መግቢያ
በዓለም ዙሪያ ስለሴቶች መብት ዛሬ ሲወራ፣ እስልምና ከ1400 ዓመታት በፊት ምን ድንጋጌ አስቀመጠ? ይህ ጽሑፍ የሴት ልጅ መብት በእስልምና ያለውን የላቀ ደረጃ ይዳስሳል። ሴቶች በጃሂልያ እና በሌሎች ጥንታዊ ፍልስፍናዎች (እንደ አርስቶትል) እንደ ጎደሎ ፍጡር ሲቆጠሩ፣ እስልምና ክብራቸውን መልሷል። ጽሑፉ እስልምና ለሴቶች ያረጋገጠላቸውን ሃይማኖታዊ እኩልነት፣ እንዲሁም አስገራሚ የሲቪል፣ የማህበራዊ እና የትዳር መብቶችን (እንደ ውርስ፣ ንብረት ባለቤትነት እና የመማር መብት) ከማስረጃ ጋር ያብራራል።
እስልምና ለሴቶች ያለው ልዩ እንክብካቤ እና ክብር
የእስልምና ሃይማኖት በመለኮታዊ አስተምህሮቶቹ እና ጥበባዊ መመሪያዎቹ ለሙስሊም ሴት ልዩ እንክብካቤ ያደርጋል፤ ክብሯን ይጠብቃል ፣ ልዕልናዋንና ደስታዋን ያረጋግጥላታል። ከጥርጣሬ ፣ ከፈተና እና ከክፉ ነገር ሁሉ አርቆ ምቹ እና የተደላደለ ህይወት አዘጋጅቶላታል። ይህ እንክብካቤ ብዙ መልክ እና ቅርፅ አለው።
እስልምና ለሴቶች ሰብዓዊነትን ፣ ክብርን እና የላቀ ደረጃን ሰጥቷቸዋል። ሴት ልጅ እናት ፣ ሚስት ፣ ልጅ ናት። ለእሷ ማዘንን ፣ ደግ መሆንን እና ልዩ ትኩረት መስጠትን አዟል። በአንጻሩ ደግሞ የሴቶችን ሚና የሚቀንሱ ፣ የሚያዋርዱ እና የሚያንቋሽሹ የተዛቡ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ትውፊቶችን በሙሉ ይዋጋል።
ከጃሂልያ ጨለማ ወደ እስልምና ብርሃን
የእስልምና ብርሃን ከመምጣቱ በፊት የነበረውን የድንቁርና (ጃሂልያ) ዘመን ዑመር ኢብኑል ኸጧብ (ረ.ዐ) እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
ቡኻሪ 4913፣ ሙስሊም 1479
“በአላህ ይሁንብኝ በጃሂልያ ውስጥ ሴቶችን እንደ ጉዳይ አንቆጥራቸውም ነበር፤ አላህ የገለጠውን ነገር እስኪገልጥ እና የሰጠውንም እስኪሰጥ ድረስ።”
እስልምና ከ1400 ዓመታት በፊት የሴትን ልጅ ደረጃ ከፍ አድርጓል፤ በእነሱ ላይ የተቃጣን በደል ሁሉ ሽሯል። በብዙ ዘርፎችም ከወንዶች ጋር እኩል አድርጓቸዋል። ከእነዚህ በደሎች መካከል፡-
- የንብረት ባለቤት መሆን እና መውረስ ይከለከሉ ነበር።
- ሚስት ባሏ ሲሞት እንደ ዕቃ ትወረስ ነበር።
- ከአስክሬኑ ጋር አብራ እንድትቃጠል ወይም እንድትቀበር ትገደድ ነበር።
- ትሸጥ እና ትለወጥ ነበር (ይህ ተግባር እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በእንግሊዝ ውስጥ እንኳ ነበር)።
ቀደምት ህዝቦች ለሴቶች የነበራቸው ንቀት ሴቶችን ከሰውነት ደረጃ የሚያስወጣቸው ፅንፍ የያዘ ነበር። ሴቶች በጃሂልያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰለጠኑ በሚባሉ ህዝቦች ዘንድም ይናቁ ነበር፡-
አርስቶትል (የግሪክ ፈላስፋ)፡ “ሴት ልጅ ያልተሟላች ጎደሎ ፍጡር ናት። ተፈጥሮም ከፍጥረቶች ሁሉ ዝቅ ያለ ቦታ ላይ አስቀምጣታለች።” ሶቅራጥስ፡ ከተመረዘ ዛፍ ጋር ያነጻጽራታል።
