የጁምአ ሶላት በጀመአ የሚሰገድ ስግደት ሲሆን በኢማሙ የሚሰጥ ኹጥባ (ትምህርት) አለው።
የአሏህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ፀሀይ ከወጣችበት ቀን በላጩ ጁምአ ነው። በዚያን ቀን አደም ተፈጥሯል ፤ ጀነትም ገብቷል ፤ ከሷም ወቶባታል» ብለዋል። {ሙስሊም}
አንድ ሰው በትክክል የገላ ትጥበትና ውዱእ አድርጐ ወደ ጀመአ ሶላት ከመጣና ዝምና ልብ ብሎ ኹጥባውን ካዳመጠ በዚያና በመጭው ጁምአ መካከል ትንንሽ ሃጢያቶቹ ይማሩለታል። {ሙስሊም}
በጁምአ ቀን የሚከናወኑ ተግባራት
- ገላን መታጠብ(ጉሱል)
- ጥፍርን መቁረጥ
- ሲዋክ መጠቀም
- ሽቶ መቀባት
- ቀደም ብሎ ወደ መስጅድ መሄድ
- ወደ ኢማሙ ጠጋ ብሎ መቀመጥ
- ልብ ብሎ ሁጥባውን ማዳመጥ
- ሱራ አል-ካኽፍን ማንበብ
- ዱአ ፣ ዚክርና ስቲግፍር ማብዛት
- ሶፍን ማስተካከል
የጁሙአ ሶላት በነማን ላይ ነው ግዴታ የሚሆነው?
የጁምአ ሶላት በእያንዳደንዱ ሙስሊም ማለትም ሴት ፣ ወንድ ፣ ወጣት ፣ አዛውንት ፣ በአእምሮው ጤናማ የሆነ ሰው ሁሉ ላይ ግዴታ ነው።
የጁምአ ሶላት በሚከተሉት ላይ ግዴታ አይሆንም
- የታመመ ወይም መከራ ችግር ያጋጠመው ሠው ወደ መስጅድ መሄዱ በሽታው የሚባባስበትና የሚያስፈራው ከሆነ
- በጉዞ ላይ ያለ ሰው
- ሃይድ ላይ የሆነች ሴት
- ልጆች
ሴቶች በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጊዜ መስጅድ በመገኘት ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ይሰግዱ ነበር። ሴቶች ወደ መስጅድ እንዳይሄዱ የሚከለክል አንድም የቁርአን አያት የለም።
እንዲሁም ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ሴቶች ወደ መስጅድ እንዳይሄዱ የሚከለክል ሰሂህ ሐዲስ የለም። ይልቁንስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአሏህ ባሪያ የሆነች ሴትን ወደ መስጅድ ከመሄድ አትከልክሏት ብለዋል። {ሰሒህ ሙስሊም}
ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ): የአንድኛችሁ ሚስት ወደ መስጅድ ለመሄድ ፍቃድ በጠየቀች ወቅት አትከልክሏት ብለዋል። {ሰሂህ አል-ቡሐሪ}
ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት አንድ ሰው መስጅድ ውስጥ የሚሰግድ ከሆነ ከ 27 ጊዜ በላይ ሰዋብ ያገኛል ብለዋል።
የጁምአ ቱርፋት
ኢብን አውስ እንደዘገበው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከቀናቶች ሁሉ በላጩ ጁምአ ነው ብለዋል። የአሏህ መልእክተኛ የጁምአን ቱሩፍት ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡ አንድ ሙስሊም ሲፀልይ ለፀለየው ነገር የፈለገውን የሚሰጥበት አንዲት ጊዜ አለች ሲሉ ይች ጊዜ በጣም አጭር መሆኗን በጣታቸው አመለከቱ። {ቡሐሪና ሙስሊም}
"እናንተ ያመናችሁ ሰዋች ሆይ! በጁምአ ቀን የሶላት ጥሪ በታወጀ እለት አሏህን ለማውሳት ተጣደፉ ፤ ግብይቶቻችሁንም ተው። እምታውቁ ከሆነ ይህ ለናንተ ከሁሉም በላይ የተሻለ ነው። የአሏህንም ችሮታ ሻቱ ስኬታማ ትሆኑም ዘንድ አሏህን ብዙ አውሱት።" {አል-ቁርአን 62:9-10}
በጀመዓ የመስገድ ምንዳ
"የአሏህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) በጀመዓ መስገድ በግል ከመስገድ ሃያ ሰባት እጥፍ በላጭ ነው ብለዋል።" {አል-ቡሐሪና ሙስሊም}
የአሏህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ "ንፁህ በሆነ ሁኔታ ላይ ሆኖ የግዴታ (ዋጅብ) ሶላቱን ለማከናወን ቤቱን ትቶ የሄደ ልክ በኢህራም ሁኔታ ላይ እንዳለ ሃጃጅ ነው" ብለዋል። {አቡ ዳውድ}
ከጁምአ ሶላት በፊት ያሉ ሱና ሶላቶች
- ወደ መስጅድ እንደገቡ ሁለት ረከአ መስገድ
አቡ ቀትዳ(ረ.ዐ) እንደዘገበው የአሏህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ከናንተ መካከል መስጅድ በገባ ወቅት ከመቀመጡ በፊት ሁለት ረከአ ሶላት ይስገድ ብለዋል። {ቡሐሪና ሙስሊም}
ጃቢር እንደዘገበው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የጁምአ ኹጥባ በማድረግ ላይ እያሉ አንድ ሰው ወደ መስጅድ መጣ። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሶላት ሰግደሃል? ሲሉ ጠየቁት። ሰውየውም አልሰገድኩም ሲል መለሰ። ሁለት ረከአ ሶላት እንዲሰግድም ነገሩት።
በሌላ ትረካ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ ከእናንተ መካከል በጁምአ ቀን ወደ መስጅድ የመጣና ኢማሙ ኹጥባ እያደረገ ከሆነ ሁለት ረከአ ይስገድ ፈጠንም ያድርጋቸው ብለዋል። {አህመድ ፣ ሙስሊም ፣ አቡዳውድ}
- በኹጥባ ወቅት ማውጋት የተከለከለ ነው
እንደ አብዛኛዎቹ ኡለማዎች ፈትዋ በኹጥባ ወቅት ዝም ማለት ግዴታ ነው። አንድ ሰው በኹጥባ ወቅት ውይይት ውስጥ ሊገባ ይቅርና በመልካም ማዘዝ ወይም ከሃጢያት መከልከል እንዲሁም ሰላምታን መመለስ አይኖርበትም።
ኢብን አባስ እንደዘገበው ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ በጁምአ ኢማሙ ኹጥባ እያደረገ እያለ የተናገረ የመራ ልክ መጽሐፍት እንደተሸከመች አህያ ነው። እናም ዝም እንዲል ለሚናገሩ ለጁምአው ምንዳ የላቸውም ብለዋል። {አህመድ ፣ ጦበራኒ ፣ ኢብን ሐጀር}