው ነበር። ሁሉም የአምላክ መንገዶችና ህግጋት እንደማይለወጡ ሁሉ፣ የአምላክ መልክተኞችም አይለወጡም።”
ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ፣ “እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “በእነዚህ ሁሉ ታላላቅ ሚናዎች ፣ በእነዚህ ሁሉ የሰው ልጅ የእንቅስቃሴ ዘርፎች እሱ ጀግና ነው! ወላጅ አልባነት አለመታደል ቢሆንም ህይወቱ በምድር ላይ የጀመረው በዚህ ነው፡፡ ንግሥና ደግሞ ከፍተኛው የቁሳዊ ሃይል ደረጃ ሲሆን ህይወቱ ያበቃው በዚያ ነው! ከወላጅ አልባ ልጅነት ወደ ተሰደደ ስደተኝነት ፣ ከዚያም ወደ የህዝብ መንፈሳዊና ዓለማዊ መሪነት ፣ የእጣ ፈንታቸው አስተካካይ ሆኖ ፣ በውስጡ ባሉት ፈተናዎችና ማባበያዎች ፣ በመጥፎ ለውጦችና መዋዠቆች ፣ በብርሃኑና በጨለማው ፣ በእድገቱና በውድቀቱ ፣ በፍርሃቱና በውበቱ ፣ የዓለምን እሳት ተቋቁሞ በሰላም ወጥቷል፡፡ ይህ በሁሉም የህይወት ዘርፍ አርአያ እንዲሆን አስችሎታል። ያከናወነው ነገር በአንድ የህይወት መስክ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሁሉንም የሰው ልጅ ሁኔታዎች የሚሸፍን ነው።”
“እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው፡ ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ
- “መካ ከወደቀች በኋላ ከአንድ ሚሊዮን ካሬ ማይል በላይ መሬት በእጁ ስር ነበር። እሱ የአረቦች ጌታ (አለቃ) ሆኖ ሳለ ጫማውንና ልብሱን ይጠግናል ፣ ፍየሉን ያልባል ፣ መሬቱን ይጠርጋል ፣ እሳት ያነዳል እንዲሁም ቤተሰቡን ያገለግል ነበር። በህይወቱ የመጨረሻ ቀናት የኖረባት ‘መዲና’ በወርቅ እና በብር ተሞልታ ነበር። ሆኖም ግን በእነዚያ የሀብት ቀናት እንኳ ምግቡ ተምርና ውሃ ብቻ ነበር፡፡ የአረቦች ንጉስ በቤቱ ምድጃ ውስጥ እሳት ሳይነድ ሳምንታት ያልፉ ነበር።”
ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ፣ “እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “በሞተበት ጊዜ የነበሩት ጥቂት ዲርሃሞች ብቻ ናቸው፡፡ ከእነሱም የተወሰነውን ዕዳ ለመክፈልና ምፅዋት ለመጠየቅ ወደ ቤቱ የመጣን ድሃ ለመርዳት የተቀመጠ ነበር። የመጨረሻ እስትንፋሱን የተነፈሰባት ልብስ ከቀዳዳው ብዛት ብዙ የተጣፈ ነበር። ብርሃን ወደ ዓለም የፈነጠቀባት ቤቱ ፋኖሱ ውስጥ ዘይት ባለመኖሩ ምክኒያት ቤቱ ጨለማ ነበር።”
“እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው፡ ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ
- “ምሽት ላይ የሚበሉት ነገር ማግኘት ባለመቻላቸው ቤተሰቡ በተከታታይ ሌሊቶች ይራቡ ነበር። የሚተኛው ለስላሳ አልጋ ላይ ሳይሆን ምንጣፍ ላይ ነበር፡፡ ይህም አብዛኛውን ሌሊቱን በፀሎት ያሳልፍ ስለነበር የሚተኛው ከረጅም ቀን በኋላ ነበር፡፡ ተግባራቱን ለመፈጸም ሃይል እንዲሰጠው ፈጣሪውን እየለመነ ብዙውን ጊዜ በእንባ ይታጠብ ነበር። በሐዲሶች እንደተዘገበው የለቅሶው ድምፅ ልክ እንደሚፈላ ድስት ድምፅ ከደረቱ ይሰማ ነበር።”
ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ፣ “እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “የመልክተኛው ትህትና ፣ የቃልኪዳኑ ትክክለኛነት እና ታማኝነት ፣ ለጓደኞቹና ለተከታዮቹ ያለው ፍቅርና ታማኝነት ፣ ድፍረቱ ፣ በጌታውና በመልእክቱ ላይ ያለው ፍፁም እምነት፤ መንገዱን የጠረጉለትና ችግሮችን ያሸነፉለት ሰይፍ ሳይሆን እነዚህ ባህርያቶቹ ናቸው። የነብዩን የሕይወት ታሪክ ሁለተኛውን ክፍል አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ ስለዚያ ታላቅ ሕይወት የበለጠ ለማወቅ የሚያስችለኝ ተጨማሪ የማነበው ነገር ባለመኖሩ አዘንኩ።”
ማህተማ ጋንዲ፣ “አዲሲቷ ህንድ” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “የነብዩ ሙሐመድ ስብዕና እውነታ ማወቅ በጣም ከባድ ነው፤ ነገርግን ማቅረብ የምችለው ከውብ ተከታታይ ገጽታዎች የተወሰደ የሕይወቱን ቅንጫቢ ብቻ ነው። ሙሐመድ ነብዩ ፣ የሰራዊት መሪው ሙሐመድ ፣ ንጉሡ ሙሐመድ ፣ ተዋጊው ሙሐመድ ፣ ነጋዴው ሙሐመድ ፣ መካሪው ሙሐመድ ፣ ፈላስፋው ሙሐመድ ፣ የፖለቲካ ሰው ሙሐመድ ፣ ሰባኪው ሙሐመድ ፣ አስተካካዩ ሙሐመድ ፣ የየቲሞች መጠጊያ ሙሐመድ ፣ የባሪያዎች ጠባቂ ሙሐመድ ፣ የሴቶች ነፃ አውጪ ሙሐመድ ፣ ባል የሆነው ሙሐመድ ፣ አስተማሪው ሙሐመድ ፣ ስርዓት አውጪው ሙሐመድ ፣ ዳኛው ሙሐመድ ፣ ካህኑ ሙሐመድ… ወዘተ ናቸው።”
ፕሮፌሰር ራማ ክሪሽና ራዎ፣ “እስልምና እና ዘመናዊው ዘመን” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “ዛሬ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ የገዛውን ሰው ባህርያት ማወቅ ፈለግሁ… በእነዚያ ቀናት እስልምና በህይወት ስርአት ውስጥ የነበረውን ቦታ እንዲይዝ ያስቻለው ሰይፍ ሳይሆን የነብዩ ቀለል ያለ ህይወት እና ፍፁም ትህትና መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አምኛለሁ።”
ማህተማ ጋንዲ፣ “አዲሲቷ ህንድ” በተሰኘ መጽሐፋቸው
- “ሙሐመድ የመልካምነት ፍሬ ነበር፤ ተጽዕኖው ጎልቶ የሚታይና ፈጽሞ የማይረሳ ነበር።”
ዲዋን ሻንድ ሻርማ፣ “የምስራቅ ነብያት”
- “የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሁሌም ፈገግተኞች ፣ ቀለል ያለ ባህሪ ያላቸው ፣ ገር የሆኑ ነበሩ። ጨካኝ ፣ ልበ ደረቅ ፣ ጩኸታም ፣ ብልግና ተናጋሪ ፣ ተሳዳቢም ሆነ አሞጋሽ አልነበሩም። የማይወዱትን ነገር ቸል ብለው ያልፉ ነበር፤ ከእሱም ተስፋ አያስቆርጡም ነበር።”
ሰፊዩረህማን አል-ሙባረክፉሪ፣ “አር-ረሒቅ አል-መኽቱም”
- “እነዚህ የጠቀስናቸው ባህሪያ፤ የፍጹምነታቸው መገለጫዎችና የታላቅ ባህሪያቸው አጭር መስመሮች ብቻ ናቸው። የክብራቸውና የባህሪያቸው እውነተኛው ገጽታ ግን ጥልቀቱ የማይደረስበትና የማይመረመር ጉዳይ ነው። የእሳቸው ባህሪ ቁርአን እስኪሆን ድረስ በጌታው ብርሃን የበራና የፍጹምነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰን ታላቅ ሰው ማንነት ማን ሊያውቅ ይችላል?”
