በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

በወጣቱ ተልዕኮ(አህመድ የሱፍ)

በእርግጥ ሸይጧን ላናንተ ጠላት ነው። እናም ጠላት አድርጋችሁ ያዙት። ተከታዮቹን የሚጣራው ከዕሳት ጏደች እንዲሆኑ ብቻ ነው። {አል-ቁርአን 35:6}

የኢብሊስ(የሸይጧን) ታሪክ በጨረፍታ

ሸይጧን ጭስ አልባ ከሆነ እሳት የተፈጠረ ሲሆን መላኢካ ባይሆንም ለአሏህ በነበረው ታዛዥነት ግን በጀነት ከነሱ መካከል ነበር። አሏህ(ሱ.ወ.ተ) አደም(ዐ.ሰ) በፈጠረ ጊዜ በጀነት ያሉ ሁሉ ከአደም(ዐ.ሰ) ፊት ለፊት ይሰግዱ ዘንድ አዘዛቸው። ነገር ግን ሸይጧን በእብሪተኝነት እና በኩራት እንዲህ በማለት አሻፈረኝ አለ

"እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ። እኔን ከእሳት ፈጠርከኝ እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።" {አል-ቁርአን 7:12}

አሏህም ሸይጧንን ረግሞት ከጀነት አባረረው። ሆኖም ግን ሰዎችን የሚያጠምበትን እድል ይሰጠው ዘንድ ጠየቀ፤ አሏህም የጠየቀውን ነገር ሰጠው።

"ስለአጠመምከኝ ለእነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ አለ። ከዚያም ከስተፊቶቻቸው ፣ ከኋላቸው ፣ ከቀኛቸውና ከግራቸው በኩል በእርግጥ እመጣባቸዋለሁ። አብዛሃኛዎቹንም አመስጋኝ ሆነው አታገኛቸውም አለ።" {አል-ቁርአን 7:16-17})

የሸይጧን ወጥመዶች

  • የአምላክ አንድነትን የማስካድ ስልት

እንደሚታወቀው የእስልምና ሃይማኖት መሠረቱ ተውሂድ ወይም አሃዳዊነት ነው። ይህም አሏህ የዚህ ዩኒቨርስ ፈጣሪና አስተናባሪ ፣ ሰጭ ፣ ነሽ መሆኑን እንዲሁም የአምልኮት ተግባራት በሙሉ ለአሏህ ብቻ ማድረግንና ልዩና ውብ የሆኑ ስሞችና ባህሪያቶች እንዳሉት ማረጋገጥ እና ማመን ነው። ከዚህ በተቃራኒ ከአሏህ ዘንድ ከበደሎች ሁሉ የከፋ በደል ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል ብሎ ማለት በአሏህ ላይ ማጋራት ነው። ለምሳሌ፦

  • የአምልኮት ተግባራትን ከአሏህ ውጭ ላሉ ነገራት ማድረግ(ከአሏህ ውጭ የሆኑ ነገሮችን መለመን ፣ ለነሱ ማረድ ፣ መስገድ ፣ በነሱ መመካት ወ.ዘ.ተ)
  • የአሏህን ስምና ባህርያት አለመቀበል ወይም በፍጡራኖቹ መመሰል ትርጉማቸውን መቀየር ወ.ዘ.ተ
  • አሏህ ልጅና እናት አለው ወይም ደግሞ ሌላ ባላንጣ አለው ብሎ ማመን

የሸይጧን ዋና ግቡ የሰው ልጆችን ማጥመም ሲሆን ነገርግን ሸይጧን ግልፅ የሆነ ክህደቶችን እንዲፈፅሙ ማድረግ ካልቻለ ሌላ አማራጮችን ይጠቀማል። ለምሳሌ የሩቅን አዋቂ አሸናፊ ጥበበኛ አሏህ ብቻ ሆኖያለ ሰዎች በጥንቆላ ፣ በድግምት ፣ በኮኮብ ቆጠራ ወ.ዘ.ተ እንዲያምኑ ለማድረግ ይሞክራል።

  • በዲነል ኢስላም መሠረት የሌላቸውን ነገሮች እንድንፈላሰፍና ቢድአ ነገሮችን እንድንሰራ የማድረግ ስልት

ሌላኛው የሸይጧን ሴራ ሰዎች የተሳሳተ አቂዳ በኢስላም እንዲይዙ ማድረግ ሲሆን ይህም አሏህ(ሱ.ወ.ተ) እና መልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ያልደነገጉትን ነገር መስራት ነው። በሌላ አገላለፅ የዕምነቱን ክፍል የሚጣረሱ ነገሮችን ከራስ ፍላፍልስፍናና ስሜት በመነሳት ያልነበሩ ነገሮች የዕምነቱ ክፍልና የአዕምኮት ተግባራት አድርጐ መያዝን ያስከትላል።

