ኸድጃ የፍቅር ምሳሌ 3

ክፍል ሶስት

የመጀመሪያዎቹ ሶስት ሴት ልጆቻቸው የሞቱት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት እያሉ ሲሆን ተወዳጇ ልጃቸው ፍጢማ (ረ.ዐ) የሞተችው እሳቸው ከሞቱ ከስድስት ወር ብኋላ ነበር።

እንዲሁም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሶስት ወንድ ልጆች ነበሯቸው። ሁለቱ ከኸድጃ (ረ.ዐ) ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ከማሪያ ኸብጥያ (ረ.ዐ) ነበር።

ሆኖም የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው ቃሲም ይባላል። በዚህም ምክኒያት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አበል ቃሲም እየተባሉም ይጠራሉ። ሁለተኛው ልጃቸው ደግሞ አብዱሏህ ሲሆን ጧሂር(ንፅሁ) ወይም ጦይብ(መልካሙ) እየተባለ ይጠራል።

የአሏህ ውሳኔ ሁኖ ሁለቱም ልጃቸው የሞቱት በልጅነት ጊዜያቸው ነበርና ከሃዲያኖች ሙሐመድ ይህን ተልዕኮውን የሚያስቀጥልለት የለውም ብለው በጣም ተደሰቱ።

ሶስተኛ ወንድ ልጃቸውን የወለዱት ከማርያ ኸብጥያ ሲሆን ስሙም ኢብራሂም ይባላል። የሞተው ገና በጨቅላ እድሜው ነበር። ታዲያ እሱ በሞተ ጊዜ የፀሃይ ግርዶሽ ተከሰተ። እንደሚታወቀው የጥንት አረቦች በጥንቆላቸውና በድግምተኛነታቸው ይታወቃሉ።

ሆኖም ይህን ክስተት ከትልቅ ሰው ሞት ጋር አያያዙት። በእርግጥ አንዳንድ ሙስሊሞችም ይህን ክስተት ከልጃቸው ኢብራሂም ሞት ጋር ያያይዙታል።

ነገርግን ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወዲያውኑ ኹጥባ ወደ ሚያደርጉበት ሚንበር ወጡና “የፀሀይ ግርዶሽ የአሏህ ምልክት ነው። በማንኛውም የሰው ልጅ ሞት ምክኒያት በፍፁም አይከሰትም። ይህንን በተመልከታችሁ ጊዜ ሶላት ስገዱ” አሉ።

አብዛሃኛዎቹ ልጆቻቸው የሞቱት እሳቸው በህይወት እያሉ ነበርና ጠላቶቻቸው ዘሩ የተቋረጠ፤ ወራሽ የሌለው እያሉ ይጠሯቸው ጀመር። በማስከተልም አሏህ የሚከተለውን የቁርአን አያ ገልፀላቸው፦

“በእርግጥ ከውሰርን(በጀነት ያለ ወንዝ) ሰጠንህ። ከሃዲያኖች እናም ለጌታህ ስገድ፤ ሰዋም። ጠላትህ በእርግጥ ዘሩ የተቋረጠ ነው (አላቸው)።” 

{አል-ቁርአን 108: 1-3}

ከሃዲያኖች “የእስልምናን መስፋፋት ለማስቆም ብዙ ዘዴዎችን ተጠቅመናል ግን እስልምና ብዙ ተከትልዮችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያፈራ ነውና በቀጣይ ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ለመወሰን ስብሰባ ሊኖረን ይገባል” አሉ።

ይህን ተከትሎም በበኑ ሐሽም ጎሳ ላይ ፓለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ አድማ ማድረግ አለብን ብለው በስብሰባቸው ላይ ወሰኑ። ይህ የተከሰተው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአሏህ መልዕክተኛ እንደሆኑ ካወጁ ከሰባት አመት ብኋላ ነበር።

ከሃብታም አባቷ ቤት በቅንጦት ያደገችው ኸድጃ (ረ.ዐ) ትልቅ የኢኮኖሚ ችግርና መከራ ተጋፈጠች። ሆኖም ግን ቤቷ የአሏህ መልዕክተኛ የሚኖሩበት ፣ ጅብሪል አዘውትሮ ወህይ ይዞ የሚመጣበት ስለሆነ የተባረከ ቤት ነበር።

