አዛን ፈርድ (የግዴታ) ሶላቶች መጥሪያ ነው። በመጀመሪያ ሙስሊሞች ያለ አዛን መስጊድ ውስጥ ይገኙ ነበር። እናም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሶሃቦቻቸውን አማከሩ፤ አንዳንዶቹ የይሁዳዎች ጡሩንባ ለመጠቀም ሃሳብ አቀረቡ፤ ሌሎቹ ደግሞ የክርስቲያኖች ቃጭል /ደወል/ ላይ ሃሳብ አቀረቡ።
ነገርግን አንዱም ለእሱ የሚያስደስት አልነበረም። ጉዳዩ እየተወያዩበት እያለ አብዱሏህ ኢብኑ ዘይድ በህልሙ የአዛን አደራረግ እንደተማረ ሊነግራቸው መጣ። ለቢላል እንዲያስተምረው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጠየቁት።
ቢላል ቢን ረባህ በኢስላም የመጀመሪያው ሙአዚን (አዛን አድራጊ) ነው። ኡመር ኢብን አልኸጧብ ለሶላት ጥሪ ሲያደርግ በሰሙት ጊዜ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሄደና አብዱሏህ ኢብኑ ዘይድ እንዳየው ያለ ህልም እሱም ተመሳሳይ ህልም እንዳየ ነገራቸው።
የአዛን ቃላቶች
አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር
አሏህ ሃያል ነው! አሏህ ሃያል ነው! (አራት ጊዜ)
አሽሃዱ አላኢላሃ ኢለሏህ
ከአሏህ ውጭ ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ! (ሁለት ጊዜ)
አሽሃዱ አነሙሐመደን ረሱሊሏህ
ሙሐመድ የአሏህ መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ (ሁለት ጊዜ)
ሀያአለ ሶላ
ወደ ሶላት ኑ (ሁለት ጊዜ)
ሃያ አለፈላህ
ወደ ስኬት ኑ (ሁለት ጊዜ)
አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር (ሁለት ጊዜ)
አሏህ ሃያል ነው! አሏህ ሃያል ነው!
ላኢላሃ ኢለሏህ (1ጊዜ)
ከአሏህ ውጭ ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ!
ለንጋት (ለፈጅር) ሶላት ጥሪ ሲደረግ “አሶላቱ ኸይሩን ሚነነውም (ሶላት ከእንቅልፍ ይበልጣል) የሚለው አባባል ሁለት ጊዜ ሃያ አለል ፈላህ ከሚለው አረፍተነገር ቡኋላ ይባላል።
አዛን በታወጀ ጊዜ ሸይጧን ላለመስማት ይሸሻል። ሙስሊሞች አዛን ሲሰሙ ለእያንዳንዱ ጥሪ መመለስ እና ከሙአዚኑ በኋላ እሱን ተከትለው ደግመው ማለት ይገባቸዋል።
ሙአዚኑ ሃያ አለሶላ (ወደ ሶላት ኑ) እና ሃያ አለል ፈላህ (ወደ ስኬት ኑ) ሌሎች ሰዎች ላሃውለውላ ቅወተ ኢላ ቢላህ (ሃይልም ብልሃትም የለም ከአሏህ ቢሆን እንጅ) ይላሉ።
አዛኑን የሰማ ማንኛውም ሰው ወይም ጅን በፍርዱ ቀን ለሙአዚኑ ይመሰክሩለታል።
የአዛን ጥሪ የሚያደርግ ሰው ሙአዚን ተብሎ ይጠራል። ከአዛን ቡኋላ የሚከተለውን በሉ
አሏሁመ ረበ ሃዚሂ ዳዕወቲ ታማ ወሶላቲል ቃኢማ አቲ ሙሐመደን አልወሲላ ወል ፈዲላ ወበአስሁ መቃመን ማህሙደኒለዚ ወአደተሁ ኢነከ ላቱህሊፉል ሚአድ።
ትርጉም፡ አሏህ ሆይ! የዚች ምሉዕ ጥሪና የዚች ለመስገድ የቀረበች ሶላት አምላክ ነህ። ለሙሐመድ ወሲላ እና ፈዲላ የተባሉ ገነቶችን ለግሳቸው። ቃል የገባህላቸውን የተመሰገነ ደረጃም አጎናፅፈህ ከሞት ቀስቅሳቸው። አንተ ቃልህን የምታጥፍ አይደለህምና። (ቡኻሪ)
ለበለጠ መረጃ ኢቃም እና ሸይጧን የሚሉ አርዕስቶችን ተመልከት