አሏህ በፃፈልህ ተብቃቃ ከሁሉም ሰዎች በፀጋ በላጭ ትሆናለህና

ይህ ርዕስ በተወሰነ መልኩ ባለፉት ምዕራፎች ውስጥ ተወድሷል። ሆኖም ግን የበለጠ ግልፅ እንዲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ ቀለል ባለ መልኩ እደግመዋለሁ። አሏህ በሰጠህ ተክለሰውነት ፣ አቋም ፣ ገንዘብ ፣ ልጅ ፣ ቤትና ችሎታ መብቃቃት ይኖርብሃል። የቁርአንም መልእክት ከዚህ የተለየ አይደለም።

«የሰጠሁህንም ያዝ ፤ ከአመስጋኞችም ሁን።»

{አል-ቁርአን 7:144}

ቀደምቶቹ የኢስላም ምሁራን እና አብዛኞቹ የመጀመሪያው የኢስላም ትውልድ ሰዎች ድሆች ነበሩ። ብዙ ገንዘብ ፣ ውብ ቤቶች ፣ መሳፈሪያዎችና ጥበቃዎች አልነበራቸውም።

ሆኖም ግን ህይወትን በሃብት ሞልተው ፤ ራሳቸውንና የሰው ልጆችን በሙሉ አስደስተው አለፉ። ምክንያቱም አሏህ የለገሳቸውን ፀጋ በትክክለኛው ቦታ ላይ ስላዋሉ፤ እድሜያቸውን ፣ ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን አሏህ ባረከላቸው።

ከነዚህ በተቃራኒ ደግሞ አሏህ ገንዘብ ፣ ልጆችና ብዙ ፀጋዎችን የሰጣቸው ሰዎችም ነበሩ። ሆኖም ግን እነዚያ ፀጋዎች ለመጥፋታቸው እና ለመከፋታቸው ምክኒያት ሆነው ህይወታቸውን አደፈረሱባቸው።

ምክኒያቱም ከተስተካከለችው ተፈጥሮ እና ከእውነተኛው የህይወት ጎዳና ስለራቁ ነው። ይህም ቁሳቁሶች ስለበዙ ሰው ደስተኛ ሊሆን እንደማይችል የሚያመላክት ነው። ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቶችን ይዘው በአስተሳሰባቸውና በስራቸው ከተራው ሰው ያልተለዩ ሆነው የሚኖሩም ብዙ ናቸው።

በአንፃሩ ደግሞ ውስን ዕውቀት ኖሯቸው ሌሎችን ሲጠቅሙ ሲያቀኑ የሚስተዋሉም አሉ።

ደስታን የምትፈልግ ከሆነ አሏህ የሰጠህን አፈጣጠር ወደህ ተቀበለው። ቤተሰባዊ ሁኔታህን ፣ ድምፅህን ፣ የግንዛቤ ደረጃህንና ገቢህንም አትናቅ።

እንዲሁም አንዳንድ ምሁራን ካለህ በታችም ቢሆን ወደህ መቀበል እንዳለብህ ይመክራሉ። ዱንያዊ ድርሻቸውን ትተው መኖርን ከመረጡ ኮከቦቹን ልዘርዝርልህ።

አጣዕ ቢን አቢ ረባህ በዘመኑ ታላቅ ምሁር የነበረ ሲሆን ጥቁር ፣ ባሪያ ፣ ፀጉረ ከርዳዳ ፣ አካለ ስንኩል ነበር። አል አሕናፍ ቢን ቀይስ የመላው አረቦች ታጋሽ የነበረ ሲሆን ሰውነቱ ቀጫጫ ፣ ወገበ ጎባጣ ፣ እግረ ደጋን ፣ አካለ ደካማም ነበር።

አል አዕመሽ በዘመኑ ምርጥ የሐዲስ አዋቂ ሲሆን ባሪያ ፣ ዓይነ ደካማ ፣ ድሃ ፣ ልብሱ የተቀደደ ፣ ገፅታውና ቤቱ የከሰሙ ነበር።

እንዲሁም የተከበሩና ከሁሉም የሰው ልጆች በላጭና የላቁ የነበሩት የአሏህ መልእክተኞች ሁላቸውም ፍየል ጠብቀዋል ፤ ዳውድ (ሰ.ዐ.ወ) የብረት ቀጥቃጭ ፣ ዘከሪያ አናፂ ኢድሪስም ልብስ ሰፊ ነበሩ።

ስለዚህ ደረጃህ የሚለካው ባለህ ችሎታ ፣ በመልካም ሥራህ ፣ ለሰዎች በምታበረክተው ጠቀሜታና በምታሳየው መልካም ስነ-ምግባር ነው። በመሆኑም ስላመለጠህ ውበት ፣ ገንዘብም ሆነ ልጆች አትተክዝ። አሏህ በሰጠህም ተብቃቅተህ በውዴታ ተቀበል።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top