“ጨረቃ በተሰነጠቀች ጊዜ፡ “ሰፊዩረህማን አል-ሙባረክፉሪ
- “በህይወታቸው ውስጥ በተከሰቱት ክስተቶች እንዳየነው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለጋስ ፣ ጀግና ፣ ጠንካራና ታጋሽ ነበሩ። ብልግና ተናጋሪም ሆነ ጸያፍ ቃላትን የሚጠቀሙ አልነበሩም። አንድን ነገር ከጠሉ ፊታቸው ላይ ይታይ ነበር። ማንንም በትኩረት አይመለከቱም ነበር፤ ማንንም በንዴት አይመለከቱም ነበር። አገልጋያቸውን አልገሰጹም፤ በማንም ላይ መጥፎ ቃል ሲናገሩ አልተሰሙም።”
ሰፊዩረህማን አል-ሙባረክፉሪ፣ “ጨረቃ በተሰነጠቀች ጊዜ”
- “የአሏህ መልዕክተኛ ከመሆናቸው በፊትም እንኳ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‘አል-አሚን’ (ታማኙ) በመባል ይታወቁ ነበር። ቃል ኪዳናቸውን ይሞሉ ነበር፤ ድል ሲያደርጉ እንኳ ትሁት ነበሩ። የዝምድና ትስስራቸውን ያከብሩ ነበር፤ የዘመዶቻቸው እና የጓደኞቻቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኙ ነበር።”
“ጨረቃ በተሰነጠቀች ጊዜ”፡ ሰፊዩረህማን አል-ሙባረክፉሪ፣
- “የዝምድና ትስስራቸውን ያከብሩ ነበር፤ የዘመዶቻቸው እና የጓደኞቻቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኙ ነበር። ከድሆችና ከምስኪኖች ጋር ይቀመጡ ነበር፤ ከባሪያዎች የሚደርሳቸውን ግብዣም ይቀበሉ ነበር። የእስላማዊ መንግሥት መሪ ሆነው በስልጣን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱበት ጊዜ እንኳ ትሁት ነበሩ። ውድ ምግቦችን በማቅረብም ሆነ ውድ ልብሶችን በመልበስ ከማንም ጋር ለመወዳደር ሞክረው አያውቁም። ስለሆነም የመልዕክተኛውን ህይወትና ለሰው ልጅ ያላቸውን ጠቀሜታ በትክክል መግለጽ አይቻልም።”
ሰፊዩረህማን አል-ሙባረክፉሪ፣ “ጨረቃ በተሰነጠቀች ጊዜ”
ከአሜሪካ ምሁራን እና የታሪክ ሰዎች ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች
- “ሲጀምሩ አረቢያ ጣዖታትን በሚያመልኩ ነገዶች የተሞላች ጠፍ በረሃ ነበረች፤ ሲሞቱ ግን አንድ ህዝብ ነበረች።”
ዊል ዱራንት፣ “የሥልጣኔ ታሪክ”
- “ታላቅነት በታላቅ ሰው ተጽእኖ የሚለካ ከሆነ እሳቸው በታሪክ ውስጥ ከታላላቆቹ አንዱ ነበሩ። በከባቢ አየር ሙቀትና በበረሃው ድርቀት ምክንያት አረመኔያዊ ፅልመት ውስጥ የተጣለን ህዝብ መንፈሳዊና ሥነ-ምግባራዊ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሃላፊነት ወሰዱ። ይህንንም ዓላማ በታሪክ ውስጥ ማንም ተሐድሶ አራማጅ ያላሳካውን ስኬት አሳክተዋል። እንደ እሳቸው ያልሙትን ያሳካ ሌላ ሰው ማግኘት ብርቅ ነው።”
ዊል ዱራንት፣ “የሥልጣኔ ታሪክ”
