የአላህ አንድነት፡ የመፈጠራችን መሰረታዊ ዓላማ

Author picture
ፍጥረተ ዓለሙ የተገኘበትን ታላቅ ሚስጥር እና የነብያት ሁሉ የጋራ ጥሪ የሆነውን የአላህ አንድነት ምንነት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያግኙ።

መግቢያ

በዙሪያችን ያለውን አስደናቂ ዓለም፣ በትክክለኛ ስርአት የምትንቀሳቀሰውን ሰማይና በውበት የተዘረጋችውን ምድር ስንመለከት “የዚህ ሁሉ ነገር እውነተኛ ዓላማ ምንድን ነው?” ብለን ጠይቀን እናውቃለን? እስልምና ለዚህ ጥልቅ ጥያቄ የማያዳግም መልስ ይሰጣል። የፍጥረት ሁሉ ዋና ግብ የፈጣሪን፣ የአላህ አንድነት (ተውሂድ) ማወቅና እሱን ብቻ መገዛት ነው።

ይህ ጽሑፍ ይህ ታላቅ እውነት እንዴት የፍጥረታት ሁሉ መሰረት ፣ የሁሉም ነብያት የጋራ ጥሪ እና የሕይወታችን ማዕከል እንደሆነ ከቁርአናዊ አንቀጾች ጋር በማስረጃ ያስረዳል።

ይህንን በመረዳት የሕይወትን ትርጉም በትክክል መገንዘብ ይቻላል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ነሕል፡ 36)

“በእርግጥ በየሕዝቡ ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ከጣዖታትም ራቁ» በማለት መልዕክተኛን ልከናል፡፡”

የፍጥረት ዓላማ፡ የአላህን አንድነት ማወቅ

አሏህ ይህንን አለም (ከውን) በአስደናቂ ውበት ፣ በትክክለኛ ስርዓት እና በታላቅ ጥበብ የፈጠረው ለታላቅ ግብ እና አላማ ነው።

ይህ አላማ የአሏህን አንድነት (በአምልኮቱ) (ተውሂድ) እንዲሁም ታላቅነቱን ፣ ሀይሉንና ችሎታውን ማወቅ ነው።

አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንከቡት፡ 20)

“ሙሐመድ ሆይ! በምድር ላይ ሂዱ፤ ፍጥረትን እንዴት እንደጀመረ ተመልከቱ፡፡ ከዚያም አሏህ የመጨረሻይቱን ህይወት ያስገኛል፡፡ በእርግጥ አሏህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና በላቸው፡፡”

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ቃፍ፡ 6-7)

“ከበላያቸው ወደ ሆነችው ሰማይ እንዴት እንደሠራናት እና እንዳጌጥናት ፣ ለእርሷም ምንም ቀዳዳዎች እንደሌሏት አይመለከቱምን? ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ በእርሷም ውስጥ ከሚያስደስት አይነት ሁሉ አበቀልን፡፡”

“አይመለከቱምን?” የሚለውን ቃል አስተውሉ።

ይህ ጥያቄ አይን እያላቸው የማያዩ ፣ ልብ እያላቸው የማያስተውሉትን ሰዎች ለማውገዝ የቀረበ ነው።

ይህ ሁሉ የአላህ አንድነት አእና ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት ሆኖ ሳለ በዚህ ታላቅ አለም ውስጥ ያለውን ማራኪ ውበትና አስደናቂ ጥበብ ማየት ግን አይችሉም፡፡

በዚህም ምክንያት ይህንን እውነታ የሚረጋገጡ የአላህ አንቀጾች በቁርአን ውስጥ ብዙ ናቸው።

ከዚህም በላይ ሁሉም መልዕክተኞች እና ነብያት ከመጀመሪያው አደም (ዐ.ሰ) አንስቶ እስከ መጨረሻው ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ድረስ በአንድ ጉዳይ ላይ ተስማምተዋል፡፡

የነብያት ሁሉ ጥሪ፡ ተውሒድ

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንቢያ፡ 25)

“ከአንተ በፊት ‘ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ’ በማለት ወደ እርሱ ራዕይ ያወረድንለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አላክንም፡፡”

የነብያት ሁሉ ጥሪ በዚህ ላይ የተመሰረተ ሲሆን መንገዳቸውም የተስማማ ነበር።

ሁሉም ነብያት የተላኩት አሏህን በብቸኝነት ያለ አጋር ማምለክን በሚያዘው ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነው እና እውነተኛ በሆነው እስልምና ነው።

ጥሪያቸው ወደ አሏህ አንድነት (ተውሒድ) እና ጠንካራ ገመዱን አጥብቆ ወደመያዝ ነው።

የእውነትና የሐሰት ፍጥጫ፡ የነብዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ምሳሌ

የአላህ ነብያትና የእሱን ራዕይ በአደራ የተቀበሉት በየዘመናቱ ሁሉ ይህንን እውነታ የሚያስተባብሉ ገጥመዋቸዋል።

እንዲያውም አንዳንዶቹ “እኔ የአለማት ጌታ ነኝ!” እስከማለት ደርሰው ነበር።

አላህ ወዳጆቹን (አውሊያዎቹን) ውሸታቸውን በሚያደቁ እና ቅጥፈታቸውን በሚያፈራርሱ በማያዳግሙ ማስረጃዎች እና የበላይ በሆኑ መረጃዎች አግዟቸዋል።

