አህካም ወይም የፍርድ ውሳኔ ለሚለው ቃል ነጠላ ቁጥር አመልካች የሆነው ሁክም የሚለው ቃል ነው። ውሳኔ ወይም ብያኔ የሚል ትርጉም አለው። በእስልምና ማንኛውም ተግባር በሚከተሉት አምስት ምድቦች ይከፈላል
ዋጅብ (ግዴታ)
በዚህ ምድብ ያሉ ተግባራቶች በሁሉም ሙስሊሞች ላይ ግዴታ ናቸው። እነዚህን ተግባራቶች የሚፈፅሙ ሰዎች ይመነዱባቸዋል፤ ይሸለሙባቸዋል። ሳይሰሩ ችላ ያሏቸው ሰዎች ደግሞ ይቀጡባቸዋል። የረመዷን ወር ፆም የእነዚህ አይነት ተግባሮች አንዱ ምሳሌ ነው።
ሐራም (የተከለከለ)
በዚህ ምድብ ስር ያሉ ተግባራቶች የተከለከሉ ናቸው። ለምሳሌ መስረቅ እና መዋሸት። ከእነዚህ አንዱን የፈፀመ፤ የሰራ ሰው ይቀጣል።
ሙስተሃብ (የተወደደ)
በዚህ ምድብ ስር የሚገኙ ተግባራቶች ቢሰሩ የሚወደዱ ናቸው። ለምሳሌ ከመግሪብ ሶላት በኋላ ሁለት ረከአ መስገድን ይይዛል። እንደዚህ ያሉ ተግባራትን የሚፈፅም ሰው ለስራው ይመነዳል፤ ይሸለማል። የተውት ግን አይቀጡበትም።
መክሩህ (የተጠላ)
በዚህ ምድብ ስር ያሉ ተግባራት የተጠሉ ናቸው። ለምሳሌ በሆድ መተኛት። ይህ የሙስተሃብ ተቃራኒ ነው። መክሩህ የሆኑ ነገሮችን ማስወገድ እንደ ጥሩ ስራ እሱን መስራት ደግሞ እንደ መጥፎ ስራ ይቆጠራል።
ሙባህ (የተፈቀደ)
በዚህ ምድብ ስር ያሉ ተግባራት በእስልምና የተፈቀዱ ናቸው። ነገርግን ሃይማኖታዊ ይዘት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ አሳ መብላት። እነሱን የመስራትም ያለመስራትም ምርጫ አለን።
የሰውየው ኒያ (ሃሳብ) ግን ሙባሁን ወደ ዋጅብነት ፣ ሙስተሃብ ፣ መክሩህ ወይም ዋጅብነት ሊቀይር ይችላል። ሌሎች ነገሮችም የሙባሁን ደረጃ ሊቀይሩ ይችላሉ።
ለምሳሌ ማንኛውም ሙባህ ሰው ሊጎዳ እንደሚችል ከተረጋገጠ ሐራም ይሆናል። እንዲሁም ዋጅቡን ለማሟላት የሚያስፈልግ ተግባር ከሆነ ዋጅብ ይሆናል።
የፈርድ እና የዋጅብ ብያኔ (ውሳኔ) ሁለት አይነት ነው።
ፈርዶል አይን (በእያንዳንዱ ሰው ላይ ግዴታ የሆነ)
ለአቅመ አዳም በደረሱ ጤናማና ሃላፊነትን መውሰድ በሚችሉ በሁሉም ሙስሊሞች ላይ መሰረታዊ የሆነ ግዳጅ ነው። ልክ እንደ አምስቱ የየቀኑ ሶላቶች እና የረመዷን ፆም ያሉ ስራዎች ማለት ነው።
ፈርዶል ኪፋያ (የጋራ ግዳጅ)
የአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ሌሎችን ከሃላፊነት ነፃ የሚያደርግ በተወሰኑ ሰዎች ሊከናወን የሚችል መሰረታዊ ግዳጅ ነው። ነገርግን በማንም ሊፈፀም ካልቻለ በሁሉም ሰው ላይ ሃጢያት ይሆናል። ለምሳሌ የተለያዩ እስላማዊ እውቀቶችን መማር እና ማስተማር
ለተጨማሪ መረጃ የሸሪአ ርዕስ ተመልከቱ