- “ሙሐመድ የመንግሥት ርዕሰ ብሔር እንደነበረ ሁሉ የሃይማኖት መሪም ነበረ። ይኸውም ቄሳርና ጳጳስን በአንድነት የያዘ ነበር። ነገርግን ጳጳስነት ይገባኛል ሳይል ጳጳስ የሆነ ፣ የቄሳር ጦር የሌለው ቄሳር ፣ የግል ዘብ (ጠባቂ) ፣ የፖሊስ ሃይል የሌለው እና ቋሚ ገቢ የሌለው ነበር። በመለኮታዊ መብት የገዛ ሰው ካለ፤ እሱ ሙሐመድ ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም አይነት ድጋፍ ሳይኖረው ሁሉም አይነት ስልጣን ነበረው። ለስልጣን መገለጫዎች ግድ አልነበረውም፤ የግል ህይወታቸው ቀለል ያለ እና ከህዝባዊ ህይወታቸው ጋር የተስማማ ነበር።”
ቦስዎርዝ ስሚዝ፣ “ሙሐመድ እና ሙሐመዳውያን”
- “ምናልባት በታሪክ ውስጥ እጅግ ታላቁ መሪ ሙሐመድ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሦስቱንም የመሪነት ባህሪያት ሰብስቦ ይዟል። ሙሴም (ሙሳ) በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይ ነገር አድርጓል።”
ጁልስ ማሰርማን፣ “በታሪክ ውስጥ ታላላቅ መሪዎች እነማን ናቸው?” በሚል ርዕስ በጻፉት መጣጥፍ
- “የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን ከሞተ ከአራት ዓመታት በኋላ በአረብ ሀገር መካ ውስጥ ከሰዎች ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ታላቅ ተጽእኖ ያሳደረው ሰው ተወለደ። የበርካታ ኢምፓየሮች ሃይማኖታዊ መሪ እና የሰው ልጅ አንድ ሦስተኛውን የዕለት ተዕለት ህይወት መምራት ቻለ፡፡ በእርግጥም ‘የአሏህ መልዕክተኛ’ የሚለውን ማዕረግ ይገባዋል።”
ዊልያም ድሬፐር፣ “የአውሮፓ የአዕምሮ እድገት ታሪክ”
- “እሱ ከአብርሃም ዘር ነው፤ ያለ ጥርጥር ጌታ ሆን ብሎ ያስነሳው ጣዖት አምልኮን እንዲቃወም ነው።”
ጆርጅ ስሚዝ፣ “ዴይሊ ኒውስ፣ ጥቅምት 10, 1855”
- “ሙሐመድ የሚያስተምረውን እውነት የምትቀበል ቤተክርስቲያን አባል በመሆናችን አመስጋኝ ነኝ ለማለት እወዳለሁ።”
ጄምስ ቶሮንቶ፣ “Ensign” በተባለው መጽሔት ላይ “የዘመናችን ቅዱስ ስለ ሙሐመድ ያለው ግንዛቤ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጣጥፍ
- “ወታደራዊ ድሎቹ ለግል ዓላማ ቢሆን ኖሮ ሰው እንደሚያደርገው ኩራት ወይም ትዕቢት በወጠረው ነበር። የክብር ማማ ላይ በነበረበት ጊዜ እንኳ በችግር ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ባህሪውና አለባበሱ ቀለል ያለ ነበር። ከንግሥና ተጽእኖ የራቀ ሲሆን ወደ አንድ ክፍል በሚገባ ጊዜ የሚያደርጉለትን ልዩ የሆነ አቀባበል ይጠላ ነበር። ዓላማው የእምነት የበላይነት ነው እንጅ ዓለምን መግዛት ቢሆን ኖሮ በእጁ እየጨመረ የመጣውን ዓለማዊ ስልጣን ይጠቀምበት ነበር፡፡ እንዲሁም በቤተሰቡ ውስጥ እንዲቀጥል የማድረግ እርምጃ ይወስድ ነበር።”
ዋሽንግተን ኢርቪንግ፣ “ሙሐመድ እና ተተኪዎቹ” በተሰኘ መጽሐፉ
