እስልምና ለንፅህና ትልቅ ቦታ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ምክኒት የኢማን ወይም የእምነት ግማሽ እንደሆነ በሐዲስ ተገልፃለ፡፡ ንፅህና የውስጥ (መንፈሳዊ) እና የውጭ (አካላዊ) ተብሎ ይከፈላል፡፡ እንዲሁም የውጭ ንፅህና ከፊል ትጥበት (ውዱእ) እና ሙሉ ትጥበት (ጉሱል) ተብሎ ይከፈላል፡፡ ለዛሬው የምናየው ውጫዊ ንፅህናን ይሆናል፡፡

ውዱእ

ውዱእ እንደ ሽንት ፣ ዓይነ ምድር ፣ በዓይነ ምድር መውጫ በኩል ከሆድ የሚወጣ አየር ፣ ጥልቅ እንቅልፍና የግመል ሥጋ መብላት ያለ ትጥበቱን ግዴታ የሚያደርግ መለስተኛ ክስተት (አል-ሐደሦ አል-አስገር) ሲከሰት የሚፈፀም የግዴታ ጦሃራ (ትጥበት) ነው።

  • የውዱእ ትሩፋት አስመልክቶ የሚከተሉት ሐዲሶች ተላልፈዋል

ከዑመር(ረ.ዐ) በተላለፈው ትረካ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል «ከናንተ መካከል ውዱእ አድርጎ ውዱኡን ያሟላና ከዚያም ‘አሽሀዱ አላኢላሀ ኢለሏህ ዋህደሁ ላሸሪከ ለሁ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ አሏሁመ አጅዓልኒ ሚነተዋቢን ወጅአልኒ ሚነል ሙተጦሂሪን’

ከአሏህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለና እሱ ብቸኛውና ሸሪክ የሌለው መሆኑን እመሰክራለሁ ሙሐመድ አገልጋዩና መልእክተኛው መሆናቸውንም እመሰክራለሁ አሏህ ሆይ ከሃጢያታቸው ተፀፅተው ወደ አንተ ከሚመለሱት አድርገኝ በብዙ ከሚጥራሩት ከሚፅዳዱትም አድርገኝ} ያለ ሰው ስምንቱ የጀነት መግቢያ በሮች ተከፍተውለት በፈለገው በር ይገባል።

ከዑሥማን (ረ.ዐ) በተላለፈው ትረካ ደግሞ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «ውዱእ አድርጐ ውዱኡን ያሳመረ ሰው ሃጢአቶቹ ከጥፍሮቹ ሥር እንኳ ሳይቀር ከአካላቱ ይወጣሉ።»

ከዓሊይ ብን አቢ ጧሊብ በተላለፈው መሠረት ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በብርድና በመሳሰሉት እየከበደው ውዱእን አሟልቶ መፈጸም ፤ እግሮችን ወደ መስጊዶች ማራመድና ከአንዱ ሶላት በኋላ ሌላውን ለመስገድ መጠባበቅ ኸጢያቶችን በሚገባ ያጥባል።»

የውዱእ አደራረግ ሁኔታ

  • በአንደበት ሳይናገሩ ውዱእ ለማድረግ በልብ ቁርጠኛ ውሳኔ(ኒያ) ማድረግ በምላስ ኒያን መናገር ያላስፈለገው ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) በውዱአቸው ፣ በሶላታቸውም ሆነ በማናቸውም የአምልኮተ አሏህ(ዒባዳ) ክንዋኔዎቻቸው ውስጥ ኒያ ሲያደርጉ በምላሳቸው ያልተናገሩ በመሆናቸውና አሏህ(ሱ.ወ) ልብ ያሰበውን ስለሚያውቅ ያሰቡትን ለርሱ መንገር አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው።
  • ከዚያም በአሏህ ስም በመጀመር «ቢስሚ ላህ» ማለት
  • ከዚያም ሁለቱን መዳፎች ሦስት ጊዜ ማጠብ
  • ከዚያም ሦስት ጊዜ መጉመጥመጥና በአፍንጫ ውሃ ስቦ ማስወጣት
  • ከዚያም ፊትን በአግድም ከጆሮ እስከ ጆሮ ከላይ ጸጉር ከቆመበት ጀምሮ ወደ ታች ከአገጭ በታች ድረስ አዳርሶ ሥስት ጊዜ ማጠብ
  • ከዚያም እጆችን ከጣቶች ጫፍ እስከ ሁለቱ ክርኖች ድረስ በቀኙ ጀምሮ ግራውን በማስከተል ሦስት ጊዜ ማጠብ
  • ከዚያም እጆቹን አርጥቦ ከግንባሩ በላይ አንስቶ ወደ ማጅራቱ ራሱ ላይ በማሳረፍና ከዚያም ወደ ፊት በመመለስ አንድ ጊዜ ራስን ማበስ
  • ከዚያም አመልካች ጣቶቹን በጆሮዎቹ ቀዳዳዎች ውስጥ በማስገባትና በአውራ ጣቶቹ የጆሮዎቹን የውጭኛ ክፍል አንድ ጊዜ ማሰብ
  • ከዚያም ሁለት እግሮቹን ከጣቶች ጫፍ እስከ ሁለቱ ቁርጭምጭሚቶች ድረስ በቀኙ እግር ጀምሮ ግራውን በማስከተል ሦስት ጊዜ ማጠብ

የገላ ትጥበት (ጉስል)

