በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

በወጣቱ ተልዕኮ(አህመድ የሱፍ)

ሂጃብና ኒቃብ እንዲሁም ቡርቃ የብዙ አለመግባባትና የክርክር አርዕስቶች ከሆኑ ብዙ ዘመናትን አሳልፈዋል። ብዙ ሃገሮች እነዚህን ሃይማኖታዊ አልባሳት የከለከሉ ሲሆን አንዳንድ ሃገሮች ደግሞ የት የት ቦታ መለበስ እንዳለባቸው ገደብ አስቀምጠዋል።

በኒቃብ እና በቡርቃ ላይ ብዙ ክርክሮች የተደረጉ ሲሆን ኒቃብ ጭቆናና ኋላቀርነት ነው የሚሉ ትችቶችም ከተለያዩ ሰዎች ይሰነዘራል። እናም ዛሬ የምናየው እውነት ኒቃብ እና ቡርቃ የኋላቀርነት እና የጭቆና መገለጫዎች ናቸውን? የሚለውን ነው።

የእስልምና አለባበስ አይነቶች

"አንተ ነብይ ሆይ! ለሚስቶችህ ፣ ለሴት ልጆችህና ለምእመናን ሚስቶችም መከናነቢያቸውን በሙሉ አካላቸው ላይ ይለቁ ዘንድ ንገራቸው። ይህ እንዲታወቁና (ነፃና የተከበሩ ስለመሆናቸውና) በባለጌዎች እንዳይደፈሩ ለመሆኑ በጣም የቀረበ ነው። አሏህም አዛኝ መሃሪ ነው።" {አል-ቁርአን 33:59}

ከሙእሚን ሴቶች ጋር በተያያዘ ሶስት ኢስላማዊ የአለባበስ ስርአርቶች አሉ። 

  1. ሂጃብ_ ይህ በጣም የተለመደ ኢስላማዊ የአለባበስ ስርዓት ሲሆን ሙስሊም ሴቶች ሙሉ አካላቸውን በመሸፈን ፊታቸውንና እጃቸውን ብቻ የሚገልጡበት የአለባበስ ስርአት ነው። 
  2. ኒቃብ_ ይህ የአለባበስ ስርአት ልክ እንደ ሂጃብ ቢሆንም ሙስሊም ሴቶች አይናቸው ብቻ ሲቀር ሙሉ  አካላቸውን ይሸፋፍናሉ። 
  3. ብርቃ_ ይህ የአለባበስ ስርአት በጣም ያልተለመደ ሲሆን ሙስሊም ሴቶች አይናቸው ሳይቀር ሙሉ በሙሉ አካላቸውን የሚሸፋፍኑበት ስርአት ነው። 

እንደ አጠቃለይ በየትኛውም የአለም ክፍል የሚኖሩ ሙስሊም ሴቶች እራሳቸውን በሂጃብ ሲሸፋፍኑ፤ በተወሰኑ ሃገሮች የሚገኙ ሙስሊም ሴቶች ደግሞ እራሳቸውን በኒቃብ እና በቡርቃ ይሸፋፍናሉ።

ኒቃብና ቡርቃ ኢስላማዊ መሠረት ያላቸው ስለመሆኑ ምንም የሚያማያጠራጥር እና ጥያቄ የማያስነሳ ጉዳይ ነው። ቀደምት ሙስሊም ሴቶችም እራሳቸውን በነዚህ አልባሳት ይሸፋፍኑ እንደነበር ብዙ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ። ሆኖምግን ኒቃብና ቡርቃ ግዴታ ናቸው ወይንስ በፍላጐት የሚደረጉ ናቸው በሚለው ዙርያ ኡለማዎች ተለያይተዋል። ለዛምነው አንዳንድ ሙስሊም ሴቶች ሂጃብ ይለብሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ኒቃብን ወይም ቡርቃ የሚለብሱት።

የተለመዱ መሠረተ ቢስ ትችቶች

  • ኒቃብ መልበስ ጭቆና ነው 

ኒቃብ የሚለብሱ ሙስሊም ሴቶች ይህን የሚያደርጉት በራሳቸው ፋቃድና ውዴታ ሲሆን አንዱ የአምልኮት ተግባር እንደሆነ ፣ ነፃነት እና ከሃራም ነገር መጠበቂያም እንደሆነ በማመን ጭምር ነው። ትልቁ ጭቆና ግን ኒቃብ መልበስ ሳይሆን ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ መከልከል ነው።

ውዷ እህቴ ሆይ! ሂጃብና ኒቃብ ጭቆና ነው የሚሉ ሰዎች ለአንች ተጨንቀው እንዳይመስልሽ ኢስላምን የሚያጠቁበት፤ የእምነቱን ስርአት የሚያበላሹበትን መንገድ በአንች በኩል እየፈለጉ ቢሆን እንጅ። ውድ እህቴ ሆይ! ኒቃብ መልበስ ጭቆናነው ብለው የሚለፍፍ ሰዎች የሐራም ነገሮችን እና የዝሙት ባህርን ሊያስቀዝፉሽ መሆኑን እወቂ!!!

