​ስለ እስልምና ሃይማኖት የሚነሱ 7 መሠረታዊ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው 

በወጣቱ ተልዕኮ(አህመድ የሱፍ)

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

1 እስልምና ምንድነው?

ኢስላም የሚለው ቃል ሰላም ከሚለው የአረብኛ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም በአገራችን ቋንቋ ሰላም የሚለውን ቃል ይወክላል። ጠቅለል ባለመልኩ ኢስላም ማለት የእራስን ፍቃድና ፍላጎት ለአምላክ ማስገዛት ማለት ነው። ሆኖም ሌሎች ሃይማኖቶች መጠሪያ ስማቸውን ከመስራቻቸው እንዳገኙ ኢስላም ግን መጠሪያ ስሙን ከሰው ወይም ከጎሳ ወይም ደግሞ ከተገለፀበት አካባቢ አላገኘም። ኢስላም የሚለው የሃይማኖቱ መጠሪያ የተሰጠው በራሱ በፈጣሪ ነው። ለዛም ነው ቃሉ ትልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው። ምክኒያቱም በዚህም ሆነ በመጭው አለም መድህን የሚገኘው የራስን ፈቃድና ፍላጎት ለፈጣሪ በማስገዛት ነውና።

ኢስላም ጥንት የሰው ዘር ሲፈጠር ጀምሮ የነበረ ሃይማኖት እንጅ ከ1400 ዓመት በፊት በነብዩ ሙሐመድ የተመሰረተ ሃይማኖት አይደለም። ሁሉም ነብያቶችና መልዕክተኞች ለምሳሌ አዳም ፣ ኖህ ፣ ሙሴ ፣ እየሱስ ሃይማኖታቸው ኢስላም ሲሆን እንዲያስተምሩ የተላኩትም ሰዎች አሏህን ብቻ እንዲያመልኩና ከጣኦታትም እንዲርቁ ነው።

2 ሙስሊሞች እነማን ናቸው?

ሙስሊም የሚለው የአርብኛ ቃል ትርጉም “እራሱን ለአምላክ ፈቃድ ያስገዛ ሰው” ማለት ነው። የኢስላም አስተምህሮት ለሰው ዘር በሙሉ ሲሆን ይህን አስተምህሮት የተቀበለ ሁሉ ሙስሊም ተብሎ ይጠራል። ይሁንእንጅ አንዳንድ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እስልምና የአረቦች ሃይማኖት ነው ብለው ያምናሉ፤ ይዋሻሉ።

ነገርግን መቼም እውነት እርቆ አይርቅም ከ80% በላይ የሚሆነው የአለም ሙስሊሞች አረቦች አይደሉም። አብዘሃኛዎቹ አረቦች ሙስሊም ናቸው ቢባል እንኳ አረብ የሆኑ ክርስቲያኖች  ፣ አይሁዳውያኖች እና እምነት አልባዎች ይገኛሉ። ለዚህም ማስረጃችን በሃገራችን ኢትዮጲያ  ውስጥ ካሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያላትን በግብፅ ያለችን ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን እና ተከታዮቿን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። እንዲሁም ከናይጀሪያ እስከ ቦስንያ ፣ ከሞሮኮ እስከ ኢንዶኖዥያ ድረስ ብንመለከት የእስልምና ተከታዮች ከተለያየ ብሄር ከተለያየ ጎሳ ከተለያየ ሐገር የሆኑ ናቸው። ሲጀመር እስልምና ለሰው ዘር በሙሉ የሆነ አለም አቀፋዊ አስተምህሮት ነው ያለው። በነብዩ ሙሐመድ የህይወት ዘመን እንኳ ሶሃባዎቻቸው (ሃዋርያዎቻቸው) ከአረብ ብቻ አልነበሩም ይልቁንም ከፐርዥያ ፣ ከአፍሪካ እና ከሮም ጭምር ነበሩ። ለምሳሌ ሁለት ኢትዮጲያዎችን በረካ(ረ.ዐ) እና ቢላሉል ሃበሽን(ረ.ዐ) ማንሳት በቂ ነው።

3​ አሏህ ማነው?

