የእውቀት ታላቅነት

የእውቀት ታላቅነት በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ምስጋና ለአለማት ጌታ ለሆነው ለአሏህ ይገባው። የአሏህ ሰላምና እዝነት በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።

የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም አደም አለይሂ ሰላም ወደዚች አለም ሲመጣ ከአሏህ ዘንድ የነገራቶችን ስምና እውቀት አሏህ ችሮት ነው።

እንዲሁም ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻው ወህይ (ቁርአን) ሲገለፅላቸው የመጀመሪያው ቃል «ኢቅራ» አንብብ የሚል ነበር። ይህ ምን ያህል እውቀት በኢስላም ቦታ ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው።

“አሏህ ከእናንተ መካከል እነዚያ ያመኑትንና እውቀት የተቸሩትን በደረጃ ከፍ ያደርጋል።”

{አል-ቁርአን 58:11}

እንዲሁም በቡኋሪ በተዘገበው ሐዲስ መሠረት እውቀትን መሻት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው።

ኢማሙ ሙሐመድ አልገዛሊ እንዳሉት እውቀት የእያንዳንዱ ተግባር ፣ የስራ ወይም የእምነት መሰረት ነው። ካለ እውቀት መልካምነትና ደግነት በዚህም ሆነ በመጭው አለም ሊገኝ አይችልም።

ስለዚህ እንደተባለው ከእውቀት በላይ ወደ አሏህ የሚያደርስ (የሚያመራ) መንገድ የለም በእውቀት ቢሆን እንጂ። የሰው ልጅ ጌታውን በብቸኝነት እንዳይገዛ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ የሰው ልጅ ልብ በድንቁርና ፅልመት መሸፈኑ ነው።

እውቀት የህይወት መሠረት ነው። በእውነቱ እውቀት በራሱ ህይወት ነው። እንዲሁም ድንቁርና የሞት መሠረት ሲሆን ድንቁርና በራሱ ደግሞ ሞት ነው።

ከእውቀት ባሻገር ከሁሉም ነገር በላይ ከአሏህ ዘንድ የተወደደ ነገር ቢኖር ኖሮ ለአደም (ዐ.ሰ) ይሰጠው ነበር። አሏህ በቁርአኑ እንዲህ ይላል፦

“አሏህ በማስተካከል የቆመ አስተናባሪ ሲሆን ከእሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ መሆኑን መሠከረ። መላዕክቶችና የእውቀት ባለቤቶችም እንዲሁ መሠከሩ። ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። አሏህ አሸናፊና ጥበበኛ ነው።”

{አል-ቁርአን 3:18}

ከዚህ መገንዘብ እንደሚቻለው አሏህ (ሱ.ወ.ተ) ራሱን በመጥቀስ ይጀምርና በሁለተኛ ደረጃ መላዕክቶችን ያወሳል። ከዚያም በሶስተኛ ደረጃ የእውቀት ባለቤቶች ሲል ይጠቅሳል።  

በሌላ አያ ደግሞ አሏህ የራሱን እና የኡለማዎች ምስክርነት በቂ እንደሆነ ያመላክታል።

“በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአሏህና እርሱ ዘንድ የመፅሐፉ እውቀት ባላቸው በቃ በላቸው።”

{አል-ቁርአን 13:43}

በሌላ የቁርአን አያህ አሏህ እንዲህ ይላል:- «በእርግጥ አሏህን ፈሪ አገልጋዮች ሊቃውንቶች ናቸው።»

ለዚህ ምክኒያቱ ግልፅ ነው። በእርግጥ አንድ ሰው ካለ እውቀት የአሏህ ፍራቻ ሊኖረው አይችልም። እንዲሁም የአሏህን ቁጣ ፣ የጀሃነምን ቅጣት ፣ የቂያማን መከራ ካለ እውቀት ሊረዳ የሚችል የለምና ነው።

ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) "አሏህ ከሁሉ በላይ ቸር ነው። እኔ ከእናንተ መካከል በጣም ለጋስ ነኝ እናም ከእኔ ብኋላ ከእናንተ መካከል በጣም ለጋስ የሆነው እውቀትን የሚሽትና የሚያስፋፋት ነው" ብለዋል።
ኢማሙ ዘሃቢይ እንደዘገበው ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) "በፍርዱ ቀን የኡለማዎች (የሊቃውንት) የቀለም ማሰሮ እና የሰማእታት ደም ወደ ፊት ይመጣል። የኡለማዎች ቀለም ከሰማእታት ደም በላይ ይሆናል" ብለዋል።

