Grave p1

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። ምስጋና ለአለማት ጌታ ለሆነው ለአሏህ ይገባው። አሏህ የመራውን ማንም አያጠምም፤ አሏህ ያጠመመውንም ማንም አይመራም።

የአሏህ ሰላምና እዝነት በረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ላይ ፣ በቤተሰቦቻቸው ፣ በሶሃቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ እስከ የውመልቂያማ ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።

=<({አል-ቁርአን 67:2})>=

{2} ያ የትኛችሁ ስራው ይበልጥ ያማረ መሆኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ህይወትን የፈጠረ ነው። እርሱ አሸናፊ መሐሪው ነው።


ሞት ማለት ነፍሳችን ከስጋችን የሚለያይበት ስርዓት ሲሆን ከዱንያ ወደ አሂራ የሚደረግ ጉዞ ነው። ሆኖም ሞት ማንኛውም ሰው የሚያጋጥመው ከባድ እና አስፈሪ እውነታ ሲሆን አንዳችነም ሞትን የማስቀረትም ሆነ የማዘግየት ሐይሉም ብልሃቱም የለንም።

ሞት በእለት ተእለት ኑሯችን የሚከሰት ሲሆን ወጣቱም አዛውንቱም፤ ሃብታሙም ድሃውም፤ ጠንካራውም ደካማውም ሁሉም ይቀምሳታል። ከሷም የምናመልጥበት መንገድ ወይም እሷን የምናዘገይበት እቅድ አንድም ነገር የለንም። በዚህም ላይ እውቀቱም ጥበቡም ያለው አሏህ(ሱ.ወ) ብቻ ነው። መቀስቀሳችነም ሆነ መመለሳችን ወደ አሏህ(ሱ.ወ) ነው።

ምንም እንኴ በዚች አለም ውስጥ ስንኖር መልካም በመስራትና ባለመስራት በኒያችን ፣ በአቂዳችን ፣ በሃብት ፣ በጐሳ ወዘተ የምንለያይ ቢሆንም መጨረሻችንን በተመለከተ ግን ያለን አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይህም ምንድ ነው ሞት።

ዛሬ ዛሬ እኛ የሰው ልጆች ሞትን ረስተን የውመል ቂያማ ምን ሊገጥመን እንደሚችል ዘንግተን ብዙ አሏህ የማይወዳቸውን ነገሮች እየሰራን እንገኛለን። ሃብት ካለን በድሆች ላይ ለመንገስ እንሞክራለን፤ ጤናማ ከሆን የታመሙትን እናገላለን። ይህ ሁሉ መፎከስ የት ያደርሰን ይሆን?

ማንኛውም ሰው ሞትን ቀማሽ ነው። ይህ እውነታም በልባችን ውስጥ ጠንካራ የሆነ መሠረት ሊኖረው ይገባል። እውነታውም ሂወት በዚች አለም ጊዜያዊና ጠፊነች የሚለው ነው። ሷሊህ የሆኑ ሰዎችም ሆኑ ክፍ ሰዎች ይሞታሉ። እንዲሁም በጅሃድ የሚዋጋ ጦረኛም ሆነ ከቤቱ የተቀመጠ ሰው፤ የትልቅ ግብ ባለቤትም ሆነ ርካሽ ደስታን ፈላጊ፤ ኢፍትሃዊነትን አሻፈረኝ ያሉ ጀግኞችም ሆኖ ፈሪ የቁም ሙቶች ሁሉም ይሞታሉ። የማንኛውም ሰው ነፍስ ሞትን የምትቀምስ ስትሆን ከዚህ ሂወት ትነጠላለች። ይሁን እንጂ በሞቱ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት የመጨረሻ መዳረሻ ቦታቸው ነው። ያም በትንሳኤው ቀን የሚመነዱት ምንዳ ይለያየቸዋል።

ከሞት ብኋላ የሰው ልጅ እንደየስራው የጁን ያገኛል። በዱንያ ላይ የሰራው ስራ መጥፎም ይሁን ጥሩ ይጠየቅበታል፤ ይመነዳበታልም። ኸይር ስራ ያለው ሰው በጀነት የተበሸረ ሲሆን ኸይር ስራ የሌለው ደግሞ ጀሃነም ይጠብቀዋል። እናም ከእሳት የተወገደና ጀነት የገባ ሰው በእርግጥ እሱ ስኬታማ ነው። በነፍሶች መካከል ልዩነት የሚፈጥር ሃብት ይህ ነው።

አንድ ሰው ከሌላ ሰው የሚለየው የመጨረሻው የእረፍት ቦታም ይህ ነው። ዋጋውም ዘላለማዊ ሲሆን ለዚህም ልንለፋለት ይገባል። ሙሉ ሃይላችን ፣ ልፋታችን እና ድካማችን እሷን ለማግኘት መሆን አለበት።


