መግቢያ
የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ዛሬ ላይ ዓለምን እያነጋገረ ካለ አንኳር ጉዳይ አንዱ ነው። ከታሪካዊ ጭቆና ነፃ ወጣን በሚል ዛሬ በፌሚኒዝም ፣ በነፃነት እና ፍፁም እኩልነት ስም የተለያዩ ጥሪዎች ይደመጣሉ።
እነዚህ ዘመናዊ እሳቤዎች እውነተኛውን የሴቶች ክብር ይመልሳሉ? ወይስ ከተፈጥሯቸው እና ከመለኮታዊ ህግጋት ጋር ይጋጫሉ? ይህ ጽሑፍ ከጥንታዊ ፍልስፍናዎች እስከ ወቅታዊ ንቅናቄዎች ድረስ ያሉትን የይገባኛል ጥያቄዎች ይመረምራል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የእስልምና ሸሪአ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን ሚዛናዊ ፍትህ እና የላቀ ክብር በማስረጃ ያቀርባል።
የሴቶች ክብር እና የነበረው የተዛባ አመለካከት በታሪክ ውስጥ
በጥንት ዘመን እና በበርካታ የሰው ልጅ ስልጣኔዎች ውስጥ ሴቶች ምንም አይነት ሰብዓዊ ክብር እንኳ አይሰጣቸውም ነበር። ይልቁንም ችላ የተባሉ ፣ ለምንም ነገር ግምት የማይሰጣቸው እና ምንም አይነት መብትም ሆነ ብቁነት የሌላቸው ተደርገው ይታዩ ነበር።
የሰው ልጅ መሆናቸው ተረስቶ እንደማንኛውም ንብረት ይሸጡና ይለወጡ ነበር። በደረጃም ከወንዶች ያነሱ ፍጡሮች እንደሆኑ ይታመን ነበር።
ይህ አይነቱ አካሄድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ ስልጣኔዎች እና ባህሎች ውስጥ የሴት ልጅ ሚና ዝቅ አድርጎ የሚመለከት እና የሚንቅ እና የሚያንቋሽሽ መሆኑን ቀጠለ።
ምንም እንኳ የምዕራቡ አለም በኋላ ላይ ለውጥ ቢያመጣም፤ ከኢንፓየር ግዛቶች እና ከቤተክርስቲያናት የጭቆና ቀንበር የተላቀቀ የሚመስል የነፃነት ጭላንጭል ታየ።
ይህ ለውጥ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሴቶች እና ለጉዳዮቻቸው አልደረሰም ነበር። ይህ የተዛባ አመለካከት በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው፦
የጥንት ፍልስፍናዊ እይታ
በድሮ ጊዜ እንደ ሶቅራጥስ ፣ ፕላቶ እና አርስቶትል ያሉ ፈላስፎች ሴቶችን ይንቁ እና ያንቋሽሹ ነበር። በእነሱ ውስጥ ክብር ወይም መብት የሚባል ነገር አይታያቸውም ነበር።
በተዛቡ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች የነበረው ገጽታ
- በሒንዱይዝም፡ አንዲት ሴት ከወላጆቿ የመውረስ መብት የላትም። ባሏ ቀድሟት ቢሞት፤ ከእሱ በኋላ መኖሯ ዋጋ የለውም ተብሎ ስለሚታሰብ አብራ ተቃጥላ እንድትሞት ትገደዳለች።
- በአይሁድ እና በክርስቲያን እምነት፡ ሴቶች ያላቸው ክብር ዝቅ ያለ ነበር። የክፋት ፣ የኃጢያት እና የብልግና ሁሉ መሰረት ተደርገው ይከሰሳሉ። እንደ እርኩስ እና ቆሻሻ ይቆጠሩ ነበር።
እነዚህ ሃሳቦች የመጡት ከተዛቡ እና ከተንሻፈፉ መጽሐፍቶቻቸው ፣ ከሃይማኖታቸው እና ከጉባኤዎቻቸው ማደማደሚ ሃሳቦች የመጡ ሲሆን በቀሳቅስቶች እና በቤተክርስቲያናት የተደገፉ ናቸው።
የዘመናችን እሳቤዎች እና የነፃነት ጥሪ
