ክፍል ሶስት

የውሸተኛ ሃይማኖት መልእክት

በአለም ላይ ብዙ የእምነት ቡድኖች ፣ ሃይማኖቶች ፣ ፍልስፍናዎችና ንቅናቄዎች ይገኛሉ። ሁሉም ትክክለኛው መንገድ የኔ ነው ወይም ወደ አሏህ የሚወስድ ብቸኛው መንገድ የኔ ነው ብለው ይናገራሉ። እናም አንድ ሰው የትኛው ትክክለኛ እንደሆነ ወይም ሁሉም ትክክለኞች እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ እንዴት ይቻላል? መልሱን ማግኘት የሚቻልበት ዘዴ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ መንገድ ጥሪ የሚያደርጉበትን ማእከላዊ የአምልኮት ዒላማ ለይቶ በማውጣት ነው። ሐሰተኛ ሀይማኖቶች ሁሉ አሏህን አስመልክቶ አንድ የጋራ ግንዛቤ አላቸው። ሰዎች ሁሉ አማልክት ናቸው፤ ወይም የተለያዩ ሰዎች አሏህ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ተፈጥሮ አሏህ ነው ብለው ይላሉ።

ከዚህም በመነሳት የሐሰተኛ ሃይማኖት መሠረታዊ መልእክት አሏህ በራሱ ፉጡራን ተመስሎ ሊመለክ ይችላል የሚል ነው። ሐሰተኛ ሃይማኖት ፍጥረትን ወይም አንድን የፍጥረት ገጽታ አምላክ ነው ብሎ በመሰየም የሰው ልጅ ፍጥረትን እንዲያመልክ ጥሪ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ነብዩ ኢሳ/እየሱስ(ዐ.ሰ) ተከታዮቻቸው አሏህን እንዲያመልኩ የጋበዙ ሲሆን የእየሱስ(ዐ.ሰ) ተከታዮችነን ባዮች ግን ኢየሱስ ራሳቸው አሏህ ናቸው በማለት ሕዝቡ ኢየሱስን እንዲያመልክ ይሰብካሉ። ቡድሃ አያሌ ሰብአዊ ይዘት ያላቸው መርሆወችን ወደ ሕንድ ያስገባ የተሐድሶ አራማጅ ነበር። አምላክ ነኝ አላለም ወይም የአምልኮታቸው ዒላማ የመሆን ሐሳብ ለተከታዮቹ አላቀረበም ነበር። ነገር ግን ዛሬ ከሕንድ ውጭ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ቡድሂስቶች ቡድሀን አምላክ አድርገው በመያዝ በነሱ ግምት በርሱ አምሳል በተቀረጹ ምስሎች ላይ ተደፍተው ይሰግዳሉ።

አምልኮው ዒላማ ያደረገውን ነገር ለይቶ ማውጣት የሚለውን መርሕ በመጠቀም ፣ ሐሰተኛ ሃይማኖት በጣም ግልጽና የሥረ-መሠረቱ ሰው ሰራሽ ተፈጥሮም ገሃድ ይሆናል። አሏህ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ብሏል፦

"ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ አምላክ ብላችሁ የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዙም፤ አሏህ በርሷ ምንም ማስረጃ አላወረደም፤ ፍርዱ የአሏህ እንጂ የሌላ አይደለም፤ እርሱን እንጂ ሌላን እንዳትገዙ አዟል፤ ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኛወቹ ሰዎች አያውቁም።" {ሱራ ዩሱፍ 12:40}

ሁሉም ሃይማኖቶች መልካም ነገሮችን ያስተምራሉና አንዱን ብንከተል ምን ያመጣል የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። መልሱ ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ሁሉ የፍጡር አምልኮ የሆነውን ከሁሉም እጅግ ከባዱን ጥፋት ነው የሚያስተምሩት የሚል ይሆናል። የፍጡር አምልኮ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መሰረታዊ ዓላማ የሚፃረር በመሆኑ በሰው ልጅ ሊፈጸም የሚችል እጅግ የከፋና ከሁሉም በላይ ከባዱ ሀጡያት ነው። ቁርአን ውስጥ በግልጽ እንደተጠቀሰው ሁሉም የሰው ልጅ የተፈጠረው አሏህን ብቻ ለመገዛት ነው።

