Table of Contents

ክፍል አንድ

በባሪያ ንግድ ወቅት ያች ወጣት ኢትዮዺያዊት ሴት በረካ እንዴት መካ ውስጥ ለሽያጭ እንደበቃች ባይታወቅም እንዲሁም የዘርሃረጓ፤ እናቷ ማን እንደሆነች ፣ አባቷ ማንእንደሆነ ወይም ቅድመአያቶቿ ማን እንደሆኑ ባይታወቅም እሷን መሰል ወጣት ወንዶችና ሴቶች አረቦችም ሆኑ አረብ ያልሆኑ ነገርግን ተይዘው ወደ ባሪያ ገበያ ለሽያጭ የበቁ በርካቶች ነበሩ።

በመጥፎ የባሪያ ገዥዎች እጅ የወደቀ ባሪያ መጥፎ እድል የሚገጥመው ሲሆን አብዛሃኛዎቹም ጉልበታቸውን ከልክ በላይ ይበዘብዟቸዋል ከልክ በላይ በሆነ ግፍና በደል ይይዟቸዋል።

በዚህ ሁኔታ ላይ እድለኞች የሆኑ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ወጣት ኢትዮዺያዊት ሴት በረካ ከእድለኞቹ መካከል ስትሆን ደግና ቸር የነበረው የአብዱል ሙጦሊብ ልጅ አብዱሏህ የራሱ አደረጋት። በእርግጥም በቤቱ ውስጥ ብቸኛዋ አገልጋይ ሆነች።

አብዱሏህ አሚናን ባገባ ጊዜ በረካ (ረ.ዐ) ሁሉንም ጉዳዮቿን የምትጠብቅ እና የምትቆጣጠር ሆነች።

እንደ በረካ ገለፃ ሁለቱ ጥንዶች ከተጋቡ ከሁለት ሳምንታት ብኋላ የአብዱሏህ አባት ወደ ቤታቸው መጣና ከነጋዴዎች ጋር ወደ ሶሪያ ለንግድ እንዲሄድ አዘዘው።

አብዱሏህም ትዕዛዙን ተቀብሎ ሄደ። ይህን ተከትሎ አሚና በጥልቅ አዘነች፤ አለቀሰችም። ምን ያልተለመደ ነገር ነው! ገና ሙሽሪት ሆኜ በእጄ ላይ ያለው ሂና ሳይለቅ እንዴት ባሌ ለንግድ ወደ ሶሪያ ይሄዳል? ስትል አሚና በጣም አዘነች።

የአብዱሏህ መነጠል ልብ የሚሰብር ነበር። እናታችን አሚና በጭንቀት ላይ ሆና ራሷን ሳተች። በረካም እንዲህ ትላለች አሚና እራሷን ስታ ሳያት በጭንቀት እመቤቴ ሆይ! ስል ጮኹኩኝ።

አሚናም አይኖቿን ከፈት አድርጋ እያነባች ተመለከተችኝ። ማቃሰቷን አምቃ በረካ ወደ አልጋው ውሰጅኝ አለች። ይህን ተከትሎ አሚና ለረጅም ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ሆነች።

ማነንንም አታናግርም፤ ማንንም አትመለከትም፤ ያሽማግሌ ታላቅ ሰው አብዱል ሙጦሊብ ሲቀር። አብዱሏህ ተነጥሏት ከሄደ ከሁለት ወር ብኋላ አንድ ቀን ጧት ንጋት ላይ አሚና ጠራችኝ። ፊቷም በደስታ ይበራ ነበር።

እንዲህ አለችኝ በረካ ሆይ! ያልተለመደ (እንግዳ) የሆነ ህልም አየሁ። እመቤቴ! ደስ የሚል ነገር ነው? አልኳት። ብርሃን ከሆዴ ወጥቶ በመካ ዙርያ ያሉ ተራራዎችን ፣ ኮረብታዎችን እና ሸለቆዎችን ሲያበራ አየሁ።