በዚህ ሰለጠነ በሚባለው ዘመን፤ የብዙኃኑን አመለካከት እና ባህሪ ላይ ተፅዕኖ ያደረጉ የተለያዩ ፅንሰ-ሀሳቦች (ቲዎሪዎች) ብቅ ብለዋል። ከእነዚህም መካከል፦
ዘመናዊነት እና ድህረ ዘመናዊነት
ዘመናዊነት የሰውን ልጅ የፍጥረተ አለሙ ሁሉ ማዕከል ያደርጋል። ከመለኮታዊ ራዕይ እራሱን ነፃ እንደሚያደርገው ፣ እሱ እራሱ ሃይል እንዳለው እና አዕምሮው ስለ አካባቢው እና ስለ ፍጥረተአለሙ ማብራሪያ እንደሚሰጠው ያስረዳሉ። አብዛሃኛው ሃሳቦች እና ተረድኦዎች ከዘመናዊነት ፅንሰ ሃሳብ የመነጩ ናቸው።
ምክኒያታዊነት
ይህ አዕምሮን እና ደረጃዎቹን ከፍ አድርጎ የመምረጥ እና የሚያሞግስ ነው። እንደነሱ ገለፃ የሰውን ልጅ የፍጥረተ አለሙ ማዕከል እንደሆነ ያስባሉ።
ነፃነት እና ግለኝነት
የሰው ልጅ ጉዳዮችን እና ለእሱ ተስማሚ በሆነ መንገድ እጣፈንታውን ይወስናል ብሎ በማሰብ ለሰብአዊ መብት አፅንኦት መስጠት ማለት ነው።
ዳርዊኒዝም
የሰው ልጅ አፈጣጠር መነሻን በተመለከተ ከብዙ ሚልዮን አመት በፊት አንስቶ አሁን ያለበትን ቅርፅ እስኪያገኝ ድረስ ያለው የሰው ልጅ እድገት የዝግመተ ለውጥ ሂደት እንደሆነ የሚናገር ፅንሰ ሃሳብ ነው።
የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ፡ ከፌሚኒዝም እስከ ተባበሩት መንግስታት ስምምነት
ሴቶች በከፋ ጭቆና እና በደል ይሰቃዩ ከነበረበት አውሮፓ የሴቶች ነፃነት ሃሳብ ብቅ አለ። የነፃነት እና የፍትህ መፈክሮች ከፍ ብለው ተውለበለቡ። ይህን ተከትሎ ሴቶች ሰብአዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ፓለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መብቶች ተሰጣቸው።
ነገርግን ፍላጎቶቻቸው ሃይማኖታዊ ድጋፍ እና መዋቅር አልነበረውም እና በድጋሚ ከሃይማኖት እና ከቀኖናዎቹ ነፃ እንዲወጡ ጥሪያቸውን ወደዚያ አዞሩ። ይህ ሁሉ ከወንዶች የበላይነት ነፃ እንሆናለን በሚል ሰበብ እና ሽፋን ነበር።
ከሴቶች ነፃነት ሃሳብ እና ጥሪ ጋር የተያያዘው ሃይማኖትን ከሁሉም የህይወት ጉዳዮች መነጠል እና ሴኩላሪዝምን እንደ አንድ የሕይወት መንገድ መተግበር ነው። በተለይ ደግሞ ሃይማኖታዊ ቁጥጥሮችን እና አስተምህሮቶችን ማለት ነው።
የፆታ እኩልነት እና ፌሚኒዝም
የፆታ እኩልነት ጥሪ መጀመሪያ ላይ ያተኮረው በእኩል የመማር ፣ የመስራት እና በፖለቲካ የመሳተፍ መብቶች ላይ ነበር። በሴቶች ላይ የሚደርስ አድልኦ እና መድሎ ሁሉ እንዲጠፋ የሚጠይቅ ነው።
ነገር ግን የእኩልነት ጥያቄው ከመሰረታዊ አውዱ ወጥቶ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ልዩነት የማይቀበል እና ሁለቱ ፆታዎች በሁሉም ነገር አንድ ናቸው የሚል አዝማሚያ ያዘ።
ፌሚኒዝም እና መርሆቹ
የሴቶች ነፃነት እና የፆታ እኩልነት ሃሳብ ‹‹የሴቶች እኩልነት ጠበቃ›› ወይም ፌሚኒዝም ተብሎ ይጠራል። ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ብዙ ፓለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ተግባራትን የሚፈፅሙ ንቅናቄዎች ተፈጥረዋል።