በእርግጥ እነዚህ የቢድአ ሰዎች ኢስላም በራሱ ሙሉ እንዳልሆነ በማመን ወይም መለኮታዊ ራዕይ በትክክል እንዳልተገለፀ በማመን ወደ ቢድአ ነገራቶች ይዘምታሉ። ይህ ግን ግልፅ የሆነ ክህደት ነው። ምክኒያቱም አሏህ የገለፀውን ነገር መካድ ነውና። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱ አል-ማኢዳ አንቀፅ 3 ላይ እንዲህ ይላል

"ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ፀጋየንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ ለናንተም ከሃይማኖት በኩል ኢስላምን መረጥኩ።" {አል-ቁርአን 5:3}
  • ግዴታ የሆኑ ስራዎችን ችላ የማስባል ስልት

አሏሁ አዘወጀል በቁርአኑ በሱረቱል ማኢዳ አንቀፅ 91 ላይ እንዲህ ይላል

"ሸይጧንም የሚፈልገው አሏህን ከማውሳትና ከሶላት ሊያግዳችሁ ብቻ ነው።" {አል-ቁርአን 5:91}

አሏህ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተወሰኑ ስራዎችን ግዴታ ያደረገ ሲሆን ለጊዜው አምስት አውቃ ሶላቶችን መጥቀስ በቂ ነው። ሸይጧንም ብዙ ሃጢያቶችን እንድንሰራ በመሻት ሶላቶቻችነን ችላ እንድንልና ብሎም ከሶላት እንድንርቅ ለማድረግ ይሞክራል።

"እነሆ ሶላት ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ከልካይ ናት።" {አል-ቁርአን 29:45}
  • ቀስበቀስ የማጭበርበር ስልት

እንዴት የጣዖት አምልኮት እንደተጀመረ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የገለፁልን ሲሆን ይህም በሸይጧን ትዕግስትና የቀስበቀስ የማጭበርበር ዘዴ ነበር። በነብዩሏህ ኑህ(ዐ.ሰ) ዘመን የነበሩ ሷሊህ ሰዎች ከሞቱ ብኋላ ሸይጧን መጣና ደግነታቸውን ለማስታወስና ለክብራቸው ሃውልት በዙርያችሁ ይቁምላቸው ሲል ገፋፋቸው። ያ ትውልድ ባለፈ ጊዜ ሰዎች ሃውልቶቹ ለምን እንደቆሙ ረሱ። ሸይጧንም የአባቶቻችሁ አባቶች ያመልኴቸው ነበር፤ በነርሱም ምክኒያት ዝናብ ይጥል የነበረው ሲል አጭበረበራቸው። ሰዎቹም እነዛን ሃውልቶች ማምለክ ጀመሩ።

ይህ ቀስበቀስ የማጭበርበር ዘዴ በብዙ መንገድ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ሰዎች ዝሙት ይፈፅሙ ዘንድ አጅነብይ የሆነችን ሴት(ወንድ) እንድንመለከት በማድረግ ይጀምርና ስለሷ እንድናስብ ብሎም ፈገግ እያልን እንድንስቅ እንድንጫወት ይጋብዘናል። በመጨረሻም ብቻችነን ተገናኝተን እንድናወራ በመጋበዝ የከፋ ሃጢያት ላይ ይጥለናል።

በተመሳሳይ መልኩ ሱና ሶላቶቻችነን እንድንተው በተለያዩ በማይረቡ ምክኒያቶች ያሳምነንና ከዛም ግዴታ የሆኑትን ሶላቶች እንዳንሰግድ ያዳክመናል። ይህን ተከትሎም ግዴታ ሶላቶቻችነን እስከመተው ወይም ችላ እሰከማለት እንደርሳለን።

  • መጥፎ ተግባራትን የማስዋብ ስልት

ሸይጧን ሃጢያት ነገሮችን አስውቦ ለሰዎች ያቀርባል። አደምና ሐዋን በዛች ከበደለኞች በምታደርጋቸው ዛፍ እንዴት እንዳታለላቸው ማስታወስ በቂ ነው። ሸይጧን ለአደም(ዐ.ሰ) እንዲህ ሲል ሹክ አለው

"አደም ሆይ! ህያው(ዘላለማዊ) ወደ ምታደርግህ ዛፍና ዘላለማዊ ወደሆነው ግዛት አላመላክትህምን? አለው።" {አል-ቁርአን 20:120}