ለዚህም ምሳሌ ወሰን ያለፈው እና የተንጠባረረው ኒምሩድን ያነጋገረው ነብዩሏህ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ነው።

አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራህ፡ 258)

“ወደዚያ አሏህ ንግሥናን ስለሰጠው በጌታው ነገር ኢብራሂምን ወደ ተከራከረው ሰው አላየህምን? ኢብራሂም «ጌታዬ ያ ህያው የሚያደርግና የሚገድል ነው» ባለጊዜ (ኒምሩድ) «እኔ ህያው አደርጋለሁ እገድላለሁም» አለ፡፡ ኢብራሂም «አላህ ፀሐይን ከምሥራቅ በኩል ያመጣል፤ አንተም ከምዕራቅ በኩል አምጣት» አለው፡፡ ያ የካደ ሰው ዋለለ (መልስ አጣ)፡፡ አላህም በዳይ ሕዝቦችን አይመራም፡፡”

ይህ የነብያት ሁሉ ተግባር ነበር፡ “በእርግጥ በየሕዝቡ ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ከጣዖታትም ራቁ» በማለት መልክተኛ ልከናል፡፡”

የ ላኢላሀ ኢለሏህ ሚዛን

ፍጥረተ አለሙ ሁሉ ሰማያቱ ፣ ምድር ፣ ከዋክብቱ ፣ ፈለኮቹ ፣ ተራሮቹ ፣ ዛፎቹና በውስጣቸው ያለው ነገር ሁሉ የቆመው “ላኢላሀ ኢለሏህ” (ከአላህ በቀር በሐቅ ሊያመልኩት የሚገባ አምላክ የለም) በሚለው ቃል ነው።

ፍጥረታት ሁሉ የተፈጠሩት ለዚች ቃል ሲባል ነው። ሚዛኖችም የሚቆሙት ፣ የመዝገብ መጽሐፍት የሚቀመጡት ፣ የጀነትና የእሳት ገበያ የሚቋቋመው ለሷ ነው።

መለኮታዊ መጽሐፍት የወረዱትና መልክተኞች የተላኩት ለዚች ቃል ሲባል ነው።

ሰዎችም አማኝና ከሀዲ ተብለው የተከፈሉት በርሷ ምክንያት ነው። ስለሷና ስለመብቶቿ ጥያቄና ሂሳብ ይኖራል።

ምንዳና ቅጣትም በርሷ ላይ ይወሰናል። እሷ የእስልምና ቃልና የሰላም ሀገር (የጀነት) መክፈቻ ቁልፍ ናት።

ማጠቃለያ

በማጠቃለል ፣ የሰማያትና የምድር መኖር ፣ የነብያት ሁሉ መላክና የመለኮታዊ መጽሐፍት መውረድ ዋናው ዓላማ የአላህ አንድነት እንዲረጋገጥ ነው።

“ላኢላሀ ኢለሏህ” የምትለዋ ቃል የሕይወታችን መሰረት ፣ የመዳናችን ቁልፍና የፍጥረት ሁሉ ማዕከላዊ እውነት ናት።

ይህንን ጥልቅ ትርጉም መረዳት ለጌታችን ያለንን ፍቅርና መገዛት እንድናጠነክር ይረዳናል።

በዚህ ርዕስ ላይ የእርስዎ አስተያየት ወይም ተጨማሪ ሀሳብ ምንድን ነው? ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ያጋሩን።

Related posts

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ኢስላም ንፅህናን የእምነቱ ግማሽ አካል ያደረገ ብቸኛ መለኮታዊ ሃይማኖት ነው። ሲዋክ ማለት ጥርስንና አፍን በእንጨት መፋቂያና መሰል ነገራት ከመጥፎ ጠረንና ቅሪቶች ማጽዳት ማለት ነው፡፡

Read More »
ሱጁድ

ሱጁድ

ሱጁድ ማለት በሶላት ውስጥ የመስገጃ ቦታ ላይ ግንባርን የመድፋት ተግባር ነው። ይህ የሚፈፀመው ግንባርን እና አፍንጫን ወለሉ ላይ በማስነካት ፣ መዳፎችን ወለሉ ላይ በማሳረፍ ፣

Read More »
ኢእቲካፍ

ኢእቲካፍ

ኢእቲካፍ ማለት ወደ አሏህ የበለጠ ለመቅረብ በማሰብ የረመዷን የመጨረሻ አስር ቀናትን መስጅድ ውስጥ ተቀምጦ ማሳለፍ ነው። ለይለቱል ቀድር (የድንጋጌው/የውሳኔው ሌሊት) በዚህ ጊዜ ውስጥ ይገኛል። ቅዱስ

Read More »

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share