ኡመር ኢብን አል-ኸጧብ

Author picture

ኡመር የኸጧብ ልጅ ነው። እናቱ ኸትማ ቢንት ሐሽም ትባላለች። አዲ ተብሎ የሚጠራ የቁረይሽ ጎሳ ቅርንጫፍ አባል ሲሆን ከሌሎች ጎሳዎች በሚኖራቸው ጥል የቁረይሽ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ ስለነበር ትልቅ አክብሮት ይሰጡታል።

ኡመር (ረ.ዐ) የተወለደው ከዝሆኑ አመት ከአስራ ሶስት አመታት በኋላ ሲሆን ማንበብ እና መፃፍ ከሚያውቁ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በእርግጥ ኡመር ያኔ እስልምናን ሳይቀበል በፊት የኢስላም ግልፅ ጠላት ነበር።

በኋላ ላይ ግን በቻለው ሁሉ ኢስላምን አግዟል። አንድ ምሽት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አሏህ ሆይ ኢስላምን በአምር ኢብን ሒሻም ወይም በኡመር ኢብን አል-ኸጧብ አጠንክረው ሲሉ ዱአ አደረጉ። ዱአቸውም ወዲያውኑ ምለሽ አገኛ።

ኡመር እስልምናን እንዲያገለግል አሏህ መረጠው። አምር ኢብን ሒሻም ወይም አቡጃህል (የድንቁርናው አባት) ሲሉ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቅፅል ስም ሰጥተውታል።

ኡመር (ረ.ዐ) ሁለተኛው ኸሊፋ ነው። ከእስልምና  አርአያዎች ውስጥ አንዱና ምርጡ ምሳሌ ነው። ነብዩ አል-ፋሩቅ ሲሉ ጠርተውታል። ትርጉሙም እውነት እና ውሸት የሚዳኝበት መለኪያ ማለት ነው።

በግልፅ ከመካ ወደ መዲና የተሰደደው ብቸኛው ሰው እሱ ነው። ወደ መዲና የሚደረገው ስደት (ሂጅራ) በተጀመረ ጊዜ ብዙዎቹ ሙስሊሞች ከመካ የወጡት በድብቅ (በሚስጥር) ነበር። ኡመር (ረ.ዐ) የጦር መሳሪያውን ታጥቆ ወደ ካዕባ በመሄድ ሶላቱን ሰገደ።

የመካ ሹማምንት ድምፃቸውን አጥፍተው ይመለከቱት ነበር። ሶላቱን ሰግዶ እንደጨረሰ ድምፁን ከፍ አድርጎ ወደ መዲና ልሄድ ነው። እኔን ማስቆም የሚፈልግ ሰው ካለ ከሸለቆው ባሻገር ያግኘኝ። በእርግጥ እናቱ በሃዘን የምታለቅስለት ይሆናል።አለ።

ብዙ ጊዜ የኡመርን አስተያየት (ሃሳብ) በመደገፍ የቁርአን ራዕዮች ወርደዋል። በሁሉም ጦርነቶች እና ዘመቻዎች ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጎን ቆሟል። ለአሏህ እና ለመልዕክተኛው የነበረው ውዴታ ጥልቅ ነበር።

ኡመር (ረ.ዐ) በፍትሃዊነቱ ፣ በትህትናው ፣ ለህዝቦቹ በነበረው ቅን ልቦና ይታወቃል። አሚረል ሙእሚኒን (የሙእሚኖች መሪ) ተብሎ የተጠራው የመጀመሪያው እሱ ነው። በህይወት እያሉ የጀነት ብስራትን ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰጧቸው አስር ሰዎች መካከል አንዱ ኡመር (ረ.ዐ) ነው።

የኡመር ስም ከብዙ እስላማዊ አበርክቶወች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ለምሳሌ የመጀመሪያው ደዋን (የማህበራዊ አገልግሎት) ተቋም ፣ ይፋዊ የእስልምና የቀናት አቆጣጠር ማስተዋወቅ ፣ ሂጅራ ፣ የህዝብ ግምጃ ቤት ፣ የፖስታ አገልግሎት ፣ የፍትህ ችሎት ምስረታ እና የዳኞች ሹመት ወ.ዘ.ተ በመጀመሪያው ቁርአን በማሰባሰብ ሂደት ውስጥም አቡበክር አሲዲቅ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

ኡመር (ረ.ዐ) የተገደሉት በእሳቸው ላይ የግል ጥላቻ በነበረው ፐርዥያዊ ባሪያ ሲሆን የፈጅር ሶላት በጀመረበት ጊዜ ነበር። የሞቱት በስልሳ ሶስት አመታቸው ሲሆን የተቀበሩት ከአኢሻ የግል ክፍል ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና ከአቡበክር (ረ.ዐ) ጎን ነው።

በአንድ ወቅት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ እሱ ሲናገሩ ከእናንተ በፊት ከሆኑ ህዝቦች መሃል ወህይ የሚገለፅላቸው ሰዎች ነበሩ። ከእኔ ኡመት መካከል እንደዚህ አይነት ሰዎች ቢኖሩ ኡመር ኢብን አል-ኸጧብ አንዱ ይሆን ነበር ብለዋል። (ሙስሊም)

ሶሃባ ፣ ኹለፋኡ ራሽዱንአመል ፊል እና አተቅዊም አል-ኢስላሚ ተመልከቱ

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top