"ጅንንም ሰውንም አልፈጠርኳቸውም፤እኔን ሊገዙኝ ቢሆን እንጅ።" {ሱራ አል-ዛሪያት 51:56}

ስለ ሆነም የጣዖታዊነት ሥረ-መሰረት በሆነው ሽርክ ላይ ሆኖ የሞተ ሰው በወዲያኛው ሕይወት ዕድሉን ዘግቷል። አሏህ የመጨረሻ በሆነው ወሕዩ(Al Quran) ውስጥ እንዲህ ይላል፦

"አሏህ በርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፤ ከዚህ ውጭ ላለው ለሚሻ ሰው ይምራል።" {ሱራ አል-ማኢዳህ 4:48}

የሐሰተኛ ሐይማኖት ውጤቶች እጅግ አደገኛ ከሆኑ ዘንዳ ፣ እውነተኛው የአሏህ ሃይማኖት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊረዱትና ሊጨብጡት የሚቻል ሁለንተናዊ የሆነ ሃይማኖት ነው። አማኙ ጀነት እንዲገባ እንደ ጥምቀት እና አዳኝ ነው ብሎ በሰው ማመን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሊኖሩ አይችሉም። ራስን ለአሏህ ፈቃድ ማስገዛት በሚለው የኢስላም ማእከላዊ መርህ እና ትርጔሜ ላይ ነው። የኢስላም ሁለንተናዊነት መሠረት ያረፈው የሰው ልጅ አሏህ አንድና ከፍጡራኑ ፈጽፅሞ የተለየ መሆኑን ለመገንዘብ በቅቶ ራሱን ለአሏህ ፍቃድ ባስገዛ ጊዜ በአካልና በመንፈስ ሙስሊም ሆኖ ለጀነት ብቁ ይሆናል። በዚህ መሠረትም በማንኛውም ጊዜ በጣም ሩቅ በሆነ የአለም ክፍል የሚኖር ማንኛውም ሰው የፍጡር አምልኮን ውድቅ አድርጐ ወደ አንድ አሏህ በመመለስ ብቻ የአሏህ ሃይማኖት የሆነው የኢስላም ተከታይ ሙስሊም መሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አሏህን አውቆ መቀበልና ራስን ለርሱ ፈቃድ ማስገዛት፤ ጥሩውን ከመጥፎው ለይቶ መምረጥን የሚጠይቅና እንዲህ ዓይነቱ ምርጫም ሃላፊነትን እና ተጠያቂነትን የሚያመለክት ሞሆኑን ልብ ማለት ይገባል። የሰው ልጅ በምርጫው ውጤት ተጠያቂ ነው። ስለዚህ በጐ ሥራ በመሥራት እና ክፍውን ማስወገድ ያስፈልጋል። የመጨረሻው ከፍተኛ በጐ ተግባር ደግሞ አሏህን ብቻ መገዛት ሲሆን የመጨረሻው ከባድ እና ክፉ ሥራ ደግሞ ፍጡራንን ከአሏህ ጋር በማጋራት ወይም በአሏህ ፈንታ ሌላን ማምለክ ነው። ይህ እውነታ በመጨረሻው መለኮታዊ መልእክት ‘ወሕይ’ ውስጥ እንደሚከተለው ተገልጿል፦

"በእርግጥ! እነዚያ ያመኑ እና እነዚያ ይሁዳዊያኖችም ፣ ክርስቲያኖችም ፣ ሳቢያኖችም ከነርሱ መካከል በአሏህ እና በመጨረሻው ቀን ያመኑ መልካም ሥራም የሰሩ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳ አላቸው፤ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም ፣ እነርሱም አያዝኑም።" {ሱራ አል-በቀራ 2:62}
"እነሱም ተውራትንና ኢንጂልን፥ ከጌታቸው ወደነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባወቁና ባረጋገጡ ኖሮ ከበላያቸው እና ከእግሮቻቸው ስር በተመገቡ ነበር። ከነሱ መካከል ትክክለኛና ሚዛናዊዎች አሉ። ነገር ግን አብዛሃኛዎቹ ቅጥ ያለፈ ሃጢያትን ይሰራሉ።" {ሱራ አል-ማኢዳ 5:66}
Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top