ሂጃብ የጀነት ቁልፍ ነው።የጀነት መግቢያን ለማግኘት የሂጃብን ጠቀሜታ እና ልዩ ልዩ ባህሪያቶቹን እና የሚያስገኛቸውን ትሩፋቶች ማወቅ ጠቃሚ ነው።

ሂጃብ ቅድስናን ያጐናፅፋል

"የአደም ልጆች ሆይ የአካል ክፍላችሁን እና ጌጦቻችሁን የምትሸፍኑበት የሆነን ማስጌጫ እና የቅድስና አልባሳትን ሰጣናችሁ፤ያም ለናንተ ከሁሉም በላይ የተሻለ ነው።ታስታውሱም ዘንድ እነዚህ ከአሏህ ምልክቶች መካከል ናቸው።" {አል-ቁርአን 7:26}

ይህ ማለት አሏህ ሁለት አልባሳትን ልኴል:- አውራሽን የምትሸፍኝበት እና የሚያስውብሽ የሆነን።የአሏህ ፍራቻ በልብሽ ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግሽ ልብስ ከሁሉም በላይ የተሻለ ነው።በሌላ አነጋገር የሃያሉ አሏህ ፍራቻ በልብሽ ውስጥ መኖር እና አስተዋይነትሽ የሰው ልጅ እራሱን ከሚያስውብበት እና ከሚያስጌጥበት ሁሉ የተሻለ የሆነን አሏህ ይሰጥሻል።ምክኒያቱም ውስጣዊ ንፅህና ከውጫዊ ውበት የተሻለ ነውና፤ላያቸው ያማረ ሆኖ ውስጣቸው አሮ በቤተሰቦቻቸው፣በዘመዶቻቸው ባጠቃላይ ማህበራዊ ኑሯቸው ምስቅልቅሉ የወጣባቸው፣ውስጣቸው በሃዘን ተውጦ አፋቸውን ከፍተው ስለሳቁ ወይም ፈሽረክ ስላሉ እውነት በልባቸው የደስተኛነት ስሜት ኖሯቸው ይመስልሻል? እንደኔ እንደኔ እያረሩ መሳቅ ብቻ ነው የሚሆነው።እናም የተሻለው ልብስሽ ለጌታሽ ያለሽ ታዛዥነት ነው።ለአሏህ ትእዛዝ ተገዥ ያልሆነች ሴት ከእሷ መልካም ነገር አይገኝም።

  • ሂጃብ ልብን ያፀዳል
"....ማንኛውንም ነገር በፈለጋችሁ ወቅት ሚስቶቹን ስትጠይቁ ከኋላቸው ካለ ክፍል (መጋረጃ) ሁናችሁ ጠይቁ፤ያ ለናንተም ለነሱም ንፁህ ነው።" {አል-ቁርአን 33:53}

ይህ የቁርአን አንቀፅ የሚያረጋግጠው ሰወች በሂጃብ ውስጥ መሆናቸው በሩህ እና በልብ መካከል ያለን ፍላጐት እና ፈተናን ሁሉ ደብዛውን እንደ ሚያጠፋ ነው።አሏህ እንዲህ ብሏል:-

 "የነቢዩ ሴቶች ሆይ! ከሴቶች እንደ ማናቸው አይደላችሁም፤ አላህን ብትፈሩ (ትበልጣላችሁ)፤ ያ በልቡ ውስጥ በሽታ ያለበት እንዳይከጅል በንግግር አትለስልሱ፤ መልካምንም በንግግር ተናገሩ።" {አል-ቁርአን 33:32}
በአቡ ሑረይራ እንደተዘገበው መልእክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ይሉኝታ (ሃያእ) የእምነት ክፍል ነው። አምነትም ወደ ጀነት ይመራል ብለዋል። {አትርሚዚ/ አል-አልባኒ ሰሂህ ብለውታል}

ሂጃብ አንዲትን ሴት በኢስላም ያላትን ደረጃ እንድትረዳ የሚያደርግ መሆኑ ጥርጥር የለውም።ሂጃብሽን መልበስሽ ሃያእ(ይሉኝታ) እንዲኖርሽ እና እንድታዳብሪው ያደርግሻል።ይህን በማድረግሽ አሏህ የተሻለን ነገር ያጐናፅፍሻል።

ሂጃብ ራስን ከመጥፎ ነገር መከለያ ነው።

መልእክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ከባሏ ቤት ውጭ ሆና እራሷን የገላለጠች ከሏህ የተሰጣት የሆነን መከለያዋን ጥሳለች ብለዋል። {አህመድ አልባኒ ሰሂህ ብለውታል}

