ክቡራን ወላጆች ልጆቻችን ከሃያሉ አሏህ የተሰጡን ጸጋዎች ናቸው። እነዚህን የዓይኖቻችነን ማረፊያዎች ፈጣሪያችን ሲሰጠን ግን ከተወሰኑ ሃላፊነቶችቶችና ግዴታዎች ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ይህ የእስላም ሃይማኖት ሲሆን ቀና የሆነ ብቸኛ መንገድ ነው። እናም የአብራካችን ክፋዮች የሆኑ ልጆቻችነን በተገቢው መንገድ በማነፅ የነገውን ትውልድ እንዲቀላቀሉና የአሏህ ባሮች እንዲሆኑ በትጋት መስራት ከእኛ ከወላጆች ይጠበቃል።
ይህን ጉዳይ በማስመልከት ከሁሉም ነገር በላይ ተወዳጅ የሆኑት መልእክተኛ ( ሰ.ዐ.ወ) ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:-
«ሁላችሁም እረኞች ናችሁ። ከምትጠብቁት ነገር ትጠየቃላችሁ። ባል የቤተሰቡ ጠባቂ ነው። ስለሆነም በቤተሰቡ ጉዳይ ይጠየቃል። ሚስት የባሏን ቤት ጠባቂ ናት። ስለሆነም የባሏን ቤት በተመለከተ ተጠያቂ ናት።»
ወላጆች ልጆቻቸውን አሏህን ለማስደሰት በማሰብ እርሱ በሚፈልገው መንገድ ካሳደጉ መልካም ስራን.. አሏህ በፍርዱ ቀን ምንዳቸውን እጥፍ ድርብ በማድረግ ይከፍላቸዋል። በልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ በኋላ በሚፈጠሩትና እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ቀናውን ጎዳና በሚከተሉት ዝርዮቻቸው ጭምር ምንዳን ያገኛሉ።
ይህ ትልቅ እድል ነው። ከዚህ በተቃራኒው ልጆቻቸው ዝንባሌያቸውን እንዲከተሉና መረን የለቀቁ እንዲሆኑ በማድረግ ያሳደጉም ተቃራኒውን ያገኛሉ። ሃያሉ አሏህ እንዲህ ይላል:-
አል-ቁርአን
ሱረቱ ረህማን 55:60
«የበጎ ሥራ ዋጋ በጎ እንጂ ሌላ ነውን?»
አል-ቁርአን
ሱረቱል ካህፍ 18:46
«ገንዘብና ወንዶች ልጆች የቅርቢቱ ህይወት ጌጦች ናቸው። መልካሞቹም ቀሪዎች ሦራዎች ጌታህ ዘንድ በምንዳ በተስፋም በላጮች ናቸው።»
ሴት ልጅ በኢስላም ያላት ቦታ
የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ “አንድ ሙስሊም ሰው ሁለት ሴት ልጆች ቢኖሩትና ለእነርሱ ጥሩ በሆነ ተርቢያ ካሳደጋቸው ጀነት ለመግባት ሰበብ ይሆኑለታል።”
እንግዲህ ማንም ቅን ልብ ያለው ሰው ይህንን የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር ክብደት ሊሰጥጠውና ለነገው ዓለም ህይወት መድህን ያስገኝለት ዘንድ በሚገባ አኳኋን ሴት ልጆቹን ሊያሳድግ ግድ ይለዋል።
ሃያሉ አሏህ የሰውን ልጅ ሲፈጥር ወንድና ሴት አድርጎና እንደ ማንኛውም ፍጡር የሁለትዮሽን መንገድ ተከትሎ ነው። ይህም በቀጣዩ የቁርአን አንቀፅ ተገልፃል።
አል-ቁርአን
ሱረቱ ሩም 30:30
“ወደ እውነት ተዝንባይ ሆነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ። የአሏህን ፍጥረት ያችን አሏህ ሰዎችን በርሷ ላይ የተፈጠረባትን ሃይማኖት ያዟት። የአሏህን ፍጥነት መለወጥ የለም። ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።”
በሌላ በኩል ደግሞ አንዱ ጾታ ሌላውን መፈለጉና የዚያ አይነት የተቃራኒ ፆታ ፍለጋ አዝማሚያዎች በተፈጥሮ የተቀመጡ የኃያሉ አሏህ ስራዎች መሆናቸው በቁርአን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል:-
አል-ቁርአን
ሱረቱል ኢምራን 3:14
“ከሴቶች ፣ ከወንዶች ልጆችም ፣ ከወርቅና ከብር ከተከማቹ ገንዘቦችም ፣ ከተሰማሩ ፈረሶችም ፣ ከግመል ፣ ከከብትና ከፍየልም ፣ ከአዝመራም የሆኑ ፍላጎቶችን መውደድ ለሰዎች ተሸለመ።”
ይህ እርስ በርስ የመፈላለግ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ታዲያ በቁጥጥር ሥር ካልዋለና በመንፈሳዊ እንዲሁም በኢስላም የሥነ-ምግባር አስተምህሮቶች ካልተለጎመ የሰውን ልጅ አይወድቁ አወዳደቅ ይጥለዋል። የአሏህ ነብይ (ሱ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
“ከእኔ በኋላ ከሴቶች የበለጠን ፈተናን በወንዶች ላይ አልተውኩም። የእስራኤል ልጆች እንዲወድሙ ምክኒያት የሆኗቸው ሴቶች ነበሩ።”
ውድ እህቴ አንቺ የመጭው ኢስላማዊ ትውልድ ተረካቢ የሆነ (የሆነች) ህፃን የሚፈሩበት ንፁህ ማህጸን ይዘሻል። አሏህ ባንቺ ማህጸን ውስጥ ኢስላምን የሚያልቁና የእርሱንም ክብር ከፍ የሚያደርጉ ልጆች ይጸነሱበት ዘንድ ፈቃዱ እንዲሆን እነሆ ራስሺን በማንፃት አመቻቺ። ይህ ማንፃት ማለት ደግሞ ሌላ ሳይሆን እርሱን በመፍራት ወደ ርሱ መቃረብ ነው።


Share