ክፍል አራት

አሏህን ማወቅ

ሰዎች አሏህን ለመገዛት ሃላፊነት ይሰማቸው ዘንድ ሁሉም አሏህን የማወቅ ብቃት ሊኖረው ይገባል። የሰው ልጆች በሙሉ አሏህን የማወቅ ተፈጥሯዊ ግንዛቤ እውስጣቸው የተተከለ መሆኑንና አብረውት የተፈጠሩ መሠረታዊ ባህሪያቸው መሆኑን የመጨረሻው መለካታዊ መልእክት(ወሕይ) ያስተምራል።

ሱራ አል-አዕራፍ አንቀጽ 172-173 ውስጥ አሏህ አዳምን ሲፈጥር የአዳም ዝርዮች ወደ ቁሳዊው አለም ከመምጣታቸው በፊት ወደ መኖር እንዲመጡ አድርጐ «ጌታችሁ አይደለሁምን? በነፍሶቻቸው ላይ ባስመሰከራቸው ጊዜ ፣ ጌታችን ነህ፥መሰከርን አሉ፤» በማለት ቃልኪዳናቸውን የወሰደ መሆኑን ገልጿል። ከዚያም በመላው የሰው ልጅ እሱ ፈጣሪያቸውና ሊገዙት የሚገባ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ለምን እንዳደረገ አሏህ አብራርቷል። እንዲህ በማለት:- «በትንሳኤ ቀን ከዚህ ኪዳን ዘንጊዎች ነበርን እንዳትሉ፥» ይህም አንተ አሏህ አምላካችን ስለመሆንህ ምንም ሐሳብ አልነበረንም ፣ አንተን ብቻ መገዛት እንደነበረብን ማንም አልነገረንም እንዳይሉ ነው ማለት ነው። አሏህ ማብራሪያውን በመቀጠል እንዲህ ይላል:- «ጣዖታትን ያጋሩት ከኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን ብቻ ናቸው፤ እኛም ከነሱ በሗላ የኾን ዘሮች ነበርን ፤ አጥፊዎቹ በሠሩት ታጠፋናለህን እንዳትሉ አስመሰከርናችሁ።»

ስለዚህ እያንዳንዱን ሕፃን በአሏህ የማመን ተፈጥሮና ራእሱን ብቻ የማምለክ ዝንባሌ አብሮት ይወለዳል። ይህ ተፈጥሮ በአረብኛ «ፊጥራህ» ተብሎ ይጠራል። ሕፃኑ ለብቻው ቢተው ኖሮ በራሱ መንገድ አሏህን ይገዛ ነበር። ዳሩ ግን ሕፃናት ሁሉ በሚታዩም ሆነ በማይታዩ ነገሮች በአካባቢያቸው ተጽእኖ ሥር ይወድቃሉ። ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) «አሏህ ባሮቼን የፈጠርኴቸው በትክክለኛው ሃይማኖት ላይ ነው፤ ነገር ግን ሰይጣኖች ያጠሟቸዋል ብሏል ማለታቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እያንዳንዱ ሕፃን “በፊጥራህ” ሁኔታ ላይ ሆኖ ይወለዳል፤ ይሁዳዊ ፣ ክርስቲያን ወይም ዞራስተሪያን (እሳት አምላኪ) የሚያደርጉት ወላጆቹ ናቸው፤…..ብለዋል።» {ሐዲሱ በቡኻሪና በሙስሊም የተጠናቀረ ነው።}

ሕፃኑ ልክ አሏህ በተፈጥሮ ውስጥ ባኖራቸው ፊዚካል ሕግጋት ተገዥ እንደሆነ ሁሉ ነፍሱም አሏህ ጌታዋና ፈጣሪዋ ለመሆኑ እውነታ በተፈጥሮዋ ተገዥ ትሆናለች። ነገር ግን የሕፃኑ ወላጆች የራሳቸውን መንገድ እንዲከተል ለማድረግ የሚሞክሩ ሲሆን ሕፃኑ በመጀመሪያዎቹ የእድሜ ዘመኑ የወላጆቹን ፈቃድ ለመቇቇምም ሆነ ለመቃወም አቅም የለውም። በዚህ ደረጃ ላይ ሕፃኑ የሚከተለው ሃይማኖት የወግ ልማዱና የአስተዳደግ አካባቢው አይነት ነው። አሏህም በዚህ ደረጃ ላይ ሕፃኑን በዚህ ሃይማኖት ምክኒያት ተጠያቂ አያደርገውም።