ብዙ ጊዜ እስልምና ሲነሳ አሏህ የሚል ቃል ተደጋግሞ ሲጠራ እንሰማለን። አሏህ የሚለው የአረብኛ ቃል በሌላ ቋንቋ አቻ የሚሆን ፍች ባይኖረውም ብዙ ጊዜ ሃያሉ ጌታ እየተባለ ይተረጎማል። አረብኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች እና አይሁዳውያኖች ይህንኑ ቃል መጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ ይጠቀማሉ። በእንግሊዝኛ “God” ተብሎ የተተረጎመውን ማለት ነው። በሌላ የሴማዊ ቋንቋዎች ጋርም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ በሂብሩ ወይም በይብራይስጥኛ ቋንቋ አምላክ ማለት “ኤላህ” ማለት ነው።

ይሁን እንጅ ትልቁ ልዩነት ኢስላም የሚያስተምረው ንፁህ አሃዳዊነትን ሲሆን ክርስትና እና ሌሎች ሃይማኖቶች ግን ስብከታቸው ጣኦታዊነት ነው። ለዚህ ማስረጃው ኢስላም አምልኮት ለአንድ አሏህ ብቻ የሚገባ እንደሆነ እና አምላክን የሚመስል ምንም ነገር እንደሌለ ፣ አቻ ተጋሪ የሌለው ፣ ልጅም ሆነ ሚስት የሌለው ነው በሚለው ንፁህ አሃዳዊነት ላይ የተመሰረት ሃይማኖት ሲሆን የክርስትና ሃይማኖት ግን ጥሪው ወደ ታቦት ፣ አምላክ ሶስትም አንድም ነው በሚል ተረት እና ብፁአን ሰዎች የክብር ስግደት ያገባቸዋል በሚል የጣኦት አምልኮት ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ነው። በዛ ላይ ማርያምን ከእየሱስ እናትነት በላይ የአምላክነት ማዕረግ ተሰጥቷት እናገኛለን።

4 ሙሐመድ ማነው?

ሙሐመድ አምላክ ለሰው ዘር በሙሉ የላከው የነብያቶች መደምደሚያ መቋጫ ነብይ ነው። ነብዩ ሙሐመድ የሰው ልጅ እንጅ የአምላክ ልጅም ሆነ የአምላክ ባህሪ ፈፅሞ የለውም። እሱ የአምላክ መልዕክተኛ ሰው ብቻ ነው። ተልዕኮው የአምላክን ራዕይ ለሰው ዘር ማስተማር ብቻ ነው። ይሁን እንጅ በብዙ ምክኒያቶች ነብዩ ሙሐመድ የነብያቶች ሁሉ ታላቅ ነው። ምክኒያቱም ከሌሎች ነብያቶች በተለየ ተልዕኮው ብዙ ሰዎችን ወደ ንፁህ አሃዳዊ እምነት ማምጣት ችሏልና። ምንም እንኳ የሌሎች እምነት ተከታዮች በአንድ አምላክ እናምናለን ቢሉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እምነታቸው ተበርዞ ነብያቶችን እና ቅዱሳንን አማልክት አድርገው በመያዝ የአምላክን የመመለክ መብት ለፍጡራን አሳልፈው ሰጥተዋል።

አንዳንድ ሃይማኖቶች ደግሞ ነብያቶቻቸው የአምላክ መገለጫዎች እንደሆኑ ያምናሉ። አምላክ እንደ ሰው ስጋ ለብሶ የተላከ የአምላክ ልጅ ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ የውሸት ሃሳቦች ከፈጣሪ ይልቅ ፍጡራኑ እንዲመለክ የሚሰብኩ ናቸው። ይህ የጣኦት አምልኮ ተግባር ሲሆን በሌላ ሶስተኛ ወገን በማርያም ፣ በመልአክቶች እና በደጋግ ሰዎች በኩል አምላክን መቅረብ ይቻላል ብለው ያምናሉ። ነብዩ ሙሐመድ ግን ያስተምር የነበረው እሱ የአምላክን ራዕይ ለማስተማር የተላከ የሰው ልጅ እንደሆነ ብቻ ነው። ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ዘር በሙሉ ታላቅ ተምሳሌት ነው። በተምሳሌትነቱ ያለ ቤተ-መንግስት ሐገር ያስተዳደረ ፣ የጦር መሪ ፣ ነጋዴ ፣ ገዥ ፣ አስተማሪ ፣ ጎረቤት ፣ ባል ፣ አባት እና ጎደኛ ነበር። አምላክም ከእሱ ብኋላ ሌላ መልዕክተኛ እንደማይልክ ቃል ገብቷል። ሆኖም ሁሉም መልዕክተኞች ሲያስተምሩት የነበረው ሃይማኖት ኢስላም ሲሆን የዚሁ ሃይማኖት የመጨረሻ እንጅ የመጀመሪያ ያልሆነው ነብዩ ሙሐመድ የነብያቶችና የመልዕክተኞች መቋጫ መደምደሚያ ነው።

5 የእስልምና አስተምህሮቶች ምንድን ናቸው?

