የሙስሊም ሴት ንፅህና ፡ የተሟላ መመሪያ

Author picture
የሙስሊም ሴት ንፅህና ማወቅ ይፈልጋሉ? ይህ ጽሑፍ ስለ የወር አበባ፣ ጀናባ፣ ኒፋስ እና ኢስቲሃዷ ህግጋት (አህካም) በዝርዝር ያብራራል። ዒባዳዎን በትክክል ለመፈፀም ያንብቡ።
የሙስሊም ሴት ንፅህና ፡ የተሟላ መመሪያ

መግቢያ

በእስልምና ንፅህና የእምነት ግማሽ ነው። በተለይ ለሙስሊም እህቶች ፣ የሙስሊም ሴት ንፅህና ህግጋትን ማወቅ የእለት ተእለት አምልኳቸውን (ዒባዳ) በትክክል ለመፈፀም ወሳኝ ነው። ብዙ ሴቶች የወር አበባ (ሀይድ) ፣ ኢስቲሃዷ (የበሽታ ደም) ፣ የወሊድ ደም (ኒፋስ) እና ከግብረስጋ ግንኙነት (ጀናባ) በኋላ ስላሉ ህግጋት ግልጽ መረጃ ይፈልጋሉ።

ይህ ጽሑፍ እነዚህን አንገብጋቢ የፊቅህ ጉዳዮች በቀላል እና ግልጽ በሆነ አማርኛ ይዳስሳል። ከንፅህና በኋላ በትክክል ገላን እንዴት መታጠብ እንዳለብን ፣ በነዚህ ወቅቶች የተከለከሉ ነገሮች ምን እንደሆኑ እና ንፁህ መሆናችንን በምን እናውቃለን? ለሚሉ ጥያቄዎች በሸሪዓ መሠረት መልስ ያገኛሉ።

ለሙስሊም ሴት የንፅህና ህግጋትን የማወቅ አስፈላጊነት

አንዲት ሙስሊም ሴት አስፈላጊ የሆኑ የንፅህና ህግጋት እንድትማር ሸሪአ ያስገድዳታል። በተለይም ከዕለት ተዕለት አምልኮዋ (እንደ ሶላት እና ፆም) ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸውን የወር አበባ (ሀይድ) ፣ ኢስቲሃዷ እና የወሊድ ደም (ኒፋስ) ያሉ ጉዳዮችን ማወቅ የሁሏም ሙስሊም ሴት ግዴታ ነው።

አንዲት ሙስሊም ሴት ማወቅ እና መስራት ካለባት ነገሮች መካከል

  1. ከግብረስጋግኑኝነት በኋላ ገላዋን መታጠብ
  2. የወር አበባዋ እንዳበቃ ገላዋን መታጠብ
  3. ከወሊድ ደም በኋላ ገላዋን መታጠብ

ገላን መታጠብ (ጉስል) ግዴታ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች

አንዲት ሙስሊም ሴት ማወቅ እና መስራት ካለባት ቁልፍ የንፅህና ተግባራት መካከል ከሚከተሉት ሁኔታዎች በኋላ ሙሉ ገላዋን መታጠብ (ጉስል) ይገኝበታል።

ከግብረስጋ ግንኙነት (ጀናባ) በኋላ መታጠብ

በቋንቋ ደረጃ ጀናባ ማለት የራቀ ማለት ሲሆን በሸሪአ ጁኑብ ማለት ደግሞ የግብረስጋግኑኝነት ወይም ነባዘርን ማፍሰስ ነው። ይህ የንፅህና መጓደል ጁኑብ ተብሎ ይጠራል። ምክኒያቱም ከንፅህና ጉድለት እስኪጠራ ድረስ ወደ ሶላት መስገጃ ቦታ መቅረብ የተከለከለ ነውና። ከግብረስጋግኑኝነት በኋላ ገላን መታጠብ ግዴታ ነው።

ኃያሉ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ማኢዳ፡ 6)

“ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክኒያት ‹‹ጀናባ›› ብትሆኑ ታጠቡ።”