  Grave p2

=<({አል-ቁርአን 3 :185})>=

{185} ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት። ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት በትንሣኤ ቀን ብቻ ነው። ከእሳትም የራቀና ገነትን የተገባ ሰው በእርግጥ ምኞቱን አገኘ። ቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ መሳሪያ እንጅ ሌላ አይደለችም።

ሞትና ውጤቱን በተመለከተ በሐዲስ በአል በራእ ቢን አዚብ(ረ.ዐ) እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል: <ከአንሷር ከሆነ ሰው የቀብር ስነ-ስርዓት ከአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ጋር ሄድንና ወደ ቀብሩ መጣን። በቀብሩ ጐን ያለው ለህድ አልተቆፈረም ነበር። እናም የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ተቀመጡ፤ እኛም በሳቸው ዙርያ ተቀመጥን። መሬቱን ይመቱበት የነበረውን ዱላ በእጃቸው ይዘዋል። ራሳቸውን ቀጥ አደረጉና ሁሌቴና ሶስቴ “ከቀብር ቅጣት የአሏህን ከለላ ሻቱ” አሉ።

ሙእሚን አገልጋይ ይህን አለም ትቶ ሲሆድ ወደ አሄራ እየሄደ ነው። ልክ እንደ ፀሃይ ገፅታ ፊታቸው የነጣ መላኢካዎች በሱ ላይ ያንዣብባሉ። ከጀነት ከፈኖች የሆነ ከፈን ከእሱ ጋር ነው። እንዲሁም እንዳይበሰብስ የሚያደርገውን ከጀነት የሆነ የጀነት ሽቶ ከእርሱ ጋር ነው። 

እነሱም ማየት እስከሚችሉት ድረስ ራቅ ብለው ከእርሱ ርቀው ይቀመጣሉ። የሞት መላኢካም ይመጣና በራሱ በኩል ተቀምጦ “አንች መልካም ነፍስ ሆይ! ከአሏህ ወደሆነ ምህረትና መልካም ወደሆነ ደስታው ውጭ” ይላል። እናም ልክ ከመጠጫ እቃ አፍ እንደሚፈስ ጠብታ ሆና ትወጣለች፤ ይወስዳታልም። በከፈኑ እና በሽቶው እስካል ወሰዳትና እስካላኖራት ድረስ ለአንድ እይታ እርግብግቢት ቢሆን እንኴ በእጁ አድርጐ አይተዋትም።

ከዚያም በምድር እንደሚገኝ የሚስክ መሰል ሽታ ይመጣል። እሷ ጋርም ወደ ላይ ይወጣሉ። በመላኢካ ግርፖች አያልፉም “ማን ነው ይህ ሰው መልካምና ንፁህ ነፍስ ያለው” የሚሉ ቢሆን እንጂ። እናም እገሌ እገሌ የእገሌ የእገሌ ልጅ ብለው ይመልሳሉ። እስከታችኛው ሰማይ እስኪመጡ ድረስ በዚህ አለም መጠራት በሚወዳቸው ስሞች ይጠሩታል። እናም የሰማይ በር ይከፈትለት ዘንድ ይጠይቃል፤ ይከፈትለታል። ወደ ሰባተኛው ሰማይ እስኪወጡ ድረስ በእያንዱ ሰማይ ያጅቡታል። እፁብ ድንቅ ሃያሉ አሏህም በኢልዩን ውስጥ የባሪያየን መዝገብ ፃፉና አካሉ ወዳለበት መሬት ተመለሱ ይላል።

ሁለት መላኢካዎች ወደ እሱ ይመጡና እንዲቀመጥ ያደርጉታል። ያኔ ጌታህ ማን ነው? ይሉታል። እሱም ጌታየ አሏህ ነው ይላል። እነሱም ሐይማኖትህ ምንድ ነው? ይሉታል። ሐይማኖቴ ኢስላም ነው ይላል። ወደናንተ የተላከው መልእክተኛ ማን ነው? ይሉታል። የአሏህ መልዕክተኛ ነው ይላል። እንዴት አወክ ይሉታል። የአሏህን መፅሐፍ አንብቤ እና በሱም አምኜበት ይላል።

ከሰማይ የሆነ ተጣሪ ይጣራል፤ በእርግጥ አገልጋየ እውነትን ተናገረሯል፤ በጀነትም ቦታ አስፉለት፤ የጀነትንም በር ክፈቱለት ይላል። እናም አሉ ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ማዕዛዋና ሽታዋ ወደ እርሱ ይመጣል። አይኑ እስከ ሚያየው ድረስ ቀብሩ ይሰፋል ብለዋል።