ከልደት እስከ ሞት ባለው የሕዝቦች ሕይወት ውስጥ አንድ እውነተኛ አምላክ አሏህ ብቻ መሆኑ ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ምልክቶችና ታአምራት በምድር ውስጥና በራሳቸው ነፍስ ውስጥም ይገለጹላቸዋል። ሰዎች ከራሳቸው ጋር እውነተኛና ታማኞች ሆነው የሐሰት አማልክቶቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተው አሏህን ቢፈልጉ….መንገዱ ቀላል ይሆንላቸዋል። የአሏህን ምልክትና ተአምራቱን እምቢ ብለው ውድቅ ማድረጉን ቢቀጥሉበትና ፍጡራንን በመገዛቱ ተግባር ቢገፉ መንገዱ የበለጠ አስቸጋሪና የማይወጡት ይሆንባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ደቡብ አሜሪካ ብራዚል ውስጥ ባለው የአማዞን ደቡብ ምስራቃዊ ጫካ ውስጥ አንዱ ሗላቀር ጐሳ «እስክዎች» ለተባለና የፍጡራን ሁሉ አምላክ ለሚወክል ዋነኛ ጣዖት መኖሪያ አዲስ ጐጆ ሰሩ፤ በሚቀጥለው ቀን አንድ ወጣት አምላክ ተብየውን እጅ ለመንሳት ወደ ጐጆው ይገባል። ወጣቱ ፈጣሪውና ሲሳይ ሰጭው እንደሆነ ትምህርት በተሰው መሠረት ለጣዖቱ በመስገድ ላይ እያለ እርጅና የተጫጫነው በቆዳ በሽታ የተጠቃና በቁንጫ የተወረረ ውሻ ወደ ጐጆው ገባ። ወጣቱ ሰው ምን ያደርግ ይሆን ብሎ ሲጠብቅ ውሻው የሗላ እግሩን ያነሳና በጣዖቱ ላይ ሲሸና ይመለከታል። ስሜቱ ክፉኛ የተነካው ወጣት ውሻውን ከቤተ-መቅደሱ በቁጣ አባረረው። ቁጣው ሲበርድለት ግን ጣዖቱ የፍጥረት አለም ጌታ ሊሆን እንደማይችል ተገነዘበና አሏህ ሌላ ቦታ መሆን አለበት አለ። ወጣቱ አሁን ግንዛቤውን ተጠቅሞ አሏህን መፈለግ ወይም ታማኝነት በሌለው ሁኔታ የጐሳውን የተሳሳተ እምነት በጭፍኑ ተከትሎ የመጓዝ አማራጭ ቀርቦለታል። ነገሩ እንግዳ ሆኖ ቢታየውም የተከሰተው ነገር ለዚያ ወጣት ሰው ከአሏህ የሆነ ምልክት ነው። እርሱ ሲያመልክ የነበረው ነገር ውሸት መሆኑን የሚያሳይ መለኮታዊ መመሪያ እውስጡ ያቀፈ ምልክት ነው።

ቀደም ሲል እንደተገለፀው ለሁሉም ህዝቦችና ለሁሉም ጐሳዎች የሰው ልጅ በአሏህ ያለውን ተፈጥራዊ እምነትና እርሱን ብቻ የመገዛት አብሮት የተፈጠረ ዝንባሌውን ለማጠናከርና በአሏህ ተገልፀው በየእለቱ ከሚስተዋሉ መምልክቶች ውስጥ የሚንፀባረቀውን መለኮታዊ እውነታ ለማጐልበት ነቢያት ተልከዋል። በአብዛኛዎቹ ሁኔታ ከነቢዮቹ ትምህርቶች ውስጥ አብዙዋቹ የተበረዙ ቢሆንም ቅሉ ትክክለኛውንና የተሳሳተውን ለይቶ ማመልከት የሚያስችሉ በከፊል ተርፈዋል። ለአብነት ያህል የተውራት አስርቱ ትእዛዛት ወንጌሎች ውስጥ የሚገኙ የነርሱ ማጠናከሪያዎች የነፍስ ግድያ የስርቆትና የዝሙት ወንጀል መቅጫ ህጐችን በአብዛኞቹ ህብረተሰቦች ዘንድ መኖር መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህም በመነሳት እያንዳንዷ ነፍስ በአሏህ ማመንና ራስን ሙሉ በሙሉ ለአሏህ ፈቃድ ማስገዛት የሆነውን የእስልምና ሃይማኖትን መቀበል አስመልክታ ሃላፊነትና ግዴታ አለባት።

እሱ በመራን ትክክለኛው መንገድ ላይ እንዲያጽናናን ከሱ የሆነ በረከት ይሰጠን ዘንድ ሃያሉ አሏህን እንለምናለን፤ እሱ በእርግጥ ከሁሉም በላይ ቸርና ርህሩህ ነው። ምስጋና ለአለማት ጌታ ለአሏህ ይሁን። የአሏህ ሰላምና በረካ በነብዩ ሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በባልደረቦቻቸውና በቅንነት ፈለጋቸውን በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top