ሂጃቧን ያደረገች ሴት በዚህ አለምም ሆነ በመጭው አለም ከጌታዋ አሏህ የሆነን መከለያ ታገኛለች፤ከጀነት ነዋሪዋችም መካከል ትሆናለች።

  • ሂጃብ የፊጥራ አካል ነው

ሂጃብ የፊጥራ(የተፈጥሮ ባህሪ ) ክፍል ነው።ይህን በጥልቅ ለመረዳት ተፈኩር(ማስተንተን) ጠቀሚ ነው። በዙሪያሽ ያሉ ነገሮችን ተመልከች ሁሉም ሽፋን አላቸው። ለምሳሌ መሬት በከባቢ አየር የተሸፈነች ናት፤ የውስጥ የአካል ክፍሎች ፣ ሴሎች ፣ ማእድናት ፣ ፍራፍሬ ወዘተ የራሳቸው የሆነ መሸፈኛ አላቸው፤ ቆዳሽ ብርሃን አስተላላፊ ቢሆን ኖሮ ምን ልትመስሊ እንደምትችይ አስቢው። ባጠቃላይ መሸፋፈን መከናነብ የስነ-ፍጥረት ህግ ነው ማለት ይቻላል። አሏህ እራስሽን እንድትሸፋፍኝ ደንግጐታል።

"ለአማኝ ሴቶች አይኖቻቸውን እና ብልቶቻቸውን ይከልሉ ዘንድ ንገራቸው፤ጌጣቸውንም ግልጽ ከሆነው በቀር አይግለጡ፤ መከናነቢያቸውንም በአንገተቸው ላይ ያጣፉ፤ጌጣቸውን ለባሎቻቸው ወይም ለአባቶቻቸው ወይም ለባሎቻቸው አባቶች ወይም ለወንድ ልጆቻቸው....በስተቀር አይግለጡ።" {አል-ቁርአን 24:31}

አንዳዴም ይሉኝታ ያላት ሙስሊም ሴት አሏህ ለሷ ህጋዊ ባደረገላት ባል ላይ እንኴ የአይን አፋርነት ስሜት ሊሰማት ይቸላል። ነገር ግን ይህ አይናፋርነትሽ አንችን ሊያስጨንቅሽ አይገባም። ይልቁንስ አንዱ የእምነትሽ ክፍል እንደሆነ ልታውቂ ይገባል። ሌሎች እህቶችሽ ይሉኝታቸውን ስለገፈፉ ፣ የጌታቸውን ትእዛዝ ጥሰው እርቃናቸውን ሆነው ስለሄዱ ፣ ብዙ ወንዶች በግራ በቀኝ አጅበዋቸው ስለሄዱ አንቺ የበቸኝነት እና የኋላቀርነት ስሜት ሊሰማሽ አይችልም። ይልቁንስ ከአሏህ ዘንድ የተመረጥሽ የኢስላም አምባሳደር እንደሆንሽ እና ሂጃብሽን አድርገሽ ሙስሊሙ ኡማ ሲያይሽ ላንቺ ያለው ፍቅር እና ክብር ሊሰማሽ ይገባል። ከሁሉም በላይ አሏህ ላንቺ ያለውን ውዴታ አስታውሽ። የሰው ልጅ ውስጣዊ ባህሪው እንኴ እራሱን እንዲሸፋፍን ጥሪ ያደርግለታል።

  • ሂጃብ አሏህን የመገዛት አካል አንዱ ነው

አሏህ ሴቶች ሂጃብን ይለብሱ ዘንድ የደነገገው እሱ ነው። የአሏህ ፍረርሃት እና ፍቅር በልቧ ውስጥ ያለ አንዲት ሙስሊም ሴት ሁሌም ለአሏህ ትእዛዝ ተገዥ ናት። የሂጃብ ጉዳይ በኢስላም ትልቅ ቦታ አለው።

  • ሂጃብ ፍፃሜን ያሳምራል
መልእክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) አሏህ ለባሪያው መልካም ነገርን ሊያደርግለት ሲፈልግ እሱን ይጠቀምበታል፤ አሏህ እንዴት ሊጠቀምበት ይችላል ሲሉ ሰወች ጠየቁ። እሳቸውም ከመሞቱ በፊት መልካም ስራን እንዲሰራ ይመራዋል ፣ እናም እያደረገውም እያለ ሩሁን ይወስዳል ብለዋል።
{ትርሚዚ አልባኒ ሰሂህ ብለውታል}