መልከመልካም ፊት ያለው ሰው፤ ልብሶቹ የተዋቡ የሆነ ሰው ወደ እሱ ይመጣና የሚያስደስትህን መልካም ዜና ተቀበል፤ ቃል የተገባልህ ጊዜ ይህ ነው ይላል። ሰውየውም ፊትህ መልካምን የሚያመለካላክት አንተ ማን ነህ? ይላል። መልካም ስራህ ነኝ ሲል ይመልስለታል። ሰውየውም እንዲህ ይላል: <ጌታየ ሆይ! ሰአቲቱን(የውመል ቂያማን) ቅርብ አድርጋት> ይላል።

ነገርግን አማኝ ያልሆነ ከሃዲ ዱንያን ትቶ ሲሄድ ወደ መጭው አለም እየሄደ ነው። ጥቁር ፊት ያላቸው መላኢካዎችም በርሱ ላይ ያንዣብባሉ። ሸካራ የጆንያ(የከሽከሽ) ልብስ ይዘው ማየት እስከሚችሉት ድረስ ራቅ ብለው ይቀመጣሉ። የሞት መላኢካ ይመጣና በራሱ በኩል ተቀምጦ እንዲህ ይላል: <አንች ቂል ነፍስ ሆይ! ወደ አሏህ ቅሬታና ቁጣ ውጭ> ይላለታል። እናም ነፍሱ በሙሉ አካሉ ትሰራጫለች። ልክ እንደመጥበሻ ሹካ ባለው ማጉርጥ ስቦ ያወጣታል። ከከርዳዳው ጆንያ ልብስ እስኪያስገባት ድረስ ከእጁ አድርጐ ለአንድ እይታ እርግብግቢት ያህል እንኴ ቢሆን አይተዋትም። ከእሷም በጣም የሚከረፋ የሆነ ሽታ ይወጣል። ከእሷም ጋር ወደ ላይ(ወደ ሰማይ) ይወጣሉ። በማንኛውም የመላኢካ ግሩፖች አያልፉም ይህ የተበከለ ሽታ ምንድ ነው? የሚሉ ቢሆን እንጂ። እናም እገሌ እገሌ የእገሌ የእገሌ ልጅ ይላሉ። ወደ ደታችኛው ሰማይ እስኪመጡ ድረስ በዚህ አለም ይጠራበት በነበረው አስጠሊ ስሞች ይጠሩታል። የሰማይ በር ይከፈትለት ዘንድ ይጠይቃል፤ ለእርሱም ይከፈትለታል።


  Grave p3

=<({አል-ቁርአን 7: 40})>=

{40} እነዚያ አንቀጾቻችንን ያስተባበሉ ከእርሷም የኮሩ ለእነርሱ የሰማይ ደጃፎች አይከፈቱላቸውም። ግመል በመርፌ ቀዳዳ እስክታልፍ ድረስ ገነትን አይገቡም። እንደዚሁም አጋሪዎችን እንቀጣለን።

እናም ሃያሉ አሏህ መዝገቡን በሲጅን ውስጥ ፃፉለት ይላል። ነፍሱም ወዳታች ትወረወራለች።

=<({አል-ቁርአን 22:31})>=

{31} ለአላህ ታዛዦች በእርሱ የማታገሩ ሆናችሁ (ከሐሰት ራቁ)። በአላህም ላይ የሚያጋራ ሰው፤ ከሰማይ እንደ ወደቀና በራሪ ወፎች እንደሚመነጫጭቁ ወይም ነፋስ እርሱን በሩቅ ስፍራ እንደምትጥለው ብጤ ነው።

እናም ነፍሱ ወደ አካሉ ትመለሳለች። ሁለት መላኢካዎችም ይመጡና እንዲቀመጥ ያደርጉታል። በማስከተልም ጌታህ ማነው? ይሉታል። እሱም <አአ አአ አላውቀውም> ይላል። ሃይማኖትህ ምንድ ነው? ይሉታል። እሱም አአ አአ አላውቀውም ይላል። እነሱም ወደ እናንተ የተላከው ማነው? ይሉታል። አአ አአ አላውቀውም ይላል። ከሰማይ የሆነ ተጣሪ ይጣራና ዋሸህ! በእሳትም ቦታውን እስፉለት፤ የጀሐነምን በራፍ ክፈቱለት ይላል። ወላፍኗ ወደ እሱ ይመጣል፤ አጥንቱም እስኪጠላለፍ ድረስ ቀብሩ ይጠባል። የሚያሳዝንህ የሆነን ዜና ተቀበል፤ ይህ ቀን ነበር ቃል የተገባልህ ይለዋል። አንተ ማንነህ ፊትህ የሚያስጠላ የሆነ መጥፎ ነገርን የሚመስል ይላል። እኔ መጥፎ ስራህ ነኝ ይለዋል።  ጌታየ ሆይ ሰአቲቱን(የውመል ቂያማን) አታቁማት ይላል።

{በአህመድና በሌሎችም እንደተዘገበው}

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top