የእስልምና ሃይማኖት መሠረቱ የአምላክ አንድነት ነው። ይህ ማለት ሊመለክ የሚገባው ፣ ውብና እንከን የሌላቸው ስሞች እና ባህርያት ያሉት ፣ የዚህ አለም ፈጣሪና አስተናባሪ ፣ ሰጭ ፣ ነሽ የሆነ ፈጣሪ መኖሩን ማመን እና እሱንም ብቻ ማምለክ ማለት ነው። በአምላክ አንድነት ማመን በእርግጥ አምላክ አንድም ሶስትም ነው ለሚለው የስላሶች ተረት ተቃራኒ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ሃይማኖቾች የዚህ ፍጥረተ አለም አስገኝ አንድ አምላክ እንደሆነ እና በአንድ አምላክ እንደሚያምኑ ይናገሩ ይሆናል። ነገርግን እስልምና በዚህ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ከአንድ አምላክ ውጭ ጌታ እና አዳኝ የሚልን መላምት ውድቅ ያደርጋል። እንዲሁም እስልምና በፈጣሪና በሰው መካከል የሚደረግን የሶስተኛ ወገን አምልኮ ፈፅሞ ያወግዛል። ለምሳሌ ማርያም በራሷ ለሰው ልጅ ምንም ምላሽ መስጠት የማትችል ሆና ሳለ “ድንግል ማርያም ሆይ! ችግሬን አንሽልኝ እንጅ ስለትሽን እሞላለሁ።” ሲሉ ይለምኗታል፤ ስለትንም ለሷ ያደርሳሉ። እንዲሁም ብፁአን ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን ይለምናሉ፤ ለእነሱም ይሰግዳሉ። ለታቦትም እንዲሁ ይሰግዳሉ፤ ይሳላሉ።

አስቡት አምላክ እንጨትን ፈጥሮ የሰው ልጅ ግን  ምላሽ የማይሰጠውን እንጨት ጠርቦ አምላኩና የአምላኩ ማደርያ አድርጎ ይገዛዋል ይሰግድለታል ፣ ይለምነዋል ፣ በእሱ ስም ይምላል ፣ ይሳላል። እስልምና ግን ከዚህ አይነት አምልኮ የፀዳ ሃይማኖት ሲሆን አምልኮት የተባለን ነገር በሙሉ ለአንድ አምላክ ብቻና ብቻ ያደረገ ሃይማኖት ነው። እንዲሁም የሰው ልጅ ሃጢያት ቢሰራ ፣ ቢቸግረው ፣ ሊያመልከው እና ሊለምነው ቢፈልግ አምላኩን በቀጥታ ቀርቦ መለመን እንደሚችል ያስተምራል። ሆኖም የነፍስ አባት ፈፅሞ በኢስላም ቦታ የለውም። ምክኒያቱም የሰው ልጅ አምላኩን በቀጥታ በመለመን እና ወደ እሱ በመመለስ ፀሎቱንም ንሰሃውንም ማድረስ ይችላልና።

የዚህ ውሸት መሠረቱ አምላክ በቀጥታ ፍጡራኖቹን አይምርም ብሎ ማመን ሲሆን የሃጢያት ሸህም አጋነው በመግለፃቸው እንዲሁም አምላክ ፍጡራኖቹን በቀጥታ አይምርም ብለው በማመን ውሸተኛ ሃይማኖቶች የሰው ልጅ ከአምላክ እዝነት ተስፋ እንዲቆርጥና እንዲርቅ አድርገውታል። አንዴ አምላክን በቀጥታ መቅረብ የማይችሉ መሆኑን ውስጣቸውን ካሳመኑ ብኋላ እርዳታን  ከውሸት አማልክቶች በመሻት ዳግም እራሳቸውን ያጠማሉ። እነዚህ የውሸት አማልክቶች የተለያየ አይነት ቅርፅ ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ፦ ቅዱሳናት ፣ መላእክት ፣ መልዕክተኞች ፣ ቤተክርስቲያኖች ፣ ታቦቶች ፣ ብፁአን ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ወይም ደግሞ የአምላክ ልጅ ወይም የሰው ስጋ ለብሶ የተወለደው አማላክ ወ.ዘ.ተ ናቸው።