የሴቶች እኩልነት ሃሳብን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እና ሃሳቦችን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ሞክረዋል።
የፌሚኒዝም መርሆዎች
- ፍፁም ነፃነት ያለው ቤተሰብ ሳይሆን ግላዊነት ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ ሃሳብ ውስጥ ነው፡፡
- ወንድ እና ሴት የሚለውን ተፈጥሯዊ ፆታ በማግለል “ማህበራዊ ፆታ” (Gender) የሚለውን ሀሳብ መቀበል።
- የሴትን ልጅ አካል ባለቤትነቱን ለእሷ መስጠት እና ያለማንም ተቆጣጣሪነት እና ያለ ገደብ የፈለገችውን እንድታደርግበት ሙሉ መብት መስጠት
- የአባውራ የበላይነትን ውድቅ በማድረግ የአባትን ሚና በቤተሰብ ውስጥ ማጥፋት።
- ተሟጋችነት፡ ከሴቶች መብት ጠበቃ ንቅናቄ ውስጥ ግብረሶዶማዊነት ፣ ፅንስ የማስወረድ ህጋዊነት ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚያጠኑ ሃሳቦች እና አለማቀፋዊ እና ቀኖናዊ እሴቶች ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግስታት ስምምነት ፡ ፍፁም እኩልነት እና ከሸሪአ ጋር ያለው ቅራኔ
በ1979 ዓ.ል በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሴቶች ላይ የሚደርስ አድልኦ እና መድሎን ሁሉ ለማጥፋት በአለም አቀፍ ስምምነቱ ሐገራት እንዲያፀድቁላቸው እና ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
የስምምነቱ “የፍፁም እኩልነት” መርህ
ስምምነቱ በሁሉም ዘርፍ ወንዶች እና ሴቶች ፍፁም እኩልነት እና አቻነት አላቸው የሚል ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና የህግ ዘርፎች እና ሌሎች ዘርፎች ላይ አቻ እና ፍፁም እኩልነት አላቸው ብሎ ያምናል።
ይህ መርህ ከነባራዊ እውነታው የተቃረነ ፣ ከሰማያዊ ህግ ጋር የተፃረረ ፣ ከቁርአን እና ከሱና ጋር ተቃራኒ የሆነ እና ጤናማ አዕምሮ የሚፈልገው ያልሆነ ነው። ከቁርአን ጋር የሚቃረን የመሆኑ ማሳያ ተከታዩ የአሏህ ንግግር ነው።
አሏህ (ሱ.ወ) በቅዱስ ቁርአኑ እንዲህ ይላል፦
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ኢምራን: 36)
“ወንድ እንደ ሴት አይደለም።”
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኒሳዕ: 34)
“ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው።”
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ: 228)
“ለወንዶችም (ጣጣቸውን ስለሚሸከሙ) በእነሱ ላይ ብልጫ አላቸው።”
ከሱና ጋር የሚቃረን መሆኑን የሚያመለክተን ደግሞ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸው ነው
አል-ቁርአን
(ቡኻሪ 893 ፣ ሙስሊም 1829)