- በግል ግንኙነቶቹ ፍትሃዊ ነበር። ጓደኞቹን እና እንግዳዎቹን ፣ ሀብታሞችን እና ድሆችን ፣ ጠንካሮችን እና ደካሞችን በፍትህ ያስተናግድ ነበር። ከሕዝቡ ጋር የነበረው ወዳጅነት እና ለቅሬታቸው የሚሰጠው ትኩረት በጣም ተወዳጅ አድርጎት ነበር።
“ሙሐመድ እና ተተኪዎቹ” በተሰኘ መጽሐፉ፡ ዋሽንግተን ኢርቪንግ
- አመጋገቡ ልከኛና ሚዛናዊ ፣ ፆምን አዘውትሮ የሚጠብቅ ፣ የቅንጦት ልብሶችን የማይወድ ነበር፡፡ በታላቅ ነገሮችም አይመካም አይኩራራም ነበር። የልብሱ ልክነት ተፈጥሯዊ እንጅ ሆን ተብሎ የተሰራ አልነበረም፤ ይህም ከከንቱ ነገሮች የላቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ዋሽንግተን ኢርቪንግ በ”ሙሐመድ እና ተተኪዎቹ” ከተሰኘው መጽሐፉ
- ሙሐመድን በአለም ላይ ትልቁን ተፅዕኖ የፈጠሩ ሰዎች ዝርዝር አናት ላይ ማስቀመጤ ብዙ አንባቢዎችን ሊያስደንቅ ወይም ሌሎችን ሊያጠራጥር ይችላል። ሆኖም በእኔ እምነት ከታሪክ ማህደር ውስጥ በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ደረጃ እጅግ የላቀ ስኬት ያስመዘገበው እሱ ብቻ ነው።
ማይክል ሀርት በ”100፡ በታሪክ ውስጥ እጅግ ተፅዕኖ የፈጠሩ ሰዎች ዝርዝር” ከሚለው መጽሐፉ
- ሙሐመድ በሁሉም ጉዳዮች እጅግ ተግባራዊ ነበር። ተወዳጅ ልጁ ኢብራሂም ሲሞት የፀሐይ ግርዶሽ ተከሰተ። ወዲያውኑ ይህ የአሏህ መጽናኛ ነው የሚል ወሬ ተሰራጨ። ይሁንና ሙሐመድ ተነስቶ የፀሐይ ግርዶሽ ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑን አወጀ። እንዲህ አይነት ነገሮች የሰዎች መሞት ወይም መወለድ ምክንያት መሆን የለባቸውም በማለት ገልጿል።
ጄምስ ሚሽነር በ”ያልተረዳው እስልምና” ከሚለው መጣጥፉ (በ”ሪደርስ ዳይጀስት” መጽሔት፣ ግንቦት 1955)
- ከእሱ በፊት እንደነበሩት ታላላቅ ነብያት ሁሉ ሙሐመድ የአምላክን ቃል ለማስተላለፍ በራሱ ላይ በቂ እምነት አልነበረውም። ነገርግን መልአኩ “አንብብ” አለው። እንደሚታወቀው ሙሐመድ ማንበብም ሆነ መፃፍ አይችልም ነበር። ይሁንና ወዲያውኑ የአለምን ትልቅ ክፍል የቀየረውን “እሱ አንድ አምላክ ነው።” የሚለውን ራዕይ መናገር ጀመረ፡፡
ጄምስ ሚሽነር በ”ያልተረዳው እስልምና” ከሚለው መጣጥፉ (በ”ሪደርስ ዳይጀስት” መጽሔት፣ ግንቦት 1955)
ከብሪታንያ ምሁራን ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች
- ባሉት ጥቂት መንገዶች እና ባደረገው ስራ ዘላቂነት እና ርቀት ላይ ተመርኩዘን ብንፈርድ ኖሮ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከመካ ነብይ የበለጠ ብሩህ እና የሚያምር ስም የለም። በታወቁት የሰው ልጆች መለኪያዎች ብንመዝነው የትኛው ፍጡር ከእሱ ልቅና እና ክብር ጋር ሊወዳደር ይችላል?