በአንድ ወቅት ሮም ውስጥ በተካሄደው ታላቅ ጉባኤ ሴት ልጅ ነፍስም ሆነ ዘላላማዊነት የሌላት እና ከዚህ አለም ህይወት ባሻገር የማትኖር እርኩስ ናት። ስጋ አትበላም ፣ አትስቅም ፣ አታወራም የሚል ማደማደሚያ አስቀምጠው ነበር።
ፈረንሳዮች ደግሞ በ586 አመት ውስጥ ስብሰባ ሲያካሂዱ ‹‹ሴት ልጅ ሰው ናት አይደለችም? ነፍስ አላት የላትም?›› በሚል ሃሳብ ዙሪያ ተወያይተው ሰው ከሆነች ከወንድ ልጅ ጋር እኩል ደረጃ አላት ልንል ነው የሚል ሙግት ገጥመው በመጨረሻ የሰው ልጅ ናት ነገርግን ወንድን ለማገልገል የተፈጠረች ናት የሚል ማደማደሚያ ላይ ደረሱ።
የፆታ እኩልነት በእስልምና
እስልምና የጥበበኛው አላህ ሃይማኖት ነው። ከአላህ ፍትህ አንዱ በሚለያዩበት ጉዳይ እኩል አለማድረጉ ፣ በሚመሳሰሉበት ጉዳይ ደግሞ ልዩነት አለማድረጉ ነው።
በእስልምና ህግ ወንዶች እና ሴቶች በአፈጣጠር እና በሰብዓዊነት እኩል ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱ አን-ኒሳእ፡ 1
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ያነን ከአንዲት ነፍስ (ከአደም) የፈጠራችሁን ከእርሷም መቀናጆዋን (ሐዋን) የፈጠረው ከእነሱ ብዙ ወንዶችን እና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ። ያነንም በእሱ የምትጠየቁበትን አሏህን እና ዝምድናዎችንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ። አሏህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና።”
በሚለያዩበት ተፈጥሯዊ ብቃት እና ኃላፊነት ግን ልዩነትን ያደርጋል። ይህ የፍትህ መገለጫ እንጅ የመበላለጥ ጉዳይ አይደለም።
ሃይማኖታዊ እኩልነት
እስልምና ወንዶች እና ሴቶችን በሃይማኖታዊ ተግባራት እና ግዴታዎች ፣ በሽልማታቸው እና በቅጣታቸው በዚህ አለም እና በመጭው አለም ህይወት እኩል አድርጓቸዋል። አሏህ እንዲህ አለ፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ነህል 97)
“ከወንድ ወይም ከሴት አማኝ ሆኖ በጎ የሰራን መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን። ይሰሩትም ከነበሩት ነገር በመልካም ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።”
ሃያሉ አሏህ እንዲህ አለ፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ኒሳእ፡ 124)
“ከወንድ ወይም ከሴት እሱ አማኝ ሆኖ ከበጎ ስራዎች አንዳችን የሚሰራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ። በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ እንኳ አይበደሉም።”
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(አቡዳውድ 236)