  • ኒቃብ መልበስ ኋላቀርነት ነው 

ኒቃብ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የፋሽን ልብሶች አካል አይደለም። ይልቁንም ጊዜና ቦታ የማይገድበው ሃይማኖታዊ ልብስና የአምልኮት ተግባር ነው። ይህ ደግሞ መቼም ቢሆን ጊዜ የማይሽረው ጉዳይ ነው።

ውዷ እህቴ ሰዎች ሂጃብ ፣ ጅልባብ ፣ ኒቃብ ፣ ቡርቃ መልበስ ኋላቀርነት ነው ስላሉሽ ዘመናዊ ሴት ለመባል ብለሽ ሂጃብሽን አታውልቂ። ሂጃብሽን እና ኒቃብሽን በማውለቅ የአሏህን ህግጋት ጥሰሽ እንዴት ለማይረባ የሰው ልጅ ትችት እጅ ትሰጫለሽ? እራስሽንም ለስላሳ ሙስሊም ብለሽ አትጥሪ! ይህን በማለትሽ ብዙ ሃራም ነገሮችን እንድትሰሪ ትገፋፊያለሽና። ለዛም ነው ዛሬ ላይ የሂጃብንና የኒቃብን ትርጉም ሳይረዱ ፀጉራቸውን ብቻ ሸፍነው ሱሪ የሚለብሱ እንዲሁም ትንሽ ሰፋ ያለች ልብስ ካላቸው ያስጠብቧትና የአካል ቅርፃቸው እንዲታይላቸው የሚያደርጉ ሙስሊሞች እየተፈጠሩ ያሉት። ትዳር ፈልገሽ ከሆነ ቶሎ አግቢ እንጅ በዚህ ስም አምላክሽን አሏህ አታምፅ። ሂጃብሽንም ሆነ ኒቃብሽን በትክክል በመልበስሽ ሙስሊሙ ኡማ ባንች ይኮራል። ላንችም ያለውን ውዴታና ፍቅር አትዘንጊ። ከዚህም በላይ አሏህ ላንች ያለውን ውዴታ አስታውሽ።

ሂጃብሽንና ኒቃብሽን በትክክል በመልበስሽ የኢስላም አምባሳደር ስትሆኝ፤ የታላቅነትን ፣ የነፃነትን እና የንፁህነትን አክሊል ትጎናፀፊያለሽ።

  • የወንዶችን የበላይነት ማሳያ ነው 

ኒቃብና ቡርቃ መልበስ በምንም ተአምር የሴቶችን የበታችነት አያመላክትም። በራሳቸው ፍቃድ ከሚለብሱ ሙስሊሞች እውነታጋ ይቃረናል።

  • ኒቃብ መልበስ ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠርም ሆነ እውቀትን ለመሻት መሠናክል ነው።

ኒቃብ የለበሰች ሴት ኒቃብ በመልበሷ ማህበራዊ ትስስር ከመፍጠርም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከመሳተፍ የሚያግዳት ነገር አይኖርም። ያ ጉዳይ ሃራም እስካልሆነ ድረስ ወይም ወደሃራም ነገር ነገር የሚያመራት እስካልሆናት ድረስ ማለት ነው። እንዲሁም ኒቃብ መልበስ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ከማድረግም ሆነ በከፍተኛ የትምህርት ተቇማት እውቀትን ከመሻት የሚያግዳት ነገር የለም።

ኒቃብ የሚለብሱ ሆነው በጣም የተማሩ፤ ስራቸውን በብቃት የሚሰሩ ሴቶች በርካታ ናቸው። እናታችን አኢሻ(ረ.ዐ) እንደ ምሳሌ ብናነሳ አኢሻ(ረ.ዐ) ኒቃብ(ብርቃ) የምትለብስ ታላቅ አሊም ነበረች። ሆኖምግን እውቅ የሆነች አሊም ከመሆንና ወንዶችንና ሴቶችን ሰብስባ ከማስተማር አላገዳትም ነበር። 

  • የማህበረሰቡን ወግ ልማድ ይፃረራል

የማህበረሰቡ ወግ ልማድ በአብዛሃኛው ሰው ተቀባይነት ያለው እስከሆነ ድረስ ምንም ነገር አይፃረርም። ኒቃብ ቅዱስነት እንጅ ወንጀል አይደለምና። የማህበረሰባችንን ባህል ወግ ልማድም የሚፃረረው እራስን በኒቃብ መሸፋፈን ሳይሆን ሃፍረተገላን መገላለጥ ነው።

ውድ እህቴ ሆይ! ከላይ የጠቀስኴቸው መሠረተቢስ ትችቶች ከሃዲዎችና ሙናፊቆች በሙስሊም ሴቶች ስም የራሳቸውን ፓለቲካዊ አጀንዳና በኢስላም ላይ ያላቸውን ጥላቻ የሚነዙባቸው የድንቁርና ሃሳቦች እንጅ ሌላ አይደሉም። መነኩሴዎች ፣ የቡድሂስቶችና የሂንዱ እምነት ተከታዮች እራሳቸውን በመሸፋፈናቸው እንደ ቅዱስ ከመታየታቸው በላይ ይከበራሉ። ሙስሊሞች ሲሆኑ ግን እንደ አሸባሪና የደህንነት ስጋት ተደርገው ይቆጠራሉ። ለምን ይሆን?

ኒቃብ ጭቆና አይደለም የማህበረሰቡን ወግ ልማድ የሚፃረር የደህንነት ስጋትም አይደለም። ይልቁንም የሙስሊም ሴቶች ፍላጎት ከመሆኑ በላይ የበለጠ ወደ ጌታቸው የሚቃረቡበት ነው።

አንዲትን ሴት አስገድዶ ኒቃብ ማስለበስ ጭቆና እንደሆነው ሁሉ በፍላጎቷ ኒቃብ የለበሰችን ሴት አስገድዶ ማስወለቅ ጭቆና እና ግፍ አይደለምን?

ውድ እህቴ ሆይ! አሏህ መልካም ወደሆነ ነገር እንዲመራሽ የምትፈልጊ ከሆነ ሂጃብሽንና ኒቃብሽን አሏህ ባዘዘሽ መሠረት ልበሽ። ራስሽንም ለትዕዛዙ ተገዥ አድርጊ። ማማርሽም ሆነ ማጌጥሽ በሂጃብሽ ላይ ይሁን።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top