በአንድ ወቅት ወላጆች ለልጃቸው ሚስት ሲፈልጉ ቆይተው “የሸህ እገሌን ልጅ ልንድርህ ነውና ሂድ እያት” አሉት። ገና እንዳያት ወደዳት። በሌላ ቀን ፈቃደኝነቷን ሊጠይቅ ሄዶ ስለትዳር ሀሳባቸዉ እና ስለወደፊት ዓላማቸው አወሩ።
ጥቂት ጊዜ አንገታቸውን ደፍተው ከቆዩ በኋላ “ቁርአን ምን ያህል ሐፍዘሃል?” ስትል ጠየቀችው። “አይ ብዙ አላፈዝኩም፤ ምናልባት ካሁን በኋላ አሃፍዝ ይሆናል። ግን መልካም የአላህ ባርያ የመሆን ጉጉት አለኝ።” አለ።
ጉጉቱን በቀልቧ ያዘችለት። “አንቺስ ሐፍዘሻል?” ሲል ጠየቃት። “የአማን ጁዝ ሐፍዣለሁ።” አለችው።
እውነቱን የነገራት መሆኑን ባወቀች ጊዜ ቀልቧ ወደደው። አሳዝኗትም፤ ወዳዉም ጥያቄዉን ተቀበለችው።
ከተጋቡ በኋላ ቁርኣን እንዲሳሃፍዛት ጠይቃው ከሱረቱ “መርየም” አብረው ጀመሩ።
ሒፍዙን ሳያቆሙ ቀጠሉ። በመጨረሻም ሁለቱም ቁርኣንን በቃላቸው ሸምድደው የሒፍዝ ሰርተፊኬት አገኙ። አላረፈችም፤ አሁን ደግሞ “ሐዲሥ ለምን አንሐፍዝም?” ብላ ቡኻሪን አጥንተው ጨርሰዋል።
በዚህ መሃል አንድ ቀን ለዚያራ ወደ ወላጆቿ ቤት ሄደው ሳለ ባልየው በኩራት ለአባቷ “አባ..አ..አንድ ያልነገርንዎት ነገር አለ። አልሐምዱሊላህ ልጅዎ ቁርኣን ሐፍዛለች።” አላቸው። አማቹ በአግራሞት አዩትና ወደ ጓዳ ገብተው የልጃቸዉን የምስክር ወረቀቶች አምጥተው አሳዩት።
አማች ባየው ነገር ደነገጠ። ልጅቷ ሳታገባው በፊት አስቀድማ ሐፍዛለች ለካ። ከቁርአን አልፋ ኩቱቡ ሲታንም ጭምር የጨረሠች ስለመሆኑ ማስረጃ አላት። ባል ተገረመና ዝም አለ።
ያኔ እንዲያ ያደረገችው የባሏ ሞራል እንዳይነካ ፈርታ ነበር። ኢልም የለህም፤ ቁርአን አላፈዝክም ብላ አላጣጣለችዉም፤ በእውቀቱ ደረጃ አልናቀችዉም።
እውነቱን በነገራት ጊዜ ከልቧ አስገባችው፤ ፈቀደችዉም። እንደሷ ቁርአን እንዲሐፍዝም ስለፈለገች በዚያ መልኩ አስጀመረችው። ሱረቱ አማን ሐፍዣላሁ ያለችውም እውነቷን ነበር አልዋሸችም። ምክኒያቱም ሱረቱ አማ ከ30 የቁርኣን ጁዞች አንዱ ነዉና።