ጆን ስቶባርት በ”እስልምና እና መስራቹ” ከተሰኘው መጽሐፉ
- በምድር ላይ አምላክን ያገኘ ሰው ካለ ፣ ህይወቱን በንጹህ እና ቅዱስ በሆነ ቅንነት ለአምላክ የሰጠ ሰው ካለ፤ ያ ሰው ቅዱስ የአረብያ ነብይ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
አርተር ግሊን ሊዮናርድ በ”እስልምና እና የሥነ-ምግባርና የመንፈሳዊ እሴቶቹ”
- የሙሐመድ ጥበብ የነገሥታትን ታላቅነት እንዲንቅ አደረገው። የአሏህ መልዕክተኛ ቤተሰቦቹን ለማገዝ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከመስራት ወደኋላ አላለም፤ እሳት ያቀጣጥላል ፣ ቤቱን ይጠርጋል ፣ በግ ያልባል ፣ ጫማውን ይጠግናል ፣ ልብሱንም በራሱ እጅ ይሰፋል። ነፍስን በማሰቃየት እና ከፍ ያለ ቦታን በመፈለግ የሚደረገውን የድኩማን መንገድ አይደግፍም ነበር። ነገርግን ሁልጊዜ የአረቦች ልማድ በሆነው ያለ ምንም ችግር ወይም ኩራት ቀለል በለ ምግብ ይብቃቃ ነበር።
ኤድዋርድ ጊቦን በ”የሮማ ግዛት ውድቀት”
- በሙሐመድ ህይወት ውስጥ ያለው ትልቁ ስኬት በንፁህ ሥነ-ምግባራዊ ሃይል ተፅዕኖ የተደረገበት ነበር። አስደናቂው ነገር የእስልምና መስፋፋት ሳይሆን ቀጣይነቱ ነው። በመካ እና በመዲና የተቀረፀው ንፁህና ፍፁም አሻራ ከ12 ምዕተ-ዓመታት በኋላም እንኳ በአዲስ መልክ ወደ እስልምና በሚመጡ ህንዶች ፣ አፍሪካውያን እና ቱርኮች ነፍስ ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ኤድዋርድ ጊቦን እና ስምዖን ኦክሌይ በ”የሳራሴኒክ ግዛት ታሪክ”
- ሙሐመድ ያደረገው ጉዞ በውስጡ ያለውን የጥንካሬው እና የህይወቱ ድንቅ ምሳሌ ነው። በፈጣሪ እና በሩቅ ዓለም ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው። በህይወት ዘመኑ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሁሉም ተከታዮቹ ላይ ተጽዕኖ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ሆኖ ይቆያል፡፡ ይህ ጥረት ታላቅ እምነትን ለማስፋፋት የነበረ ሲሆን ታላቅ ሰው ብቻ ሊያደርገው የሚችል ነው።
ጆንሮድዌል ከቁርአን ትርጉሙ መግቢያ ላይ
- በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመዲና መንፈሳዊ እና አለማዊ ገዥ ሆነ፡፡ ዓለምን በሚያናውጥበት ዘንግ ላይ እጁን አኖረ።
ጆን ኦስቲን በ”ሙሐመድ የአሏህ ነቢይ”
