አማር እና አሞራዎቹ

Author picture

ፈገግታው ጨረቃ ጅስሙ የሚያሳሳ፤
ድክ ድክ የሚል እንደጨቅላ እንቦሳ፤

በአማር ቁንጅና በልጃቸው ሀሴት፤
“ኡሙን” ሲያስለቅሳት ልቧን ፍቅር ሞልቶት፤
“አቢው” ይቦርቃል የልጅ ደስታ አስክሮት፤

በማር አንደበቱ “ኡሚ” ሲል ሲጣራ፤
ደግሞም ወደ አባቱ “አቢ” ሲል በተራ፤
ከአካባቢው ሲርቅ የሀዘን መከራ፤
ታጭዶ ይታፈሳል ፍቅር እንደአዝመራ፤

ድንገት……..
በጨዋታው መሀል ማንም ሳያስተውል፤
በደመቀው ሰማይ ደመናው በጠራ፤
ጀቶች ፈሰሱበት ሰርግ እንዳየ አሞራ፤
አማር በማየቱ ትናንሽ አሞራ፤
በጣም ተደሰተ ፊቱ በሀሴት አበራ፤

እያዉለበለበ ቀኝ እጁን ወደ ላይ፤
የሚያገኝ መስሎት አጸፋውን ከላይ፤
ደስታን ማግኘት ሽቶ ድንገት ሞትን ሳያይ፤

“እወዳችኋለሁ” ብሎ ወደ ላይ ተጣራ፤
በስሜት ተማርኮ ለበራሪ አሞራ፤
የቦንብ ብልጭታ በሰማይ ሲበራ፤
በጣም ደስ ብሎት ወላጁን ሊጠራ፤
ደንቦል ደንቦል ብሎ ወደፊት አመራ፤

ድንገት……..
ቤተሰቡን አዬ ፊቱ ሲሯሯጡ፤
አንድ ፍሬያቸውን በሞት እንዳያጡ፤

ከላይ የዘነበው የቦንብ ዶፍ ናዳ፤
ሆኖ እጣፋንታቸው የዘላለም ፍዳ፤

ቅዥት ሆኖ ቀርቶ የሰነቁት ተስፋ፤
አማር ተዘርሮ ፊታቸው ተደፋ፤

እግሮቹ በረሩ የሚቦርቅበት፤
ልሳኑ ተዘጋ ኡሚ የሚልበት፤

አማር ፍልቅልቁ……የወላጆቹ እንቁ፤
አማር ፍልቅልቁ…ለሰከንዶች ብርቁ፤

አካሉ ፈራርሶ በደም ጎርፍ ታጠበ፤
ዳግም ላይመለስ ሕይወቱ አሸለበ፤

አማር በእናቱ ፊት በቦንብ ሲደፋ፤
ክሩ ተበጠሰ የመኖሯ ተስፋ፤

ከጧት እስከማታ ፊቷ ውል እያለ፤
ሞቱን ለመቀበል አንጀቷ እንዴት ቻለ?

ምንጭ___ አብዱል ጀባር

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top