ሙስሊሟ እህቴ ለባልሽ ታዛዥ ሁኝ

ሙስሊሟ እህቴ ለባልሽ ታዛዥ ሁኝ

ሙስሊሟ እህቴ ለባልሽ ታዛዥ ሁኝ በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

የአሏህ ሰላምና እዝነት በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ፣ በቤተሰቦቻቸው ፣ በሶሃቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ እስከ የውመልቂያማ ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።

ሴት ልጅ ከእናት አባቷ ቤት ከወጣችበት እለት አንስቶ በባል ቃልኪዳን ውስጥ ትገባለች። ከዚህም ጎንለጎን ባል ለሚስቱ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ኢስላም እንዲያሟላላት ሲያዘው፤ እሷን ደግሞ ለርሱ ታዛዥ እንድትሆን ያዛታል።

ይህ ማለት ደግሞ ስብዕናዋን አጥታ ፣ መብቷን ተነጥቃ እንደባሪያ ዝቅ ትበል ማለት አይደለም። እራስን በባል ስር በማድረግ ታዛዥ መሆን ማለት እንጂ መጨቆን ወይም ሃሳብን በነፃነት አለመግለፅ ማለት አይደለም።

ይልቁንስ ረዳት በመሆን ሃሳቧን ፣ አስተያየቷን እና ስሜቷን ለባሏ ማካፈል ማለት ነው። እንዲያውም ብልህ ወንድ ማለት በራሱ ሃሳብ ብቻ ተደግፎ የመጨረሻ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት የሚስቱን ሃሳብና አስተያየት የሚጠይቅ ነው።

ከመብት ጋር በተያያዘ በዘመናችን በርካታ ቤተሰቦች እሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አሉ እነሱም:- ሴት የወንድ ረዳት አይደለችም ፣ የራሷ ነፃነት እና መብት ያላትናት ፣ የቤት ስራ የሴት የወንድ እየተባለ መለየት የለበትም ወ.ዘ.ተ የሚሉ ናቸው።

ነገር ግን ለአንድ ሙስሊም ሴት ትክክለኛ ክብር እና መብት ኢስላም ከሰጣት ውጭ የሚያስከብራት የለም። የሚገርመው ሴቶች እህቶቻችን ባሎታቻቸውን ሲሰድቡ፤ በአመፅ ቤታቸውን ሲንዱ በአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ላይ እያመፁ መሆኑን አለመረዳታቸው ነው።

አንዲት ሙእሚን ሴት እራሷን በባሏ ስር በማድረግ ታዛዥ እምትሆነው ባሏ የሚወዳትና የሚጠነቀቅላት ጥሩ ባል በመሆኑ ነው።

ሌላው ቀርቶ ፅኑና ደስተኛ የቤተሰብ ፍቅርን መስርታ መኖርን የምትሻ ሴት የባህሪ ችግር ያለባት ቢሆንም እንኳ እራሷን በባሏ ስር ማድረጓን እና ታዛዥ መሆኗን አትተውም፤ ምክኒያቱም የባል ሐቅ ምን እንደሆነ የተረዳች ናትና።

ለባሏ ታዛዥ እማትሆን ጨቅጫቃ ሚስት ግን የባሏን ባህሪ ችክ የሚልና በቀላሉ የሚበሳጭ እንዲሆን ታረገዋለች።

እንግዲህ አንዲት ሙስሊም ሴት በባሏም ሆነ በአሏህ ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን የባሏን የቤት አስተዳዳሪ ሃላፊነት ተቀብላ ለባሏ ታዛዥ መሆን ይኖርባታል።

ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል: ‹‹አንድን ሰው ከአሏህ ሌላ ላለ እንዲሰግድ ባዝ ኖሮ ሴትን ለባሏ እንድትሰግድ አዛት ነበር አሉ፤ በመቀጠልም በዚያ ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ ሴት የጌታዋን ሐቅ አታደርስም የባሏን መብት እስካልፈፀመች ድረስ›› ብለዋል።

ይህ ሐዲስ እኛ ሴቶች ምን ያህል የባሎቻችንን ሐቅ መጠበቅ እንዳለብን እና ይህ ካላደረግን የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቀን በሚገባ ይጠቁመናል። ስለዚህ እህቶቼ ይህንን አውቀን ተወዳጅ እና የባልን ሐቅ ጠባቂ እንሁን።

አሏህ ላላገባን ጥሩ ትዳርን ላገባችሁ ደግሞ ባሎቻችሁን ተንከባካቢና ታዛዥ ያድርጋችሁ። አሚን!

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top