የወር አበባ ካበቃ በኋላ መታጠብ

አንዲት ሙስሊም ሴት የወር አበባዋ ባቆመ ጊዜ ሶላት እና ሌሎች ዒባዳዎችን ለመጀመር ገላዋን መታጠብ አለባት።

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ፡ 222)

“ስለ ወር አበባ ይጠይቁሃል። እሱ አፀያፊ ነው። ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው። ንፁህ እስከሚሆኑም ድረስ አትቅረቧቸው። ንፁህ በሆኑ ጊዜ አሏህ ካዘዛችሁ ቦታ ተገናኟቸው። አሏህ ከሃጢያት ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው።”

በዚህ አንቀጽ ላይ “ንፁህ በሆኑ ጊዜ” (ፈኢዛ ተጦሃርነ) የሚለው የአላህ ንግግር የገላ ትጥበትነን የሚያመለክት መሆኑን ዑለማዎች ያስረዳሉ።

ከወሊድ ደም (ኒፋስ) በኋላ መታጠብ

አንዲት ሴት የወሊድ ደም (ኒፋስ) ማየቷ እንዳበቃ ገላዋን መታጠብ እንዳለባት የኢስላም ሊቃውንት (ዑለሞች) በማያሻማ መልኩ ተስማምተዋል።

የወር አበባ (ሀይድ) እና ኢስቲሃዷ ልዩነት

  • የወር አበባ (ሀይድ)፡ አንዲት ሴት ልጅ ባልፀነሰች ጊዜ ወይም ሳትታመም በተፈጥሮ ከማህፀኗ የሚፈስ ደም ነው።
  • ኢስቲሃዷ ደግሞ በህመም ወይም በሌላ ምክኒያት ከተለመደው ጊዜ ውጭ ከሴት ልጅ ማህፀን የሚፈስ ደም ነው።

ይህ ደም እንደ ወር አበባ አይቆጠርም፤ ሶላት እና ፆምንም አይከለክልም (ነገር ግን ለእያንዳንዱ ሶላት ውዱእ ማድረግ ያስፈልጋል።

የወር አበባ የቆይታ ጊዜ ከሴት ወደ ሴት ይለያያል። አብዛኛዎቹ ሊቃውንት እንደሚሉት ከፍተኛው የቆይታ ጊዜ 15 ቀን ነው። ከዚያ ከበለጠ እንደ ኢስቲሃዷ (የበሽታ ደም) ይቆጠራል። በአብዛኛው የሴቶች የወር አበባ ቆይታ ከስድስት እስከ ሰባት ቀን ነው።

የወሊድ ደም (ኒፋስ) ምንነት እና የቆይታ ጊዜ

ኒፋስ ማለት በወሊድ ጊዜ ወይም ከወሊድ በፊት እንደ ምልክት (ከሁለት ወይም ከሶስት ቀን በፊት) የሚፈስ ደም ነው። ይህ ደም ማህፀኗን ላላ እና ዘና የሚያደርግ ደም ነው። ከወሊድ በኋላ እስከ አርባ ቀን ድረስ ሊቀጥል ይችላል።

  • ከፍተኛው የቆይታ ጊዜ፡ 40 ቀናት
  • ዝቅተኛው የቆይታ ጊዜ፡ ገደብ የለውም። (ከ40 ቀን በፊት ደሙ ካቆመ፣ ሴቷ ታጥባ ዒባዳዋን ትጀምራለች)።

በወር አበባ እና በወሊድ ደም ወቅት የተከለከሉ (ሀራም) ተግባራት

አንዲት ሴት በወር አበባ (ሀይድ) ወይም በወሊድ ደም (ኒፋስ) ላይ እስካለች ድረስ የሚከተሉትን ተግባራት ከመፈጸም ተከልክላለች፡-

  • የግብረስጋ ግንኙነት ክልከላ

ባል ከሚስቱ ጋር በወር አበባ ጊዜዋ ግብረስጋ ግኑኝነት ከመፈፀም ተከልክሏል።

አሏህ እንዲህ አለ፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ 222)