እመቤቴ! የነፍሰጡርነት ስሜት ይሰማሻል እንዴ? አልኴት። አዎ በረካ! ነገርግን ሌሎች ሴቶች እንደሚሰማቸው የምቾት ማጣት ስሜት እይሰማኝም አለች። መልካም ነገር ይዞ የሚመጣ የተባረከ ልጅ ትወልጃለሽ አልኳት።

አብዱሏህ ከአሚና ከተለየበት ጊዜ አንስቶ በሐዘንና በትካዜ ላይ ወደቀች። በረካ (ረ.ዐ) ከጎኗ ሁና እያወራቻትና የተለያዩ ታሪኮችን እየተረከችላት ታፅናናት ነበር።

አብርሃ ተብሎ የሚጠራ የየመን ገዥ ከተማውን እያጠቃ ስለነበር አብዱል ሙጦሊብ ቤቷን ትታ ወደ ተራራው እንድትሰደድ ሲነግራት የበለጠ አዘነች።

አሚናም በጣም ሐዘን ላይ እንደሆነችና ወደ ተራራው ለመውጣት ደካማ እንደሆነች እንዲሁም አብርሃ ወደ መካ ገብቶ ካዕባን በፍፁም እንደማያጠፋውና በአሏህ የተጠበቀ እንደሆነ ስትነግረው በጣም ተበሳጨባት።

ይሁን እንጂ ከአሚና ፊት የፍርሃት ምልክት አይታይም ነበር።

በረካ እንዲህ ትላለች ቀንም ማታም ከጎኗ ነኝ። ሆኖም ከአልጋዋ ስር ስለነበር የምተኛው እያቃሰተች ባሏን ስትጠራ እሰማትታለሁ። ማቃሰቷ ይቀሰቅሰኝ ስለነበር ተነስቼ ላፅናናት እና ላጀግናት እሞክራለሁ።

ከፊሎቹ ነጋዴዎች ከሶሪያ በተመለሱ ጊዜ ቤተሰቦቻቸው በእልልታ ተቀበሏቸው። በረካ ስለአብዱሏህ ሁኔታ ለማወቅ ወደ አብዱል ሙጦሊብ ቤት ተደብቃ በሚስጥር ሄደች።

ነገርግን ስለእሱ ምንም ዜና አልነበረም። ወደ አሚና ተመልሳ ሄደች። ሆኖምግን እንዳታዝን እና እንዳትጨነቅ በማሰብ ያየቸችውንና የሰማችውን ነገር አልነገረቻትም።

በመጨረሻም ሙሉ ነጋዴዎች ተመለሱ፤ አብዱሏህ ግን እነርሱ ጋር አልነበረም። ብኋላ ላይ የአብዱሏህ መሞት ዜና በመጣ ጊዜ በረካ ከአብዱል ሙጠሊብ ቤት ነበረች።

እንዲህ ትላለች ዜናውን ስሰማ ጮኹኩኝ። ከዛ ብኋላ ምን እንደማረግ አላውቅም። እየጮኹኩ ወደ አሚና ቤት ሄድኩ። አብዱሏህ ተወዳጅ የነበረ፤ ለረጅም ጊዜ የጠበቀቅነው፤ መልከመልካም የመካ ወጣት፤ የቁረይሾች ኩራት ነበር።

አሚና ይህን አሳማሚ ዜና ስትሰማ ራሷን ሳተች። እኔም በመኖርና በመሞት አፋፍ መካከል ሆና ያለ ከአልጋዋ ጎን ሆኜ አስታመምኳት። እኔ ብቻ ስቀር ከአሚና ቤት ማንም አልነበረም። እናም ልጇን እስክትወልድ ድረስ ቀኑንም ሌሊቱንም ከጎኗ ሆንኩ።

ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተወለዱ ጊዜ በእጆቿ እቅፍ ያደረገቻቸው የመጀመሪያዋ በረካ ነበረች። ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ገላጣው በረሃ ሐሊማ ጋር በተላኩ ጊዜ በረካ ከአሚና ጋር ቆየች።