በሐዲስ ሸሪፍ እንደተዘገበው አንድ ሰው እውቀትን በመሻት ላይ እያለ የሞተ አሏህን በዚያው ሁኔታ ላይ ይገናኛል።

በሙአሊመቱ ተንዚል እንደተዘገበው ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) «አንድ ሰው እውቀትን ለመሻት ሲጓዝ መላኢካዎች ክንፎቻቸውን ከእግሩ ስር ያደርጉለታል ፤ ሰማያትና ምድር እንዲሁም የውቅያኖስ አሳዎች ዱአ ያደርጉለታል።» ብለዋል።

የእውቀትን ታላቅነት ለመረዳት እውቀት ከአሏህ ባህሪያት መካከል አንዱ መሆኑን መገንዘብ በራሱ በቂ ነው። በዚህም ሆነ በመጭው አለም የህይወታችን መድህን የብልፅግናችን መሠረቱ እውቀት ነው።

እውነታውን ስንመለከት እውቀት የሌለው ሰው እንሰሳ ነው። የሰው ልጅ ልዩና ታላቅ የሚያደርገው ነገር እውቀቱና ንግግሩ ነው። ይህ ለኛ ጠቃሚ ከሆነ የእውቀትን ሃብት ለማግኘት ሁሌም መጣር ይጠበቅብናል።

እውቀትን በመፈለግ ላይ ሊገጥሙን የሚችሉ መሠናክሎች

እውቀትን በመሻት መንገድ ላይ ሆነን የሚገጥሙን መሰናክሎች የሚከተሉት ናቸው፦

የሸይጧን ፈተና

ከተረገመው ሸይጧን ዘንድ በጣም የተጠላና በጣም አደገኛ ነገር ቢኖር እውቀትን መሻት ነው። ይህን ጣልቃ ገብነት ፣ መሰናክል ለመዋጋት በጣም ቀላሉ ዘዴ የቁርአን አያቶችን እና ሐዲሶችን ማስታዎስ ሲሆን እንዲሁም ለሸይጧንም ጉትጎታና ማዘናጊያ ትኩረት አለመስጠት ነው።

ነፍስያ

መከራን ስትጠላ መዝናናትን እና መንፈስን ማርካታ ትወዳለች። በእርግጥ አንድ ሰው የዱንያን ጊዜያዊነትና የአሂራን ዘላለማዊ መኖሪያነት ሲረዳ እውቀትን የመሻት መከራ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ይሆንና ደስታውና ጥቅሞቹ እልቆቢስ ይሆኑለታል።

  • የጓደኛ ተፅእኖ
  • አለማዊ ጥቅምን መፈለግ
  • የሃብት ስስት

የዚህ ብልጭልጭ አለም ሃብት ጠፊና ከእውቀት ጋር ሊነፃፀር የማይችል ነው። አንድ ሰው ሲሞት ሃብቱ አይከተለውም ይልቁንስ ወደ መቃብሩ የሚከተለውና ጀነት እስኪገባ ድረስ የሚረዳው ነገር ቢኖር እውቀት ነው።

  • ቅን የሆነ አስተማሪ ማጣት
  • የእለት ተእለት ኑሯችንን ማሰብ

ውድ ሙስሊም እህት ወንድሞቼ ከገባንበት የድንቁርና አሮንቃ እንውጣ። በዚች ጊዜያዊ መኖሪያ አብዛሃኛዎን ጊዜያችነን ለምን በማይረባ ፍሬ ቢስ በሆነ ነገር እናባክነዋለን።

ስለዲናችን እውቀትን የምንሻበት ሰአት ይኑረን! በዚህም ሆነ በመጭው አለም እውቀት ጠቃሚ ነው። ከእፍረትና ከውርደት እንድናለን።

ይህን ትልቅ ሃብት ለመከሰብ ጊዜያችንንና ገንዘባችነን በእውቀት ላይ ኢንቨስት እናድርግ። አዲስ ነገርን ለማውቅ ከፍተኛ ጉጉት ይኑረን።

Share the Post:

Related Posts

መረጃ እና አስፈላጊነቱ

መረጃ ትርጉም ያለው መልዕክት ሆኖ ከአንድ ምንጭ ወደ ተጠቃሚ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር መግለፅ የሚያስችለን  ነው፡፡ ይህ መረጃ ከግለሰብ አስተሳሰብ

Read More
ተውባ
Ahmed Yesuf

ተውባ

ተውባ ማለት ሃጢያትን ወይም ወንጀልን ከሰራንና ከአሏህ(ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር አደጋ ላይ ከጣልን ብኻላ ወደ አሏህ በፀፀት መመለስ ማለት ነው።

Read More

Join Our Newsletter

Scroll to Top