ይሁን እንጅ በማንኛውም ሁኔታ የውሸት አማልክቶችን የሚለምኑ  ፣ ለእነሱ የሚሰግዱ ፣ ከእነሱ እርዳታን የሚሹ ሰዎች የሚጠሯቸው ወይም ብለው የሚያስቧቸው አምላክ እንደሆኑ ሲሆን እምነታቸውም በአንድ አምላክ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይሞግታሉ። ታዲያ ስለ ስላሶች እና አምላክ የሰው ስጋ ለብሶ ስለመወለዱ ሲነሳ እሱ ሚስጥር ነው ብለው ነገሩን አመድ ያለብሱታል። በእስልምና ግን በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ግልፅ ልዩነት አለ። በመለኮትነት ዙርያ በእስልምና ምንም አይነት ሚስጥር ወይም አሻሚ የሆነ ነገር የለም። ምክኒያቱም ፍጡር ለሆነ ነገር ማንኛውም የአምልኮት አይነት አይገባውም። ምክኒያቱም አምልኮት የተባለ ነገር በሙሉ ለአንድ አምላክ ብቻና ብቻ ነውና የሚገባው። አንዳንድ ሃይማኖቶች ደግሞ አምላክ የፍጡራኑ አካል ነው ብለው በማመን ወደ ፈጣሪያቸው ለመቅረብ ፍጡር የሆነውን ነገር ማምለክ ይጀምራል። ይህ ግን ከንቱነት ነው።

ሙስሊሞች አምላክ ሚስት ፣ ልጅ ፣ ቤተሰብ ፣ አጋዥ ደጋፊ የሌለው መሆኑን ያምናሉ። በሙስሊሞች እምነት አምላክ አይወልድም አይወለድም። ምክኒያቱም አምላክ አስገኝ የሌለው ድንቅ እና ዘላለማዊ ነውና። የሰው ልጅን ከሃጢያት ለማዳንም የሰው ስጋ ለብሶ መወለድ አያስፈልገውም። ምክኒያቱም ይህን ፍጥረተ አለም ሲፈጥር ጀምሮ እዝነቱ እና ምህረቱ በሰማይም በምድርም የተዘረጋ ነውምና። ለዛም ነው ሃያሉ ፣ ርህሩሁ ፣ አዛኙ የተባለው።

6 ቁርአን ምንድን ነው?

ቁርአን አምላክ ለሰው ልጆች በጅብሪል (በመልአኩ ገብርኤል) አማካኝነት በአረብኛ ቋንቋ ለነብዩ ሙሐመድ የገለፀ የመጨረሻው ወህይ (ራዕይ) ሲሆን እስከ እለተ ትንሳኤ ድረስ ሙሉ የሆነ የህይወት መመሪያ ነው። ይህ ቁርአን የነብዩ ሙሐመድ ሶሃባዎች እየሸመደዱት እና እያነበቡት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እንዲት ሆሄ ሳትቀየር እስከዛሬው ቀን ድረስ ዘልቋል። ቁርአን በዚህ ዘመንም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እየሸመደዱት እና እየተማሩት ነው።

የቁርአን ቋንቋ አረብኛ ሲሆን በሚልዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በህይወት ያለ ቋንቋ ነው። እንደሌሎች ሃይማኖቶች መጽሐፍት ሳይሆን ቁርአን አሁንም በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች በተገለፀበት ቋንቋ እየተነበበ የሚግኝ ነው። የአረብኛ ቁርአን ህያው የሆነ ተአምራዊ መጽሐፍ ነው። ቁርአን ለሰው ልጆች በሙሉ የተገለፀ ሲሆን በ23 ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር ለሙሐመድ የተገለፀለት። ቁርአን በነብዩ የህይወት ዘመን በሙስሊሞችም ሆነ በካፊሮች ፊት ይቀራ የነበረ ሲሆን እንደ ክርስትና ሃይማኖት መጽሐፍት ሳይሆን ቁርአን የተፃፈው ሙሐመድ በህይወት በነበሩበት ጊዜና በእርሱ ሶሃባዎች (ሃዋርያዎች ) አማካኝነት ነው።