“ስለ ወር አበባ ይጠይቁሃል። እሱ አፀያፊ ነው። ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው። ንፁህ እስከሚሆኑ ድረስ አትቅረቧቸው። ንፁህ በሆኑ ጊዜ አሏህ ካዘዛችሁ ቦታ ተገናኟቸው። አሏህ (ከሃጢያት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው።”

በዑለሞች ስምምነትም በወሊድ ደም ወቅትም ክልክል ነው።

  • የፍች ክልከላ (ጦላቅ)

ባል ሚስቱን በወር አበባ ወይም በወሊድ ደም ላይ እያለች መፍታት አይፈቀድለትም። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ጦላቅ፡ 1)

“ነብዩ ሆይ! ሴቶችን መፍታት ባሰባችሁ ጊዜ፤ በኢዳቸው (የወር አባባ በመጠበቂያ ጊዜያቸው) ፍቷቸው።”

ይህ የወር አበባ መጠበቂያ ጊዜያቸው ወይም (ኢዳቸው) የሚለው የአሏህ ንግግር ትርጉም የወር አበባ ላይ ፣ ወሊድ ላይ ወይም በንፅህና ጊዜያቸው ግብረስጋ ግኑኝነት አድርገው እያለ እርግዝናቸው ባለየበት ሁኔታ እንዳይፈቷቸው ነው።

  • የሶላት እና የፆም ክልከላ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ቡኻሪ 1951)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “አንዲት ሴት በወር አበባ ጊዜ የማትሰግድ እና የማትፆም መሆኗ እውነት አይደለምን? ያ የእምነቷ እጥረት ነው።”

ያመለጣትን ፆም ቀዷ ታወጣለች፣ ሶላትን ግን ቀዷ ማውጣት አይጠበቅባትም።

  • በካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ የማድረግ ክልከላ

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

ቡኻሪ 305 ፣ ሙስሊም 1211

‹‹ይህ አሏህ በአደም ሴት ልጆች ላይ ሁሉ የደነገገው ነው። ንፁህ እስክትሆኝ ድረስ በካዕባ ዙሪያ ካለመዞር በቀር ሐጃጆች የሚያደርጉትን አድርጊ አሉ።››

  • ቁርአንን የመንካት ክልከላ

ይህ ክልከላ አሏህ በቅዱስ ቃሉ እንዳለው ነው፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ዋቂአ፡ 79)

“ሙጦሃሩን (የተጥራሩ) እንጅ ማንም አይነካውም።”

ማሳሰቢያ፡ ጁኑብ የሆነ ሰው እስኪታጠብ ድረስ አያነብም። የወር አበባ ላይ ወይም የወሊድ ደም ላይ የሆነች ሴት አንድን የቁርአን አንቀፅ መከለስ ብትፈልግ ወይም ሌሎችን የምታስተምር ብትሆን እና መሰል ነገሮችን የምታደርግ ከሆነ ልክ እንደ እጅ ጓንት መሰል ግርዶሽ ወይም መከለያ ነገር በመጠቀም ቁርአንን መንካት ለእሷ የተፈቀደ ነው።

  • መስጅድ ውስጥ የመቆየት ቅድስና

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(አቡዳውድ 232)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በንግግራቸው፡ “መስጅድ በወር አበባ ላይ ለሆነች ሴት እና ጁኑብ ለሆነ ሰው የተፈቀደ እንዲሆን አላደርግም” ብለዋል።

ነገር ግን አስፈላጊ ሲሆን ለማለፍ (ለመግባትና ለመውጣት) ይፈቀዳል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ሙስሊም 298)

አኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ትላለች፡ ‹‹የወር አበባ ላይ ነኝ አልኳቸው። እሳቸውም፡ ‹‹የወር አበባሽ በአንች እጅ አይደለም አሉኝ።››

