ላ ኢላሀ ኢለሏህ፡ የሕይወት ትርጉም እና የደህንነት ቁልፍ

Author picture
የፍጥረታት ሁሉ ምስጢር፣ የደስታ ምንጭና የጀነት መክፈቻ የሆነችውን "ላ ኢላሀ ኢለሏህ" የተሰኘችውን ታላቅ ቃል ትርጉም በጥልቀት ይረዱ።

መግቢያ

በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ሊናገራት ከሚችላቸው ቃላቶች ሁሉ የላቀችውና እጅግ ወሳኟ ቃል የትኛዋ ናት? መልሱ ግልጽ ነው፡ ላ ኢላሀ ኢለሏህ (ከአላህ በስተቀር በሐቅ የሚመለክ አምላክ የለም)።

ይህች ቃል የከንፈር እንቅስቃሴ ብቻ ሳትሆን የፍጥረታት ሁሉ መገኛ ምስጢር፣ የሕይወት ትርጉም እና የዘላለም ድነት ቁልፍ ናት።

አላህ ሰውንና አጋንንትን የፈጠረው፣ መጽሐፍትን ያወረደው እንዲሁም ነብያትን የላከው ይህችን ቃል እውን ለማድረግ ነው። ይህ ጽሑፍ የዚህችን ታላቅ ቃል ጥልቅ ትርጉም፣ የተውሒድን ምንነት፣ እንዲሁም በአንድ አማኝ ሕይወት ውስጥ ያላትን ወሳኝ ሚና ከቁርኣንና ከሐዲስ ማስረጃዎች ጋር በማቅረብ ይዳስሳል።

የፍጥረት ሁሉ ምስጢር፡ ላ ኢላሀ ኢለሏህ

‹‹አጋንትንም ሆነ የሰው ልጆችን አልፈጠርኳቸውም እኔን ሊገዙኝ ቢሆን እንጅ።››

ላ ኢላሀ ኢለሏህ (ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም) ሚለው ታላቅ ቃል አሏህ ፍጥረታቱን የፈጠረበት ምስጢር ነው።

አሏህ መጽሐፍትን ያወረደውና ነብያቱን እና መልእክተኞቹን የላከው ለዚህ ቃል ሲል ነው።

ጅብሪል (ዐ.ሰ) የአላህን ወህይ ለነብያትና ለመልእክተኞች ይዞ መውረዱ ለዚሁ ቃል ሲባል ነው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ነሕል 16:2)

‹‹ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላዕክትን ከራዕይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል (ከሐዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ፍሩኝ ማለትን (አስታውቁ በማለት ያወርዳል)፡፡››

አንዳንድ ቀደምት ምሁራን እንዲህ ብለዋል፦

“አላህ ለባሪያዎቹ ‘ላ ኢላሀ ኢለሏህ’ የሚለውን ከማወቃቸው የበለጠ ታላቅ ፀጋ አልሰጠም።”

እሷ የተውሒድ (አሏህን አንድ የማድረግ) ቃል ፣ የኢኽላስ ምስክርነት እና ከእሳት የመዳኛ ቃል ነች።

የተውሒድ ትርጉም እና የአምልኮ መሰረት

አሏህን በዚህ ቃል አንድ ማድረግ ከሁሉም የበለጠ ሲሆን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ግዴታ ነው። “የመጨረሻ ንግግሩ ‘ላ ኢላሀ ኢለሏህ’ የሆነ ሰው ጀነት ይገባል።“

ለዚህም ነው የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሙአዝን ወደ የመን በላኩት ጊዜ እንዲህ ያሉት፡

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

“እናንተ ከመጽሐፉ ሰዎች ወደሆኑ ህዝቦች ትሄዳላችሁ። መጀመሪያ የምትጠሯቸው ‘ላ ኢላሀ ኢለሏህ’ የሚለው ምስክርነት ይሁን። በሌላ ዘገባ ደግሞ ‘አሏህን አንድ እንዲያደርጉ’ ተብሏል።”

የተውሒድ ትርጉም ምንድን ነው?

የአሏህ አንድነት ማለት በሁሉም ጉዳዮችህ ከአሏህ የምትፈልግ መሆንህን ፣ ለሁሉም ፍላጎቶችህ በእሱ ጥገኛ መሆንህን እና ምንም ቢሆን ከጌታህ ወጭ ምንም ማድረግ እንደማትችል ማወቅ ነው።

አላህን አንድ ማድረግ ማለት በአምላክነቱ ፣ በጌትነቱ ፣ በስሞቹና በባህሪያቱ አንድ ማድረግ ነው።

እሱ እውነተኛው አምላክ ሲሆን ብቻውን ያለ አጋር የሚመለክ ነው። የአምልኮ ተግባራት ሁሉ የእሱ መብት ናቸው።

ስለሆነም ሶላትህ ፣ ፆምህ ፣ ሐጅህ ፣ ፍርሃትህ ፣ ተስፋህ እና መውደድህ ለእሱ ብቻ አድርግ።

ከሁሉ የከፋው ወንጀል፡ ሽርክ

ማንኛውንም የአምልኮ አይነት ከአሏህ ውጪ ለሌላ አካል የሰጠ ሰው በአሏህ ላይ አጋርቷል።

አሏህ ከሚያጋሩት የተብቃቃ ነው፡፡ ሙሽሪኮችንም አይወድም። አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈው የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ሙስሊም ዘግበውታል)