ይህ ምንም የማያውቁ ህፃናት ለከፋ ችግርና ረሃብ የተጋለጡበት ፣ ወጣቶች የዛፍ ቅጠል እየበሉ ህይወታቸውን ለማትረፍ የተሯሯጡበት የመከራ ጊዜ ነበር። ይሁን እንጅ የረሱል ተከታዮች ጠንካሮች ነበሩና ከእምነታቸው ነቅነቅ አላሉም። ይልቁንም የበለጠ ጠንካሮችና ንፁሆች ሁነው ወጡ።

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ መዲና ከተሰደዱ ብኋላ ቤታቸውን የአሊ ወንድም ይኖርበት ጀመር። ብኋላ ላይ ሙአውያ ቢን አቡ ሱፍያን (ረ.ዐ) ይህን ቤት ገዝቶ መስጊድ ገነባበት። ሆኖም የኸድጃ ቤት ቦታ ለዘላለም የሶላትና የኢባዳ ቦታ ሆነ። አሏህ ሶላትን ግዴታ ከማድረጉ በፊት ኸድጃ (ረ.ዐ) ሶላቷን ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ትሰግድ ነበር።

ኸድጃ (ረ.ዐ) የሞተችው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ መዲና ከመሰደዳቸው (ከሂጅራ) ከሶስት ዓመት በፊት ነበር። የሞተችው በ65 ዓመቷ ሲሆን 25 ዓመቷን ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር አሳልፋለች። በጊዜው ሞትን ትጠላ ስለነበር በሞት አፋፍ ላይ ሆና በተመለከቷት ጊዜ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አሏህ የደነገገው ነው እያሉ ያፅናኗት ነበር።

ተወዳጅ ባሏን በሰመመን እይታ እየተመለከተች ነፍሷ ምድራዊ አካሏን ተለይታ ሄደች። መቃብሯ የተዘጋጀው በመካ አቅራቢያ ሁጁን ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ሲሆን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መቃብሯ በትክክል የተዘጋጀ መሆኑን ለማረጋገጥ ወርደው ካዩ ብኋላ አካሏን በእጆቻቸው እቅፍ አድርገው ወደ ቀሪው ቤቷ አስገቧት። ህይወቷን ለኢስላም መስዋዕት ያደረገች የሙስሊሞች እናት ይችን ዱንያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለየች።

በተመሳሳይ ዓመት ከቤተሰቦቻቸው መካከል የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አጋዥ እና ረዳታቸ የነበረው አጎታቸው አቡጧሊብ ሞተ። በሁለት ወራቶች ውስጥ ሁለቱን ጥብቅ አጋሮቻቸውን እና አጋዦቻቸውን አጡ። በዚህም ምክኒያት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በጣም አዘኑ። ሆኖም ይህን አመት አመል ሁዝን (የሃዘን አመት) ሲሉ አወጁ።

አጎታቸው በነዚያ ወሳኝ ጊዜያቶች የነበረውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና በጊዜው የነበረውን ስልጣን ተጠቅሞ ከአረመኔዎች ሴራ ጠብቋቸዋል። ሃብታም ሚስታቸውም ሁሉንም ሃብቷን ለኢስላም ስትል ያወጣች ሲሆን ትልቅ የሞራል ድጋፍ ታደርግላቸው ነበር።

አንድ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሶሃባ እንዳስተላለፈው ስጦታ በመጣላቸው ጊዜ ወድያውኑ ለኸድጃ (ረ.ዐ) ጎደኞች ይልኩላቸው የነበር ሲሆን ተወዳጅ የሆነችው ሚስታቸው አኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው ደግሞ ፍየል በታረደ ጊዜ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተወሰነ ስጋ ለኸድጃ (ረ.ዐ) ጎደኞች ይልኩላቸው ነበር።

በዚህም ምክኒያት አኢሻ(ረ.ዐ) ከማንም የነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶች ላይ ቅናት በፍፁም አድሮብኝ አያውቅም ኸድጃ ላይ ቢሆን እንጅ ትላለች።

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለኸድጃ (ረ.ዐ) የነበራቸውን ዘላለማዊ ፍቅር ሲገልፁ ለጎደኞቿ ትልቅ ክብር አለኝ በልቤ ውስጥ ልዩ ቦታ አላትና ይሉ ነበር።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top