በአንድ ወቅት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በህልሙ ግኑኝነት ያደረገ መሆኑን ሳያስታውስ ረጥቦ ስለ ተነሳ ሰው ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ አሉ፡ ‹‹መታጠብ ይገባውል አሉ።›› በህልሙ ግኑኝነት ሲያደርግ አይቶ ነገርግን ምንም አይነት ምልክት ስላላገኘ ሰው ተጠይቀው ሲመልሱ ደግሞ እንዲህ አሉ፡ ‹‹መታጠብ አይጠበቅበትም አሉ።›› ኡሙ ሱለይም ‹‹ሴት ያን ካየችስ ገላዋን ትታጠባለችን?›› አለች። እሳቸውም ‹‹አዎ! ሴቶች የወንዶች እህቶች ናቸው›› አሉ።››
በእስልምና ታሪክ የሴቶች ሚና
በአሏህ መልዕክተኛ መልዕክት ያመነችው የመጀመሪያዋ ሴት ነበረች። እሷም የሙዕሚኖች እናት የሆነችው ኸድጃ (ረ.ዐ) ናት።
በእስልምና ታሪክ ውስጥ ሴቶች ደማቅ እና አንፀባራቂ ምሳሌን ፅፈው አልፈዋል። በመልካም ባህሪያቶቻቸው ፣ ጥልቅ በሆነ እውቀታቸው እና የእስልምናን መልዕክት በመረዳት አቅማቸው በደንብ ይታወቃሉ። በተለያዩ ዘርፎች ፣ በሃይማኖታቸው ፣ በሳይንስ እና በትምህርት የላቁ ስመጥሮች ነበሩ። ከእነሱ መካከል ደግሞ በጣም የምትታወቀው የምዕመናን እናት የሆነቸው አኢሻ (ረ.ዐ) ናት።
ሴቶች ልክ እንደ ሐጅ እና ኡምራ ሁሉ ግዴታ ፣ የተወደደ እና የተፈቀደ በሚለው ሁክም መሰረት በህብረት ሶላት ፣ የዝናብ ልመና ሶላት ፣ በሁለቱ ኢዶች በጀመአ (ህብረት) ሶላት ፣ በጁምአ ሶላት ከወንዶች ጋር አብረው ይሳተፋሉ። ከዚህ በተጨማሪ ወደ እስልምና ጥሪ እንዲያደርጉ ፣ በመልካም እንዲያዙ እና ከመጥፎ ነገር ሁሉ እንዲከለክሉ ታዘዋል። ብዙ ሃይማኖታዊ ተግባራትን እንዲፈፅሙ ታዘዋል። ይህ የሚያመለክተው ሁለቱም ፆታዎች በሃይማኖት ጉዳይ እኩል መሆናቸውን ነው። ብቸኛው ልዩነታቸው ያለው በእነሱ መካከል ያለው የሞራል ደረጃ ብቻ ነው።
በሚና መለያየት ውስጥ ያለው ጥበብ
ይህ የእኩልነት መርህ ከተፈጥሮ ልዩነቶች ጋር ተዳምሮ በሚዛናዊነት እያንዳንዱ ፆታ የራሱን ተልዕኮ እንዲወጣ ያደርጋል።
- ወንድ፡ የሴትን እና የልጆችን ወጪ የመሸፈን፣ ቤተሰቡን የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ አለበት።
- ሴት፡ በቤቷ፣ በባሏ እና በልጆቿ ላይ ያተኮረ ኃላፊነት አለባት።
የእኩልነት መርህ በሃይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ ሁለቱ ፆታዎች እንደጥቅል በተቀመጡ በተፈጥሮ ያላቸውን ልዩነትም ከግምት ውስጥ ያስገባል። ከዚህ የሚገኘው ውጤት በተልዕኮዎቻቸው መለያየት ነው። እያንዳንዱን ግለሰብ በትክክለኛው እና በሚገባው ቦታ ላይ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ በህይወት ውስጥ ውህደትን ይፈጥራል። ወንድ የሴትን እና የልጆችን ወጭ የመሸፈን ግዴታ አለበት። እነሱን መጠበቅ እና ቤተሰቡን መንከባከብ አለበት። ሴት ደግሞ በቤቷ ፣ በባሏ እና በልጆቿ ላይ ሃላፊነት አለባት። ልትወጣው የሚገባ የራሷ የሆነ ሃላፊነት አለባት።
እስልምና ከ1400 አመታት በፊት መልዕክቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለሴቶች የተረጋገጡትን የዜጎች ፣ የማህበራዊ እና የግል መብቶቻቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዚህ ዘመን ለሴቶች መብት ጥብቅና ከመቆማቸው በፊት እስልምና ለሴቶች ዋስትና ሰጥቷል።