ብዙ ሐላል የነበሩ ምግቦች በአደም(ዐ.ሰ) ዙርያ ቢኖርም ሸይጧን ግን ከዛች ሐራም ከሆነች ዛፍ እንዲመገብ ገፋፋው።

"ይጠሉት የነበሩትንም ነገር ሸይጧን አሳመረላቸው።" {አል-ቁርአን 6:43}

ሸይጧንን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን

በመጀመሪያ ደረጃ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ሸይጧን የኛ ግልፅ ጠላት መሆኑን መገንዘብና ጠላት አድርገን መያዝ ነው። የጠላታችነን ማንነት ካወቅን ያኔ እሱን ማሸነፍ እንችላለን። የሸይጧን ሃይል ወይም አቅም ያለው የማታለል ብቃቱ ላይ ነው። ሆኖም እራሳችነን ከሸይጧን ተንኮል ለመጠበቅ የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ስልቶች እንዲሁም የተለያዩ ዘዴዎቹን መረዳት ይኖርብናል።

  • የአሏህ እርዳታን መሻት

የአሏህን ጥበቃና ከለላ መለመን እንዲሁም በሱ ላይ መመካት ሸይጧንን ማሸነፊያ አይነተኛ መሳሪያ ነው። ሱረቱል አል- ፈለቅና ሱረቱ ናስ አዘውትረን በመቅራት ከሸይጧን ተንኮል በአሏህ መጠበቅ እንችላለን። ሆኖም ግን በህይወት እስካለን ድረስ ሸይጧን መቼም ቢሆን እጅ አይሰጥም፤ እኛን ለማጥመም ደከመኝ ሰለቸኝ አይልም። ስለዚህ ዘወትር አሏህ ይመራንና ይጠብቀን ዘንድ እሱን መለመን ይኖርብናል።

  • የአሏህን ምህረት መለመን

በሸይጧን ሴራ ከተሸነፍን በአሏህ እዝነትና ቸርነት ህይወታችነን የምናስተካክልበት ሌላ እድል አለን።

"የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ሸይጧን ለሃያሉ አሏህ(ሱ.ወ.ተ) እንዲህ አለ "አምላክ ሆይ በልቅናህ ይሁንብኝ ባሮችህን ለማጥመም መሞከሬን እቀጥላለሁ ነፍሳቸው በአካላቸው እስካለች ድረስ" አለ። ጌታ(አሏህ) "በልቅናየ ይሁንብኝ ምህረቴን እሰከለመኑኝ ድረስ እነሱን መማር እቀጥላለሁ አለ" ብለዋል። {አህመድ}

ተውበት ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ቅንና እውነተኛ እንዲሁም ከልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ያን ወንጀል ወይም ሃጢያት ደግሞ ላለመፈፀም ማሰብንና ቆራጥ ውሳኔን መወሰን ይጠይቃል።

  • ከወንጀል ተግባራቶች መራቅ

አሏህ(ሱ.ወ.ተ) ከዛች ዛፍ በከለከለው ጊዜ ከዚህ ዛፍ አትብላ አይደለም ያለው። ይልቁንም በሱረቱል በቀራ አንቀፅ 32 ላይ እንደገለፀው “ወደዚህ ዛፍ አትቅረቡ” ሲል ነበር የከለከለው። ስለዚህ ወንጀል እንድንፈፅም ከመሚመሩን ነገሮች በሙሉ እራሳችንን ማራቅ ይኖርብናል ማለት ነው።

  • መልካም ደጃ ይኑረን

እኛ ወጣቶች እንደመሆናችን መጠን ብዙ ጊዜ በጏደኞቻችን ተፅዕኖ ስር እንወድቃለን። ሆኖም ደኞቻችን መጥፎ ከሆኑ የኛም ማንነት የጏደኛችነን ማንነት ነው ሊመስል የሚችለው። ስለዚህ መጥፎ ደኛ አሏህን ወደ ማመፅ እንጅ ወደ ኸይር ነገር ስለማይመራ የኛ ምርጫ አሏህን የሚታዘዝ ፣ የከለከለውን ነገር የሚከለከል ፣ መልካም ነገር እንድንሰራ የሚያበረታታን መሆን ይኖርበታል።

"ከሰይጣንም ጉትጎታ ቢያገኝህ በአሏህ ተጠበቅ። እርሱ ሰሚም አዋቂም ነውና።" {አል-ቁርአን 7:200}
  • መልካም ስራዎችን እንስራ

በመልካም ስራዎች ግዜያችነን ካሳለፍን ለመጥፎ ስራዎች ቦታ አይኖረንም። እንዲሁም በሸይጧን ሴራ በቀላሉ ከመሸነፍ እንድናለን።

አሏህ ሃጢያቶቻችነን ይምረን ዘንድና ከሸይጧን ወጥመዶች ይጠብቀን ዘንድ ውብ በሆኑ ስምና ባህሪያቶቹ እለምነዋለሁ።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top