- የፈጠረው አንቀሳቃሽ ሃይል ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ፣ ራሳቸውን የቻሉ ስርወ መንግስታት ፣ ውብ ከተሞች ፣ የቅንጦት ቤተመንግስቶች ፣ የአምልኮ ቤቶች እና ሰፊ ከተሞችን አስገኘ። ከዚህም በላይ ቃላቶቹ በዘመናቱ የመጡ የትውልዶችን እምነት አስተዳድረዋል፤ ይህም ለመጪው አለም የህይወታቸው መመሪያ ሆኖ ያገለግላል። በሺዎች በሚቆጠሩ የአምልኮ ቤቶች ውስጥ የአሏህ ነብይ እና የመልዕክተኞች መጨረሻ አድርገው የሚቆጥሩት ሲሆን በእሱ ላይ የሚያደርጉት ውዳሴያቸው ይሰማል።
ጆንስቶባርት በ”እስልምና እና መስራቹ”
- ሙሐመድ በብልሃቱ እና በእስልምና መንፈስ አማካኝነት በአረቦች ውስጥ በፈጠረው የላቀ መንፈስ የአረቦችን ክብር ከፍ አደረገ። ከስንፍና እና ከጎሳዊው ትምኪት አላቀቃቸው፡፡ ወደ ብሔራዊ አንድነት እና ኢምፓየር ወደ መመስረት ደረጃ ከፍ አደረጋቸው። የሙሐመድ የእምነት ልቅና ፣ ቀላልነት ፣ ልክንነት ፣ ንጽህና እና ሙሐመድ በራሱ ላይ ያስቀመጠው ታማኝነት በሥነ-ምግባራቸው እና በአስተሳሰብ አወቃቀራቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
አርተር ግሊን ሊዮናርድ በ”እስልምና እና የሥነ-ምግባርና የመንፈሳዊ እሴቶቹ”
- በቁም ነገርም ሆነ በሌላ የእሱ የዕለት ተዕለት ባህሪ ዛሬ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚከተሉት ህግ ሆኗል። በየትኛውም የሰው ዘር ክፍል ውስጥ እንደ ሙሉ ሰው ተደርጎ የተወሰደ እና በዚህ ደረጃ እሱን ለመመሰል የተመከረ ሰው የለም። የክርስትና መስራች ባህሪ የተከታዮቹን የዕለት ተዕለት ኑሮ አያስተዳድርም። ከዚህ በተጨማሪ የየትኛውም የሃይማኖት መስራች የሙስሊሞች መልዕክተኛ የነበራቸው ልዩ ልቅና አልነበራቸውም።
ዴቪድ ጆርጅ ሆጋርዝ በ”የአረብ ባሕረ ገብ መሬት”
- የታላቁን የአረብ ነብይ ህይወት እና ባህሪ ያጠና ማንኛውም ሰው፤ ይህ ነብይ እንዴት እንደኖረ እና ሰዎችን እንዴት እንዳስተማረ የሚያውቅ ሰው ከአሏህ ታላላቅ መልዕክተኞች አንዱን ማክበርና ማድነቅ አይችልም። ምንም እንኳን የምነግራችሁ ብዙ ሰዎች የሚያውቋቸው ነገሮች ሊሆኑ ቢችሉም፤ እነዚህን ነገሮች በድጋሚ ባነበብኩ ቁጥር ለዚህ ታላቅ የአረብ መምህር አዲስ አድናቆት እና ክብር ይሰማኛል።
አኒ ቤዛንት በ”የሙሐመድ ህይወት እና ትምህርቶች”
- ሙሐመድ ሁልጊዜ ገዳይ በሆነ አደጋ ውስጥ ነበር፡፡ እናም የመዳኑ ነገር ከተአምር ጋር ቅርብ ነበር፡፡ ነገርግን ስኬታማ ሆነ። በህይወቱ መጨረሻ ላይ አካባቢውን ሲያምስ የኖረውን የጎሳ ሁከት ሥር ላይ መጥረቢያ አስቀምጧል፡፡ እናም ከዚያ በኋላ ከአረማዊነት ምንም ፍርሃት አልነበረም። አረቦች በታሪካቸው አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጁ ነበሩ።
ካረን አርምስትሮንግ በ”ሙሐመድ፡ የነብዩ የህይወት ታሪክ”
ከጀርመን ምሁራን ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች
- ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ በሰው ልጅ ሃይማኖታዊ ፣ ሥነ-ምግባራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ላይ እንደ አረቡ ሙሐመድ ያለ ወሰን የለሽ ተጽዕኖ የፈጠረ የሰው ልጅ አልመጣም።
አውሮፓዊው የታሪክ ምሁር ዮሃን ዶለንገር
ከስኮትላንድ ምሁራን የተሰጡ ምስክርነቶች
- እውነተኛ እና ታማኝ ሰው ነበር፡፡ በድርጊቱ ፣ በቃሉ እና በአስተሳሰቡ እውነተኛ ነበር።
ቶማስ ካርላይል “ጀግኖች እና የጀግኖች አምልኮ” በተሰኘው መጽሐፉ
- በዚህ ሰው፤ በሙሐመድ ላይ የተሰበሰቡ ውሸቶች ሁሉ ምንም ሳይሆኑ የእኛው ነውሮች ናቸው።
ቶማስ ካርላይል “ጀግኖች እና የጀግኖች አምልኮ” በተሰኘው መጽሐፉ
ከተለያዩ መጽሐፍት የተወሰዱ
- በልማዶቹ ቀላል ነበር። ህመምተኛን ይጎበኝ ነበር ፣ በመንገዱ ላይ ያለን ማንኛውንም የሟች አስክሬን ይከተል ነበር። የአንድ ባሪያን የእራት ግብዣ ተቀብሏል ፣ ልብሱን ይጥፍ ነበር ፣ በጉን አጣብቷል ፣ ራሱን ያገለግል ነበር። አንድ ሰው እጁን ሲጨብጠው፤ ሰውየው እጁን እስኪለቅ ድረስ እጁን አይለቅም ነበር፤ ፊቱንም ከእሱ ላይ አያዞርም ነበር።
“የስኬት ቁልፎች” ከተሰኘው መጽሐፍ
- ትረካዎች እንደሚሉት ከሰዎች ሁሉ እጅግ ለጋስ እና እውነተኛ ነበር፤ ከሰዎች ሁሉ እጅግ ታማኝ እና በንግግሩም እጅግ ርህሩህ እና ደግ ነበር።
“የሰኬት ቁልፍ” ከተሰኘው መጽሐፍ
- የሚያዩት በድንገት በክብር ይሞላሉ፤ ወደ እሱ የቀረበ ሰው ሁሉ ይወደው ነበር። እሱን የገለፁት ሰዎች እንዲህ ይላሉ፡- “ከእሱ በፊትም ሆነ በኋላ እንደ እሱ ያለ አላየንም።”
“የስኬት ቁልፎች” ከተሰኘው መጽሐፍ
ማጠቃለያ
በዚህ ጽሑፍ እንዳየነው ከፈረንሳይ እስከ አሜሪካ ፣ ከህንድ እስከ ብሪታንያ ያሉ በርካታ የዓለማችን ታላላቅ ሰዎች ስለ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያላቸውን አድናቆትና ክብር ገልጸዋል።
እነዚህ ገለልተኛና ከእስልምና ውጪ ያሉ ምሁራን የሰጧቸው ምስክርነቶች ፣ የእርሳቸውን ሁለንተናዊ ስብዕና ፣ ፍትሐዊ አመራር ፣ የላቀ ባህሪና ለሰው ልጅ ያስተላለፉትን ዘመን ተሻጋሪ መልእክት ያረጋግጣሉ።
የእነዚህ ምሁራን እይታዎች ፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የታሪክ አቅጣጫን የቀየሩ ታላቅ መሪ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ።
እርስዎስ ስለ ነብዩ ሙሐመድ የተሰጡ ምስክርነቶች ውስጥ በጣም የገረመዎትና ልብዎን የነካው የትኛው ነው?
ሀሳብዎን ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ ያካፍሉን።



Share