አሏህ ይምረኝ ይሆን?

Author picture

አሏህ ይምረኝ ይሆን? በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። የአሏህ ሰላምና እዝነት በረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ፣ በቤተሰቦቻቸውና በሶሃቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ እስከ የውመል ቂያማ ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።

  • ሃራም ከሆኑ ነገሮች ጋር ያለን ቀረቤታ ምን ይመስላል?
  • ሃጢያት የሆኑ ነገሮችን ስንሰራ ቀላል መስለው ይታዩናል ወይስ ይከብዱናል?

ኑ እውነተኛና ጥርት ስላለች ተውባ እንተዋወስ! ወደ አሏህ ጥርት ባለች ተውባ ጓዛችንን ጠቅልለን እንመለስ!!!

በሱረቱ ተውባ መካከለኛዋ አያ ላይ አሏህ በተውበት ወደ እሱ ከተመለስን መጥፎ ስራዎቻችነን በመልካም ሊቀይርልን ቃል ገብቷል።

“እነዚያ የተፀፀቱት ፣ ያመኑትና መልካም ስራን የሰሩት ሲቀሩ። ለነሱም አሏህ መጥፎ ስራዎቻቸውን ሃጢያታቸውን በመልካም ስራ ይቀይርላቸዋል። አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው።”

{አል-ቁርአን 25:70}

ያማረ ተውባ

ተውባ አብዛሃኛውን ጊዜ ቀለል ባለ መልኩ እንደ ፀፀት(ንስሃ) ይተረጎማል። ነገር ግን በጣም ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው። የቃል በቃል ፍቹ ወይም ትርጉሙ ወደ አሏህ መመለስ ወይም ማፈግፈግ ማለት ነው።

ተውባ ማለት እራስን ዋጋቢስና የማይረባ አድርጎ መቁጠር አይደለም!!! ይልቁንም ተውባ በጣም ከሚወደዱ የኢባዳ አይነቶች አንዱ ሲሆን እያንዳንዱን ሃጢያቶቻችነን ወደ አሏህ የበለጠ እንድንጠጋና ከጠንካራ ባሪያዎቹ መካከል ለመሆን አይነተኛ መሳሪያ ሲሆን ምስያው በተስፋቢስነት ሊበጣጠስ እንደሚችል የብርሃን ሰንሰለት ነው።

ሁለት የሸይጧን መሠናክል

ሸይጧን በተውባ ወደ አሏህ ከመመለስ በሁለት መንገዶች ሊያሰናክለን እና ሊያደናቅፈን ይሞክራል። (1) ሃጢያቶቻችነን አቅለን እንድንመለከት እና እንድናስባቸው የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። እናም ሙሉ በሙሉ ማለት ይችላል በተውባ ላይ ቸልተኛና ግዴለሽ እንድንሆን ወዲያውኑ ሐራም በሆነ ነገር ይፈትነናል። (2) በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀለኛ እንደሆንና ወንጀላችን ደግሞ የከፋና በጣም የከበደ ፣ የተደጋገመ እንደሆነ ይጐተጉተናል። ታዲያ ይህን ሁሉ ወንጀል ይዘህ ወደ አሏህ ስትመለስ እፍረት አይሰማህም ሲል ይሰብካል።

በዚህ መንገድ እራሳችነን እንድንጠላ ፍሬቢስና የማንረባ ሰዎች እንደሆንና ሁልጊዜ በሃጢያቶች ላይ ተዘፍቀን እራሳችነን እየወቀስን እንድንኖር ነገሮችን ያመቻቻል። አሏህ ለእኛ ያለውን ውዴታ እንድንጠራጠር ያደርጋናል። ይባስ ብሎ አንዳንዴ ተውበት ከማድረግ ከመቆጠባችን የተነሳና ተስፋ በማጣታችን ምክኒያት የበለጠ በሃጢያት ላይ ሃጢያት በወንጀል ላይ ወንጀል እያከታተልን የበለጠ አመፀኞች እንሆናለን።

በአሏህ ምህረት ላይ ገደብ አናስቀምጥ

ለአሏህ ምህረት ሃጡያቶቻችን በጣም ከባድና ግዙፍ ናቸው ብለን ካሰብን ሳናውቀው የአሏህን ምህረት እየገደብን ነው ማለት ነው። አሏህ ተዋብ ነውና አሁኑኑ ወደ አሏህ እንመለስ።

ጥያቄው መሆን ያለበት አሏህ ይምረኝ ይሆን ሳይሆን እውነት ከልቤ ወደ አሏህ ጥርት ባለች ተውባ እመለስ ይሆን የሚለው ነው።

አሏህን እናመስግነው ቃልኪዳኑንም እንወቅ

ተውበት ማድረግ እንዳለብን ከተሰማን አሏህን እናመስግነው። ምክኒያቱም አሏህ ይህን ለኛ የሰጠን በረካ ነውና።

“በላቸው «እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ። አላህ ኃጢኣቶችን በመላ ይምራልና። እነሆ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና። ቅጣቱም ወደ እናንተ ከመምጣቱና ከዚያም የማትረዱ ከመኾናችሁ በፊት ወደ ጌታችሁ (በመጸጸት) ተመለሱ። ለእርሱም ታዘዙ። «እናንተ የማታውቁ ስትኾኑም ቅጣቱ በድንገት ሳይመጣባችሁ በፊት ከጌታችሁ ወደናንተ የተወረደውን መልካሙን (መጽሐፍ) ተከተሉ።”

{አል-ቁርአን 39:53-55}

የአሏህን ቃልቂዳኖች እንማር ዘንድ ቁርአንን እናንብ!!!

  • ቁርአን መቅራት ከተስፋቢስነት ያድናል
  • የአሏህን ውዴታ ያስገኛል
  • ጥሩን ከመጥፎ እንነድንለይ ያስችለናል
  • ሂወታችንን የሚቀይር ብቸኛው መመሪያ ነው

የሃጢያታችን ብዛትና ክብደት ገምግመን ሳይሆን የአሏህ መሃሪነትንና ታላቅነት አውቀን ወደ አሏህ እንመለስ። አሏህ ጥርት ባለች ተውባ ጓዛችነን ጠቅለን ወደ እሱ የምንመለስ ያድርገን! አሚን!

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top