ከ5 ዓመት ብኋላ ወደ መካ መጡ፤ አሚናም በፍቅር በደስታ ተቀበለቻቸው። ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስድስት ዓመት ሲሞላቸው እናታቸው አሚና በያስሪብ የሚገኘውን የባሏን መቃወብር ልትጎበኝ ወሰንች።

በረካ እና አብዱል ሙጠሊብ ሊያግባቧት ቢሞክሩም አሚና ቆርጣ ስለተነሳች አልተቀበለቻቸውም። እናም አንድ ቀን ጧት ጉዞ ጀመሩ። ይሁእንጂ ልጇን ከሃዘን እና ከጭንቀት ለማዳን አሚና ለሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአባታቸውን መቃብር ልትጎበኝ እየሄደች መሆኑን አልነገረቻቸውም።

አብዛሃኛውን ጊዜም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከበረካ አንገት አካባቢ እጃቸውን ተደግፈው ይተኙ ነበር። አሚና የአብዱሏህን መቃብር በጎበኘባቸው ጊዜ ውስጥ የበለጠ በሃዘን ተጎሳቆለች።

ወደ መካ እየተመለስን እያለ አሚና ባሳሳቢ ሁኔታ ታመመች። በያስሪብ እና በመካ መከካል አል-አብዋ ተብሎ በሚጠራ ቦታ የአሚና የጤንነት ሁኔታ በፍጥነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ።

አንድ ቀን ምሽት ሰውነቷ ግሎ በሚተናንነቅ ድምፅ በረካ! በረካ! ስትል ጠራችኝ።

በረካ እንዲህ ስትል ትተርካለች:- በረካ ሆይ! በቅርቡ ይህን አለም እነጠላለሁ፤ ልጄን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተንከባከቢው፤ በሆዴ ውስጥ ሆኖ ያለ አባቱን አጣ አሁን ደግሞ እናቱን ሊያጣ ነው። አንች እናት ሁኝው፤ አትተይውም ስትል በጆሮየ ሹክ አለችኝ።

ልቤ ተንቀጠቀጠ እናም ማልቀስ ጀመርኩ። በእኔ ለቅሶ ህፃኑም ማልቀስ ጀመረ። እራሱን ወደ እናቱ እጆች ወረወረና በአንገቷ ጥምጥም አለ። እንዴ አቃስታ አሸለበች።

በረካ አምራ አለቀሰች። በእጆቿ ከአሸዋው መቃብሯን ቆፍራ ቀበረቻት። ከልቧ በቀረው እንባዋ መቃብሯን አራሰችው። በረካ ከሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ወደ መካ ተመልሳ በአያታቸው እንክብካቤ ስር እንዲሆን አደረገች።

ልጁን ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ከቤቱ ሆና የቆየች ሲሆን አብዱል ሙጦሊብ ከሁለት ወር ብኋላ ሲሞት ልጁን ይዛ ወደ አጎቱ አቡጧሊብ ሄደች። እናም ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እስኪያድጉና ኸድጃ (ረ.ዐ) እስኪያገቡ ድረስ ተንከባክባ ፣ ፍላጎታቸውን አሟልታ አሳደገቻቸው።

በረካ ከሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ከኸድጃ ቤት መኖር ጀመረች። በፍፁም ትቼው አላውቅም እሱም በፍፁም ትቶኝ አያውቅም ትላለች። አንድ ቀን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጠሩኝና እናቴ ሆይ! አሁን አግብቻለሁ አንቺ ደግሞ እስካሁን አላገባሽም የሆነ ሰው ቢመጣና ለጋብቻ ቢጠይቅሽ ምን ታስቢያለሽ? አሉኝ።

በረካም ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) እየተመለከተች በፍፁም ትቼህ አልሄድም። እናት ልጇን ትተዋለች እንዴ? አለች። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ፈገግ አሉና ግንባሯን ሳምምምም! አደረጓት።

ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ሚስታቸውን ኸድጃ(ረ.ዐ) እየተመለከቱ ይች በረካ ከእናቴ ቀጥሎ እናቴ ናት። ቀሪ ቤተሰቤ እሷናት አሉ።

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top