በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
ቁርአን ግልፅ የሆነ ልንስራራበት እና ልናስተነትንበት የሚገባ ሲሆን ለሰው ልጆች በረካ የሆነ መለኮታዊ መጽሐፍ ነው። አሏህ በቁርአኑ እንዲህ ይላል:-
"ይህንን ቁርአን በተራራ ላይ ባወረድነው ኖሮ ከአሏህ ፍራቻ የተነሳ ተዋራጅ ተሰንጣቂ ሆኖ ባየኸው ነበር። ይህችንም ምሳሌ ያስተነትኑ ዘንድ ለሰዎች እንገልፃለን።" {አልቁርአን 59:21}
መሬት ሚዛኑዋን እንድትጠብቅ አጥብቆ በያዛት እና ግርማሞገስን በተላበሰው ተራራ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንኴ ውጤቱ ይህ ነው።
- እውነት የአሏህን ንግግር በመስማታችን ልብችን ይርዳል?
- እንደው በቁርአንስ ታንፀን ያደግን ስንቶቻችን እንሆን?
- የአሏህ ቅጣት አሳማሚነት ተሰምቷት የምታነባ ዐይን ያለችን ስንቶቻችን ነን? እኛ የሰው ልጆች በዚህ ምሳሌ ልናስተነትን ይገባል።
አሏህ(ሱ.ወ.ተ) ቁርአንን ታዓምር ፣ በረካ ፣ አዳኝ ፣ አስታዋሽ በሚሉ ባህሪያት ጠርቶታል። በሙስሊም እንደተዘገበው ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል: “ከአሏህ ቤት የአሏህን መጽሐፍ ለመቅራትና በአንድላይ ሊያጠኑት የሚሰባሰቡ ሰዎች የሉም የመንፈስ እርጋታና ምህረት አካቧቸው ፣ መላኢካዎች ከበዋቸውና አሏህ ከነሱ ጋር ሆኖ ቢሆን እንጂ ብለዋል።”
ምልክትና ተአምር
ቁርአን በራሱ ተአምር የሆነ የአሏህ ንግግር መሆኑን እናውቃለን። ይህ እምነት የእምነታችነን መሠረታዊ ክፍል ይፈጥርልናል። ከዚህ በተጨማሪም አሏህ(ሱ.ወ.ተ) በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል:-
"በእርግጥ በሰማያትና በምድር ፍጥረት ውስጥ እንዲሁም በሌሊትና በቀን መፈራረቅ ውስጥ ለሚረዱ ሰዎች ምልክቶች አሏቸው።" {አል-ቁርአን 3:190}
ቁርአን ከኛ በላይ ባለው ሰማይ ፣ ከስራችን ባለው መሬት ፣ በዙርያችን ባሉ ዛፎች ፣ አእዋፍት ፣ ሸለቆዎች ፣ ወራጅ ውሃዎች ፣ ባህሮች እንዲሁም በፀሀይ ፣ በጨረቃ ፣ በዝናብ ፣ በከዋክብት ወ.ዘ.ተ እንድናስተነትን በሚያደርጉ አያቶች(ምልክቶች) የተሞላ ነው። ቁርአን በዙርያችን ባሉ ነገሮች ትልቅም ሆነ ትንሽ እንድናስተነትን ጌታችንን እንድናውቅና እንድናልቀው ይረዳናል።
የቁርአን ተአምር የሚገኘው በመመሪያነቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቁርአን ከ1000 ዓመታት በላይ ያልተከለሰ ያልተበረዘ እንዲሁም ያልተቀየረ ነው።
ቁርአን የሰው ልጅ የፈጠራ ስራ ነው ብለው የሚያስቡትን በማስተባበል አሏህ የሰው ልጆችን እንዲህ ሲል ይፈትናቸዋል:-
"እውነተኞች ከሆኑ ተመሳሳይ የሆነች (አያት) እንዲያመጡ አድርጋቸው።" {አል-ቁርአን 52:34}
አንድም የሰው ልጅ ቁርአንን ወይም አያቶቹን(አንቀፆቹን) የሚመስል ምንም ነገር ማምጣት ወይም መፍጠር አልቻሉም። እንዲያውም እንኴ ወደ አሏህ (ሱ.ወ.ተ) ቃል የተጠጋ ድንቅና ያሸበረቀ ያማረ ስድንባብ አይደለም በአረብኛ በሌላ ቇንቇ እንኴ የፈጠረም ሆነ ያመጣ አንድም የለም።
የቁርአን የሰዋሰው ትክክለኛነት የቅላፄውና የድምፀ ልሳኑ ውበት እስከ ትንሳኤው ቀን ዘላቂ ሲሆን ከቁርአን ጋር የሚመሳሰልም ሆነ የሚጠጋ የቋንቋ ተዐምር አልተፈጠረም አይፈጠርም።
"ቁርአንን አያስተነትኑትምን? ከአሏህ ውጭ የሆነ ቢሆን ኖሮ ብዙ ቅራኔዎችን እርስበርስ የሚጋጩ ነገሮችን ባገኙበት ነበር።" {አል-ቁርአን 4:82}
ከሁሉም በላይ ከገፅ እስከ ገፅ የሚነበብ በሰው ልጆች አእምሮ እያንዳንዱ ቃል ተሸምድዶ የተቀመጠ ብቸኛው መጽሐፍ ነው።
"በእርግጥ ዚክሩን(ቁርአንን) ያወረድ ነው እኛነን። በእርግጥም እንጠብቀዋለን።" {አል-ቁርአን 15:9}
ቁርአን ከ1400 ዓመታት በፊት የተገለፀ ሲሆን የቁርአንም መልዕክት ታማኝና ታዛዥ በሆኑ የአሏህ ባሪያዎች እየተማሩትና እያስተማሩት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ ላይ ደርሷል። በቡኻሪ እንደተዘገበው የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ከእናንተ መካከል በላጩ ቁርአንን ተምሮ ያስተማረ ነው ብለዋል።
እናም ውድ ሙስሊም እህት ወንድሞቼ ጊዜው ሳይጨልምብን የሞትን ቅጣት ከመቅመሳችን በፊት ወደ ቁርአን ወደ ሱና እንመለስ። አሏህ (ሱ.ወ.ተ) የሂወታቸው መመሪያ ቁርአንና የሐዲስን ካደረጉት እንዲሁም ቁርአንን ለማወቅም ሆነ ለማሳዎቅ ከሚጣጣሩት መካከል ያድርገን። አሚን!!!