‹‹እያንዳንዳችሁ ለምትጠብቁት ነገር ሃላፊነት አለባችሁ። ወንድ በቤተሰቡ ውስጥ እረኛ ነው። በእነሱ ላይ (በቤተሰቦቹ) ሃላፊነት አለበት። ሴት በባሏ ቤት ውስጥ እረኛ ናት። በምትጠብቀው ነገር (በቤተሰቦቿ) ላይ ሃላፊነት አለባት።››
ይህ ብዙ ማብራሪያ አይፈልግም፤ ምክኒያቱም ይህ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ልዩነቱ በችሎታ እና የህይወት ኡደት እንዲቀጥል በማድረግ ሂደት ውስጥ ልዩነት ይፈጥራልና ነው።
የተሟላ እኩልነት እና አቻነትን ለማሳካት መሞከር ከወንዶች እና ከሴቶች አፈጣጠር ጋር የሚቃረን ነው።
የተባበሩት መንግስታት ስምምነት እና በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለ ጥላቻ
የተባበሩት መንግስታት ስምምነት እና የሴቶች መብት ተሟጋች ንቅናቄ የሚያሳየው በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ግኑኝነት እንዲያበቃ የሚፈልጉት የፉክክር እና የታሪካዊ ግጭት መስተጋብር አካል እንደሆነ ነው።
በወንዶች እና በሴቶች መካከል ፍፁም እኩልነት እንዲመጣ በማድረግ ይህ ባላንጣነት እንዲያበቃ ይፈልጋሉ። ለወንድ ልጅ ጥቅም የሆነ ሁሉ ለሴት ልጅ ጉዳት እንደሆነም ያስባሉ።
በእርግጥ ይህ ጠባብ እይታ ነው። በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ግኑኝነት አንዱ አንዱን የሚተካበት ሳይሆን አንዱ ያንዱን ክፍተት የሚሞላበት ፣ ጥላቻ እና ፍክክር ሳይሆን ትብብር እና መደጋገፍ የሚሰፍንበት ነው።
እያንዳንዳቸውም የየራሳቸው ሚና እና ተግባር አላቸው። ህይወትን ለማስቀጠል በስምምነት እና በመሸፋፈን መርህ በጋራ እውቀት ፣ ፍቅር እና መተዛዘን የሰውን ልጅ ዘር ያስቀጥላሉ። አሏህ እንዲህ አለ፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ኹጅራት: 13)
“እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድ እና ከሴት ፈጠርናችሁ። ትተዋወቁም ዘንድ ጎሳዎች እና ነገዶች አደረግናችሁ። በእርግጥ ከእናንተ መካከል አሏህ ዘንድ በላጩ አሏህን ፈሪው ነው።”
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሩም: 21)
“ለእናንተ ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደ እነሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ ፣ በመካከላችሁም ፍቅርን እና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶች ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ተአምራቶች አሉ።”
ከዚህ በተጨማሪ በህይወት ውስጥ ሁለቱ ፆታዎች የሚጫወቱት ሚና መለያየት የሚያመለክተው ምንም አይነት በደል ፣ ኢፍትሃዊነት ሳይኖር መብቶቻቸው እና ሃላፊነቶቻቸው የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ተጨማሪ ሃላፊነት በተጨማሪ መብቶች ይካካሳል።
በወንዶች እና በሴቶች መካከል እኩልነት እንዲኖር ሸሪአ ያስተምራልን?
የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ በሸሪአ ሲታይ፤ እስልምና በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ፍፁም እኩል መሆናቸውን ይደነግጋል፦
- በሰውነታቸው እና በሞራል ልዕልናቸው
- በኃላፊነት እና አደራን በመሸከም
- በዚህ ዓለምም ሆነ በመጭው ዓለም በሚያገኙት ምንዳ
- መብቶቻቸው በመከበር
- የአምልኮ ስርአቶችን በመፈፀም
ሸሪአ የሚያረጋግጠው ፍትህ (ልዩነትን ማክበር)
ሸሪአ ፍፁም አቻነትን ሳይሆን ፍትህን ነው የሚያስተምረው። በአካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ውቅራቸው ምክንያት በመካከላቸው ያለውን አዎንታዊ ልዩነትም ያረጋግጣል። ለምሳሌ፦
- ሴቶች በአቋም ድክመት ምክንያት ጅሃድ (ተጋድሎ) አይጠበቅባቸውም።
- በወር አበባ እና በወሊድ ደም ጊዜ አይሰግዱም አይፆሙም (በኋላ ቀዷ ያወጣሉ)።
- ምንም እንኳ ሃብታም ብትሆን የቤት ወጪን መሸፈን አትገደድም።
ይህ ተጨማሪ ኃላፊነትን በተጨማሪ መብቶች ማካካስ ሲሆን የፍትህ ዋናው መሰረትም ይኸው ነው።
የሸሪአ የውርስ ፍትህ
በእስልምና ህግ መሰረት ሴቶች በውርስ የሚደርስባቸው ግፍ የለም። አንዳንዴ ሴት ከወንዱ ድርሻ አነስ ያለውን ትወስዳለች። አንዳንዴ እኩል እና ተመሳሳይ ድርሻ ትወስዳለች።
አንዳንዴ ደግሞ ከእሱ ድርሻ በላይ የምትወርስበት እና እሱ ሳይወርስ እሷ የምትወርስበት ሁኔታ አለ።
ይህ የአሏህ ድንጋጌ እና የዕውቀት ሰዎች ማብራሪያ መጽሐፍት ውስጥ በዝርዝር የተቀመጠ ነው።
ሸሪአ ለሴቶች ያረጋገጠው ክብር እና መብቶች
እኩል ምንዳ፡ ሴት ልጅ በሸሪአ የተጠበቀች እና የተከበረች ናት። አሏህ እንዲህ የይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ጋፊር 40)
“መጥፎ የሰራ ሰው ቢጤዋን (አምሳያዋን) እንጅ አይመነዳም። አማኝ ሆኖ ከወንድ ወይም ከሴት በጎ (መልካም) ነገር የሰራ ሰው ጀነት ይገባል። በእሷ ውስጥም ያለ ቁጥጥር ይመገባሉ።”
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ትርሚዚ 11)
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹በእርግጥ ሴቶች የወንዶች እህቶች (አቻዎች) ናቸው።›› ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሴት ልጅ የፈለገ ሃብታም ብትሆን ወዳ እና ፈቅዳ ካልሆነ በቀር አንድ ብር ማውጣት አይጠበቅባትም። ይልቁንም የሴቷ ጠባቂ (አባቷ ወይም ባሏ) የመጠለያዋን ፣ የመጠቃቀሚያዋን እና ሌሎች ወጭዎቿን መሸፈን ይገደዳል።
አባቷም ሆነ ባሏ እንኳ ቢሆኑ በእሷ ገንዘብ ላይ ተቆጣጣሪ የለባትም። ሴት ልጅ የመሸጥ ፣ የማጫረት ፣ የንግድ ሽርክና የመፍጠር ፣ ዋስትና የመስጠት እና የመቀበል መብት አላት።
ማጠቃለያ
የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ በሁለት የተለያዩ ሚዛኖች ላይ ይገኛል። ፌሚኒዝም እና የተባበሩት መንግስታት ስምምነት “ፍፁም አቻነትን” ሲጠይቁ ሸሪአ ደግሞ “ፍፁም ፍትህን” ያረጋግጣል።
እስልምና ለሴት ልጅ ከተፈጥሮዋ ጋር የሚስማማ ክብር ፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና ጥበቃ ሰጥቷታል። እውነተኛው የሴቶች ክብር እና መብት የሚረጋገጠውም በዚህ መለኮታዊ ፍትህ ውስጥ ነው።
እርስዎስ ምን ያስባሉ? እውነተኛው የሴቶች ክብር በፍፁም እኩልነት ወይስ በመለኮታዊ ፍትህ ውስጥ ይገኛል? አስተያየትዎን ከታች ያጋሩን።




Share