ውድ እህቴ ሆይ! አሏህ መልካም ወደሆነ ነገር እዲመራሽ የምትፈልጊ ከሆነ ሂጃብሽን አሏህ ባዘዘሽ መሠረት ልበሽ፤ራስሽንም ለትእዛዙ ተገዥ አድርጊ።

  • ሂጃብ ከሃጢያት ይከላከላል
መልእክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ጀሃነም የሚገቡ ሁለት ቡድኖች አሉ ከነአሱ መካከል አንዷ የለበሰች የመሰለች ነገር ግን ያለበሰች የሆነች ናት ብለዋል።
{ሙስሊም}

በአሏህ(ሱ.ወ) ቁርአንና በነቢዩ ሙሐመድ( ሰ.ዐ.ወ) ትምህርት መሰረት ሂጃብ አምስት ቅድመ ሁኔታዎች አሉት።

  1. መሸፈን ያለበት አካል

በኢስላም አንዲት ሴት ልጅ ከፊቷና አመዳፏ በስተቀር ሁሉንም የሰውነቷን ክፍል እንድትሸፍን ያዛል።ለወንዶች ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከአምብርት ጀምሮ እስከ ጉልበት ድረስ መሸፈን ያለበት መሆኑን ያስተምራ።ሴት ልጅ ፍላጐቿ ከሆነ ፊቷንም ሆነ መዳፏን መሸፈን የምትችል ሲሆን አንዳንድ የኢስላም ሊቃውንቶች ደግሞ ሴት ልጅ ፊቷንም ሆነ እጆቿን መሸፈን ግዴታ መሆኑን ያስተምራሉ።ኢስላም በሴቶች ላይ ብቻ የደነገው የሂጃብ ቅድመ ሁኔታ ይህኛው ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ አምስት ህግጋት በወንዶችም ላይ ይሠራሉ።

  1. የልብሱ ስፋትና የስፌቱ ሁኔታ

ልብሱ ሰውነት ላይ የሚጣበቅና የሰውነትን ቅርፀጽን የሚያሳይ መሆን የለበትም።ይህ ህግ ለወንድም ሆነ ለሴት የሚሠራ ሲሆን በቀላሉ ሴቶች የሚለብሱት አካላቸው ላይ የተጣበቀና የሰውነት ቅርጽን የሚያሳይ መሆን የለበትም።ለምሳሌ የዳሌ ስፋትን፣ጡትን፣የወገብ ቅርጽን እና የመሳሰሉትን የሰውነት አካላትን የሚያሳይ ወይም ግልጽ የሚያደርግ ልብስ በኢስላም ክልክል እና የተወገዘ ነው።

  1. የጨርቁ ስስነት

ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚለብሷቸው አልባሳት በጣም ስስ ከሆነ የጨርቅ ዓይነቶች የተሠሩ መሆን የለባቸውም።ከየትኛውም አቅጣጮ ብርሃን ወደ ውስጥ የሚያስተላልፍ እና የአካል ክፍልን የሚያሳዩ የልብስ አይነቶች በሙሉ ክልክል ናቸው።

  1. የልብሱ ማራኪነት

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሚለብሷቸው አልባሳት አለመጠን ተጋነው ተቃራኒ ፆታን የሚስቡና የተቃራኒ ፆታን ወሲባዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ እንዲሁም በጣም የተንቆጠቆጡና ለአላፊ አግዳሚው መጠቇቆሚያ የሚያደርጉ መሆን የለባቸውም።

  1. ተገቢ የሆነ የአለባበስ ሕግን መከተል

በኢስላም ሥርዓት ውስጥ ሴቶች መልበስ የሚችሉት የሴቶችን አለባበስ ብቻ ነው።ሴቶች ወንድ የሚያስመስላቸውን፤ወንዶች ደግሞ ሴት የሚያስመስላቸውን የአለባበስ ሥርዓት መከተል አጥብቆ የተወገዘ ነው።ልብስ ለሌሎች የሚያስተላልፈው መልእክት በኢስላማዊ ሥርዓት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሌላ ባእድ ሀይማኖት ተከታዮች ወይም ሀይማኖት የሌላቸው ጣዖት አምላኪዎችና የመሳሰሉ ህዝቦች እምነታዊ መግለጫ የሆነ የአለባበስ ሥርዓትን መከተል የቱንም ያህል ማራኪና ምቹ ቢሆኑም እንኴ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top