እውነትን መናገር በጣም የሚወደድ መልካም ልማድ ነው። ሁልጊዜም እውነትን የምንናገር ከሆነ እራሳችነን ከብዙ ችግሮች መጠበቅ እንችላለን። ይህ ብዙ መጥፎ ነገሮችን የሰራ ሰው ታሪክ ነው።
ነገር ግን እውነትን ለመናገር ቃል በመግባቱ ከመጥፎ ነገር ጠብቆታል።
አንድ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መጣና እንዲህ አላቸው: የአሏህ ነብይ ሆይ ብዙ መጥፎ ልማዶች አሉብኝና መጀመሪያ የትኛውን መተው አለብኝ? ሲል ጠየቃቸው። ነብዩም ውሸት መናገርን በመጀመሪያ ተው አሉት።
ሰውየውም ይህን እንደሚያደርግ ቃል ገብቶላቸው ወደ ቤቱ ሄደ። በምሽት ሊሰርቅ ሊሄድ ነበርና ከመሄዱ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር የገባውን ቃልኪዳን አሰበ። ነገ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የት ነበርክ? ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላለሁ ልሰርቅ ሂጄ ነበር እላቸዋለሁ? አይሆንም እንዲህማ ልላቸው አልችልም፤ እንዲሁም ልዋሻቸው አልችልም። እውነቱን የምናገር ከሆነ ሰዎች እኔን መጥላት ይጀምራሉ፤ ሌባ ብለውም ይጠሩኛል። በመስረቄም እቀጣለሁ አለ።
ሰውየው በዚያን ለሊት ላለመስረቅ ወሰነና ይህን መጥፎ ልማዱን ተወ። በቀጣዩ ቀን ወይን (አስካሪ መጠጥ) ለመጠጣት ፈልጐ ይህን ለማድረግ ባሰበ ጊዜ ለራሱ እንዲህ አለ:- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ቀን ምን አደረክ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ ልዋሽ አልችልም ደግሞ እውነታውን ብናገን ሰዎች ይጠሉኛል።
ምክኒያቱም ሙስሊም ወይን (አስካሪ መጠጥ) መጠጣት አይፈቀድለትም። እናም ወይን (አስካሪ መጠጥ) የመጠጣት ሀሳብን (ፍላጎቱን) ተወ።
በዚህ መንገድ ሰውየው መጥፎ ነገሮችን ለመስራት ባሰበ ጊዜ እውነትን ለመናገር የገባውን ቃል ኪዳን ያስታውሳል። እያለያለ አንድ በአንድ መጥፎ ልማዶቹን ሁሉ ተወ። ጥሩ ሙስሊምና ጥሩ ሰው ሆነ።
ሁልጊዜም እውነትን የምንናገር ከሆነ ጠንካራ ሙስሊም መሆን እንችላለን። የአሏህ ውዴታን ያስገኝልናል። የአሏህን ውዴታ ካገኘን አሏህ በጀነት ይመነዳናል።