ወጣትነታችንን እንጠቀምበት

ውድ ጓደኞቼ አሏህ(ﷻ) በህይወት እንድንኖር 60 አመት እድሜ ቢሰጠን…ይህ ማለት 22,000 ቀን (60×365) ነው። አሏህ ይህን ሁሉ ቀናት የሚሰጠን ታዲያ ለፍርዱ ቀን እንድንዘጋጅ ነው። ያን ቀን አሏህ ጥያቄዎችን ይጠይቀናል። የሚፈልገውም ትክክለኛ መልስ ነው። አሏህ(ﷻ)እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ ነውና ጥያቄዎቹ ምን እንደሆኑ ቀድሞ በቁርአን እና በሐዲስ ነግሮናል። እዝነቱ በጣም ትልቅ ነው፤ አጥናፍ ወሰን የለውምና የጥያቄዎቹንም መልስ ነግሮናል። እስኪ አስቡት አንድ ተማሪ ሊፈተን ገብቶ ፈተናውን እንደገለጠ በአንድ ጎን ጥያቄው ፣ በአንድ ጎን ደግሞ የጥያቄው መልስ ተቀምጦ ቢያገኘውስ። ይህ ተማሪ ፈተናውን ከተፈተነ በኋላ ቢወድቅ ምንድነው የምንለው? ስለ ተማሪው ምን እናስባለን? ደደብ ወይም የማይረባ እንደሆነ ነው የምናስበው አይደል። ጥሩ! ታድያ እኛ ሰዎች በፍርዱ ቀን እነዚህን ጥያቄዎች እና መልሳቸውን እያወቅን እንወድቃለን። ያን ቀን ከመውደቃችን እና ከመክሰራችን በፊት አሁን መንቃት ያለብን ጊዜ ነው።

ወጣትነት የህይወታችን አፍላ ጊዜ ነው። የልጅነት እድሜ አልፎ በእራሳችን የምንቆምበት ፣ ጥንካሬና ብርታት የምናገኝበት ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ የሌለበት ፣ ሁሉነገር አዲስ ፣ ሮጠን የማንደክምበት ፣ ተጫውተን የማንጠግብበት አፍላ ጊዜ። ሆኖም ሰዎች ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉ የሚወስኑበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ የምናደርገው ነገር በቀሪ ህይወታችን በምናደርገው ነገር ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል። ለዛም ነው በዚህ ወሳኝ ጊዜ እስልምናን ወደ ህይወታችን ማምጣት እና መተግበር አስፈላጊ የሆነው። ብዙ ሰዎች እድሜያችን ሲገፋ አርባና አምሳዎቹ ውስጥ እስልምናችነን እንተገብራለን ብለው ያስባሉ። ምናልባትም እኔ እና እናንተም ይህ ስሜት ይኖረናል። ነገርግን እስኪ በዚህ መንገድ እንመልከተው። ጥሩ የእግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን ብንፈልግ ኳስ ማድበልበል ፣ መለጋት እና ማቀበል ወ.ዘ.ተ መለማመድ ያለብን ገና በልጅነት ፣ በወጣትነት እድሜ ነው። በጊዜ ሂደት የኳስ ክህልሎታችን እያሻሻልን እንሄዳለን። ነገርግን እድሜያችን ሲገፋ ፣ እርጅና ሲመጣ መጫወት እንጀምራለን ብንል ጥሩ እና ውጤታማ ተጨዋች የመሆናችን እድል ዜሮ ነው የሚሆነው። እንኳንስ ልኖርጥ ቀርቶ ለሰአታት ልንቆም አንችልም። ይህ እውነት ነው! እድሜ ሲገፋና እርጅና ሲመጣ ቁመን ለመስገድ እንኳ ሃይልና ጉልበቱ አይኖረንም። በዚህ እድሜ ላይ ያሉ ሰዎች ብዙዎቹ ማረፍና መቀመጥ ነው የሚወዱት።

የወጣትነት ህይወታችን አፍላ ጊዜ ነው። ለዛም ነው አሏህ ዘንድ በጣም ተወዳጅ የሆነው። በመጭው አለም ህይወት የወጣትነት ጊዜህን በምን አሳለፍከው ወይም አሳለፍሽው ተብለን መጠየቃችን አይቀርም። የወጣትነት ጊዜያቸውን አሏህን በማምለክ ለሚያሳልፉ በፍርዱ ቀን ፀሐይ ስንዝር በምትቀርብበት ጊዜ ጥላን አዘጋጅቶላቸዋል። ያን ቀን ከአሏህ ዙፋን ጥላ በቀር ሌላ ጥላ አይኖርም። አስቡት በጣም ፀሃያማና ሞቃት በሆነ ቀን ለብዙ ሰአታት ውጭ ላይ ብንቆም እንዴት ነው የሚያደርገን? ምንድነው የምንፈልገው? በእርግጠኝነት እምናርፍበት ጥላ እንፈልጋለን። ነገርግን ፀሐይ ወደ እኛ በጣም በቀረበች ጊዜ ፣ ሙቀቱ ባየለ እና በከፋ ቀንስ….የዚያን ቀን የአሏህን ዙፍን ጥላ የሚፈልገው ማነው? አዎ ሁላችንም እንፈልጋለን!

እኔ እና እናንተ የአሏህን ትዕዛዛት በመፈፀም ፣ ኢባዳዎችን በማብዛት ደካሞች ነን። አሏህ ያን ያውቃል። አሏህ የሚፈልገው የተሻለ ነገር ለመስራት መጣራችንን እና መሞከራችን ነው። ህፃን ልጅ መራመድ ሲጀምር እየወደቀ እየተነሳ ነው። ቁጭ እንዳለ አይቀርም ወይም በአንድ ጊዜ ሳይድህ ሳይለማመድ ቆሞ ሊሄድ አይችልም። ይነሳል፤ ይወድቃል። እግሮቹ በጠነከሩ ጊዜ በእራሱ መራመድ ይጀምራል። ልክ እንደዚሁ እኛም የቻልነውን ሁሉ ማድረግ እና መታገል ይጠበቅብናል። እጅ መስጠት የለብንም። ኢንሻ አሏህ! አንድ ቀን አሏህን ለመገዛት በጣም ጠንካሮች እንሆናለን። አሁን እየወደቅን እየተነሳን ቢሆን የአሏህን ትዕዛዛት ለመፈፀም ለአሏህ ቃል እንግባ! ምንም ይሁን ምን የተፈጠርንበትን አላማ እየወደቅን እየተነሳንም ቢሆን እንፈፅማለን። መንገዱን አሏህ ያግራልን! አሚን!

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top