እስልምና ያረጋገጣቸው የሴቶች የሲቪል እና ማህበራዊ መብቶች
ከ1400 ዓመታት በፊት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከመቋቋማቸው ከረጅም ጊዜ በፊት እስልምና ለሴቶች የሚከተሉትን የሲቪል እና ማህበራዊ መብቶች አረጋግጧል፡-
- የመማር እና የማስተማር መብት፡ እስልምና እውቀት መፈለግን በወንዶችም በሴቶችም ላይ ግዴታ አድርጓል።
- የመስራት መብት፡ ምንም እንኳ ወጪን መሸፈን የወንድ ኃላፊነት ቢሆንም ሴት ልጅ መስራት ከፈለገች በእስልምና ደንቦችና ህግጋት መሰረት መስራት ትችላለች።
- የንብረት ባለቤት የመሆን መብት፡ ሴቶች ስራ በመስራት ወይም ውርስ በማግኘት የንብረት ባለቤት የመሆን ሙሉ መብት አላቸው። ንብረቷን እንደፈለገች የማድረግ ሙሉ ነፃነትም አላት። በገንዘቧ ላይ አንድም ተቆጣጣሪ የለባትም፤ አባቷ ፣ ባሏ ወይም ሌላ ሰው ቢሆንም እንኳ።
- የሴቶች የውርስ መብት በእስልምና፡ ቁርአን ፣ ሱና እና የፊቅህ ሊቃውንት ሴቶች በፍትሃዊነት የውርስ ድርሻ እንዲያገኙ በግልጽ ደንግገዋል።
የሴት ልጅ የግል እና የትዳር መብቶች
እስልምና ለሴቶች በትዳር እና በግል ህይወታቸው ሰፊ መብቶችን ሰጥቷል፡-
- መልካም ባልን የመምረጥ፣ የመቀበል ወይም ያለመቀበል ሙሉ መብት።
- ጥሎሽ (መህር) የማግኘት መብት (ይህ የራሷ የግል ንብረት ነው)።
- የእሷ እና የልጆቿ ወጪ (ነፈቃ) በባሏ የመሸፈን መብት።
- በባሏ በመልካም ቃል እና ተግባር፣ የተከበረ ህይወት የመኖር መብት።
- ባል ከአንድ በላይ ሚስት ካለው፣ እኩል አያያዝ የማግኘት መብት።
- ከባሏ ውጭ በራሷ ንግድ ዋስትና የመሆን የኢኮኖሚ ነጻነት መብት።
- መለያየት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ፍች (ኹልዕ) የመጠየቅ እና የማግኘት መብት።
- ከፍች በኋላ (እንደገና ካላገባች) ልጆቿን የማሳደግ (ሞግዚት የመሆን) መብት።
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ሴቶች በእስልምና ውስጥ ያላቸውን መብት የሚያንፀባርቁ ምሳሌዎች ናቸው። ከዚህ ባሻገር እስልምና ለሴቶች ያጎናፀፋቸው መብቶች በጣም በርካታ ናቸው።
ማጠቃለያ
የሴት ልጅ መብት በእስልምና በዘመናዊ ድርጅቶች የተሰጠ ሳይሆን ከ1400 ዓመታት በፊት በመለኮታዊ ራዕይ የተረጋገጠ ክብር ነው። እስልምና ሴቶችን ከጃሂልያ ውርደት አውጥቶ በሃይማኖት ፣ በኢኮኖሚ (ውርስ ፣ ንብረት) እና በትዳር (ባልን መምረጥ ፣ ፍች) ሙሉ መብትና ነጻነት አጎናጽፏቸዋል። ይህ የኢስላም ፍትሃዊ ስርዓት ለሴቶች የሰጠውን ደረጃ ያሳያል።
እርስዎስ እስልምና ለሴቶች በሰጠው መብት ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት? ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ ያጋሩን።




Share