“አሏህ እንዲህ አለ ‘እኔ ከሁሉም አጋሪዎች ከሚጋሩት የፀዳሁ (የተብቃቃሁ) ነኝ። አንድ ሰው በእኔ ላይ የማጋራት ስራ ቢሰራ እሱንም ተጋሪውንም እተወዋለሁ።'”

አሏህ ምስጉ እና ተብቃቂ ነው፡፡ ከባሪያዎቹ ታዛዥነትና ዱአዎች ምንም ፍላጎት የለውም። ጥቅማቸውም ወደ እሱ አይመለስም።

የአጥፊው ጥፋት አይጎዳውም ፣ የትጉሁም ታዛዥነት አይጠቅመውም። ይልቁንም አምላኪዎቹ በታዛዥነታቸው የሚጠቀሙና በጥፋታቸው የሚጎዱ እነሱ ናቸው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ፋጢር 35:15-17)

‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ሁልጊዜ ወደ አሏህ ከጃዮች ናችሁ፡፡ አሏህም እሱ ተብቃቂ ምስጉኑ ነው፡፡ ቢሻ ያስወግዳችኋል፡፡ አዲስንም ፍጡር ያመጣል፡፡ ይህ በአሏህ ላይ አስቸጋሪ አይደለም፡፡››

የተውሒድ በረከቶች፡ የህይወት ሰላምና የወንጀል ምህረት

አላህን በብቸኝነት ማምለክ በዱንያም በአኼራም ታላላቅ በረከቶችን ያስገኛል።

በዚህች አለም፡ አሏህን አንድ ማድረግና እሱን ብቻ ማምለክ ደረትን ያስፋፋል ፣ ልብን ያበራል ፣ ነፍስን ያስደስታል እንዲሁም በነፍስ ውስጥ እረፍትና መረጋጋትን ያመጣል።

እሱ የደስታ መሰረትና መነሻ ሲሆን አሏህ ዘንድ ስራዎች ተቀባይነት የሚያገኙበት መሰረትም ነው።

በመጨረሻው አለም፡ ተውሂድን አጥብቆ የያዘ ሰው አሏህ ስራውን ይቀበለዋል፤ ወንጀሉንም ይምረዋል። ከተውሒድ ያፈነገጠ ሰው አሏህ ስራውን አይቀበለውም።

ከአነስ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ቲርሚዚይ ዘግበውታል)

“አሏህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ፡ ‘የአደም ልጅ ሆይ! ምድርን የሚሞላ ወንጀል ይዛችሁ በእኔ ላይ ሳታጋሩ ወደ እኔ ብትመጡ ምድርን ሚሞላ ምህረት ይዜ ወደ እናንተ እመጣለሁ።'”

ማጠቃለያ

ሲጠቃለል “ላ ኢላሀ ኢለሏህ” የእስልምና ልብ ናት። የፍጥረት ዓላማ፣ የአምልኮ መሰረት፣ የስራዎች ተቀባይነት መለኪያና የወንጀል ምህረት ቁልፍ ናት።

ይህችን ቃል በምላሳችን ከመመስከር ባሻገር ትርጉሟን በጥልቀት በመረዳትና የህይወታችን መመሪያ በማድረግ እውነተኛ ሰላምና የዘላለም ስኬትን እናገኛለን።

ይህችን ታላቅ ቃል በሕይወታችን ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን ብለው ያስባሉ? ሀሳብዎን ከታች ያካፍሉን።

Related posts

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ኢስላም ንፅህናን የእምነቱ ግማሽ አካል ያደረገ ብቸኛ መለኮታዊ ሃይማኖት ነው። ሲዋክ ማለት ጥርስንና አፍን በእንጨት መፋቂያና መሰል ነገራት ከመጥፎ ጠረንና ቅሪቶች ማጽዳት ማለት ነው፡፡

Read More »
ሱጁድ

ሱጁድ

ሱጁድ ማለት በሶላት ውስጥ የመስገጃ ቦታ ላይ ግንባርን የመድፋት ተግባር ነው። ይህ የሚፈፀመው ግንባርን እና አፍንጫን ወለሉ ላይ በማስነካት ፣ መዳፎችን ወለሉ ላይ በማሳረፍ ፣

Read More »
ኢእቲካፍ

ኢእቲካፍ

ኢእቲካፍ ማለት ወደ አሏህ የበለጠ ለመቅረብ በማሰብ የረመዷን የመጨረሻ አስር ቀናትን መስጅድ ውስጥ ተቀምጦ ማሳለፍ ነው። ለይለቱል ቀድር (የድንጋጌው/የውሳኔው ሌሊት) በዚህ ጊዜ ውስጥ ይገኛል። ቅዱስ

Read More »

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share