የቁርአንን አስተምህሮት ለተወሰነ ጎሳ ወይም ለተመረጡ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ የህይወት መመርያ ነው። ይዞ የመጣው መልዕክት አዲስ ሳይሆን ሁሉም መልዕክተኞች “አምላክን ተገዙ ከጣኦታትም ራቁ” ሲሉ ያወጁትን መለኮታዊ መልዕክት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም በአንድ አምላክ የማመንና ህይወትን በዚህ መጽሐፍ የመምራት ጠቀሜታን ፣ የተለያዩ የቀደምት ነብያትን ለምሳሌ፦ የኖህን ፣ የአብርሃምን ፣ የሙሴን እና የእየሱስን ታሪክ አቅፎ ይዟል። እንዲሁም ብዙ የአምላክ ትዕዛዛትን እና ክልከላዎችን ይዟል። ለዘመነው አለም ፣ ሰዎች ለተለከፉበት የጥርጣሬ በሽታ ፣ መንፈሳዊ ተስፋ መቁረጥ ፣ ለፖለቲካው ውጥንቅጥ እና ግርግር የቁርአን አስተምህሮት መፍትሄዎችን ይዟል።

7 ሙስሊሞች የሰው ልጅን ተፈጥሮ ፣ የህይወትን አላማ እና የመጭውን አለም ህይወት እንዴት ይመለከቱታል?

በቅዱስ ቁርአን አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው እሱን ብቻ ያመልኩት ዘንድ እንደሆነ እና የእውነተኛ አምልኮቶች ሁሉ መሰረቱ አምላክን መፍራት እንደሆነ ያስተምራል። የእስልምና አስተምህሮት ሁሉንም የህይወት እርከን ያቀፈ በመሆኑ በሁሉም የሰው ልጅ ጉዳዮች ውስጥ አምላክን መፍራት መሠረት ሊኖረው ይገባል። እስልምና የሰው ልጅ የሚሰራቸው ሁሉም ስራዎች ለአምላክ ተብለው በአምላክ ህግ መሰረት የተሰሩ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ስራዎች እንደ አምልኮት ይቆጠራሉ ሲል ግልፅ አድርጎታል። ሆኖም በእስልምና የአምልኮት ተግባር በፀሎት ወይም በስግደት  ብቻ የተገደበ አይደለም። የእስልምና አስተምህሮት መተናነስን ፣ ትህትናን ፣ ቅንነትን ፣ ትዕግስትን እና ለጋስነትን የሚያበረታታ ሲሆን ኩራትን እና በራስ መደነቅን ያወግዛል። እስልምና የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ትክክለኛና ሚዛናዊ እንደሆነ ያስተምራል።

የሰው ልጆችም በተፈጥሮ ሃጢያተኞች እንዳልሆኑ እና እምነትና ተግባር ተያይዘው የሚሄዱ ነገሮች እንደሆኑ ያስተምራል። አምላክም ለሰው ልጆች ነፃ ምርጫን ሰጥቷቸዋል። ለአንድ እምነት መለኪያውም መልካም ሃሳብና ተግባር ነው። ነገርግን የሰው ልጆች የተፈጠሩት ደካማ ሆነው ሲሆን ሃጢያት ላይ ይወድቃሉ። ምክኒያቱም የሰው ልጆች እምነት ሙሉ እንደሆነ አይቀጥልምና። አንዳንዴ ሊጨምር አንዳንዴ ደግሞ በቸልተኝነት ሊቀንስ ይችላል። ይሁንእንጅ የሰው ልጆች ሃጢያት ሲሰሩ የነፍስ አባት ወይም የንሰሃ አባት አያስፈልጋቸውም። ምክኒያቱም ፈጣሪያቸውን በቀጥታ በመለመን በንሰሃ ወደ እሱ መቅረብ ይችላሉና። የእስልምና ህይወት ሚዛናዊነት አምላክን በመፍራት እና እልቆቢስ በሆነ እዝነቱ በማመን ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለነብዩ ሙሐመድ የተገለፀው ቁርአን ስለ መጭው አለም ህይወት እና ስል ፍርዱ ቀን ትልቅ አስተምህሮትን ይዟል። በዚህም ምክኒያት ሙስሊሞች ሀሉም የሰው ልጆች ስለ ቀድሞ ህይወታቸው እምነት እና ተግባራት በአምላክ ፊት ይዳኛሉ ብለው ያምናሉ። አምላክም በዳኝነቱ አዛኝ ፣ ርህሩህ እና ፍትሃዊ ነው።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top