ጉስል ወይም የገላ ትጥበት እንደ ሩካቤ ሥጋ ግንንኙነት ፣ ጀናባህ እና የወር አበባ ሐይዱ መጥቶ መሄድ ያለ ገላን የመታጠብ ግዴታ (ዋጅብ) የሆነ ጦሃራ ነው።

የገላ ትጥበት አፈፃፀም

  • ገላ ለመታጠብ በምላስ ሳይናገሩ በልብ ኒያ ማድረግ
  • ከዚያም በአሏህ ስም በመጀመር «ቢስሚ ላህ» ማለት
  • ከዚያም የተሟላ ውዱእ ማድረግ
  • ከዚያም በራሱ ላይ ማፍሰስና በደንብ ካረጠበው በኋላ ሦስት ጊዜ በራሱ ላይ ማፍሰስ
  • ከዚያም የተቀረውን የገላውን ክፍል ማጠብ

ተየሙም

ተየሙም:- ውሃ ያጣ ወይም ውሃ መጠቀም ለጉዳት የሚዳርገው ሰው በውዱእና በገላ ትጥበት (ጉስል) ፈንታ በአፈር የሚደረግ ግዴታ (ዋጅብ) የሆነ ጦሃራ ነው።

የተየሙም አደራረግ

ተየሙም ንፅህና የሚያደርገው በውዱእ ይሁን ወይም በገላ ትጥበት (ጉስል) ምትክ የቱ እንደሆነ ለይቶ ኒያ ማድረግና መዳፎቹን በመሬት ገጽ ወይም እንደ ግድግዳ ባለና ከመሬት ጋር በተያያዘ ነገር ላይ በማሳረፍ በመዳፎቹ ፊቱንና እጆቹን ማበስ ነው።

ጫማ ላይ ማበስ አል-መስሑ ዐለል ኹፍፈይን ወይም ጫማ ሲባል ማለት የተፈለገው ከቆዳና ከመሳሰሉት የተሠራ ሆኖ እግር የሚጠለቅበትና የሚሸፈንበት ሽፋን ማለት ነው። ጀዋርብ ወይም የግር ሹራቦች ሲባል ደግሞ ማለት የተፈለገው ከጥጥና ከመሳሰሉት ነገሮች ተሠርቶ እግር ላይ የሚለበስ ካልሲ ለማለት ነው።

ጫማዎችና ካልሲዎች ላይ ማበስን የሚመለከት ደንብና ማበስ ሕጋዊ ለመሆኑ ከቁርአንና ሱና የተወሰደ ማስረጃ፦

በጫማዎቹ ላይ ማበስ ከአሏህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) የተላለፈ ሱና ሲሆን ጫማ ወይም የእግር ሹራብ የለበሰ ሰው ውዱእ ሲያደርግ አውልቆ እግሩን ከመታጠብ የጫማዎቹን ወይም የእግር ሹራቦቹን የላይኛ ክፍል በእጅ አበስ አበስ ማድረጉ የበለጠ ይሆናል። ለዚህ ማስረጃው የሙጊራብን ሹዕባህ ሐዲሥ ነው።

ሙጊራ በተረኩት መሠረት ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ውዱእ እያደረጉ ወደ እግሮች ትጥበት ሲደርሱ ጫማዎቻቸውን ላወልቅላቸው ጎንበስ ስል፡ «ተዋቸው ንጹህ ሆነው (ከታጠብኩኝ በኋላ) ነው ያስገባኋቸው አሉና በእጃቸው የጫማዎቻቸውን የላይኛ ክፍል አበሱ።»

በውዱእ ወቅት ሁለቱን እግሮች ከጫማ አውጥቶ ከማጠብ ይልቅ ጫማዎቹን ሳይፈቱ በእጅ ማበስ ሕጋዊነቱ በአሏህ መጽሐፍ በቁርአን እና በአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ሱና የፀና ነው።

የሕጋዊነቱ ማስረጃ ከቁርአን የሚከተለው የአሏህ(ሱ.ወ) ቃል ነው «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን ፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ። ራሶቻቻችሁንም በውሃ እበሱ። እግሮቻችሁንም እስከ እስከ ቁርጭምጭሚቶች እጠቡ፤…»

በላይኛው አያ ውስጥ በአማረኛ «እግሮቻችሁንም» ተብሎ የተተረጎመው «ወአርጁ ለኩም» እና «ወአርጁልኩም» የሚሉና ከአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መተላለፍፋቸው የተረጋገጠ ሁለት ዓይነት ‹ቅራአህ› አነባብ አለው። በአንደኛው አነባብ መሠረት እግሮቻችሁንም እጠቡ የሚል ትርጉም ይሰጣል።

በሁለተኛው አነባበብ ደግሞ ራሶቻችሁንም በውሃ እበሱ ከሚለው ጋር በመጣመር እግሮቻችሁንም በውሃ እበሱ የሚል ፍቺ ይሰጣል። ሁለቱ እግሮች በውዱእ ወቅት ሊታጠቡም በውሃ ሊታበሱም መቻላቸውን ያብራራው የነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ሱና ነው።

ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እግሮቻቸው ከጫማ ውጭ በሆኑ ጊዜ ውዱ እካደረጉ ያጥቧቸው ነበር ሲሆን ውዱእ ሲያደርጉ ጫማ አድርገው ከሆነ የጫማዎቻቸውን የላይኛ ክፍል በእጅ ያብሱ ነበር።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top