የወር አበባ አንድምታ

የወር አበባ መጀመር በሸሪዓ ውስጥ ሁለት ዋነኛ አንድምታዎች አሉት፡-

  • የጉርምስና ምልክት (አቅመ ሄዋን)፡ ለሴት ልጅ የጉርምስና መድረሷ አስተማማኝ ምልክት ሲሆን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሸሪዓ ግዴታዎች (ሶላት ፣ ፆም ወዘተ) ይጀምሩባታል።
  • የኢዳ መነሻ፡ የተፈታች ሴት የመጠበቂያ ጊዜዋ (ኢዳ) የሚቆጠረው በወር አበባ ኡደት ነው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ፡ 228)

“የተፈቱ ሴቶች በነፍሶቻቸው (ከማግባት) ሶስት የወር አበባን ኡደትን ይጠብቁ።”

ሴቶች ከወር አበባ የነፁ መሆኑን የሚያመላክቱ ነገሮች

አንዲት ሴት ከወር አበባ የነጻች መሆኗን በሁለት ምልክቶች ታረጋግጣለች፡-

ነጭ ፈሳሽ (አል-ቀሷቱል በይዷእ)፡ በወር አበባ መጨረሻ ላይ ከማህፀን የሚወጣ ንፁህ ነጭ ክር መሰል ፈሳሽ የንፅህና ምልክት ነው።

የደም ፍሰቱ ማቆም እና መድረቅ፡ ይህ ምልክት የሚታወቀው አንዲት ሴት ወደ ብልቷ ቁራጭ ጨርቅ ወይም ጥጥ ባስገባች ጊዜ ጨርቁ ንፁህ ሆኖ (በደም ፣ በቡናማ ወይም ቢጫ ቀለም ሳይቀባ) ሲወጣ ነው።

የትጥበት ስርዓት እና ግዴታዎች

ጉስል (የገላ ትጥበት) ትክክለኛ እንዲሆን ሁለት መሰረታዊ ግዴታዎች አሉት፡-

ኒያ ማድረግ (ማሰብ)፡ ንፅህናን ለማግኘት (ለምሳሌ ከጀናባ ወይም ከሀይድ) በማሰብ መታጠብ።

መላ አካልን በውሃ ማዳረስ፡ ፀጉርን እና ሁሉንም የሰውነት ክፍሎች በውሃ በደምብ ማዳረስ።

ሴቶች ከወር አበባ እና ከጁኑብ በኋላ የሚታጠቡበት መንገድ

ትክክለኛውና የተሟላው (ሱናን የጠበቀው) የትጥበት ስልት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳስተማሩት ነው፡፡ አኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው አስማ (ረ.ዐ) ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ከወር አበባ በኋላ ስለመታጠብ ስትጠይቃቸው እንዲህ አሉ፡-

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ቡኻሪ 314 ፣ ሙስሊም 332)

‹‹ውሃ ይዛ እራሷ ላይ በማፍሰስ እና የፀጉሯ ስር ድረስ እስኪደርስ በማሸት እራሷን በደንብ ታንፃ። ከዚያም ሰውነቷ ላይ ውሃ ታፍስ። ከዚያም ደረቅ ጨርቅ በመያዝ እራሷን ታንፃ አሉ። አስማ በእሱ እንዴት እራሴን ላንፃ? አለች። ሱብሃነሏህ! በእሱ እራስሽ አጥሪ አሏት። ወደ እኔ ጎተትኳትና ‹‹በደም የጎደፈውን ቦታ ፈግፍጊው›› አልኳት ትላለች አኢሻ(ረ.ዐ)››

ትጥበትን የሚያበላሹ ነገሮች

ውሃ ወደ የትኛውም የሰውነት ክፍል እንዳይዳረስ የሚያደርግ ማንኛውም ነገር ውዱእንም ሆነ ጉስልን ያበላሻል (ያልተሟላ ያደርገዋል)። ለምሳሌ፡ ሴቶች የሚጠቀሙት የጥፍር ቀለም (ውሃ የማያሳልፍ ከሆነ) ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ቁሳቁሶች ከመታጠባቸው በፊት መወገድ አለባቸው።

ቢጫማ እና ቡናማ ምልክት

ከወር አበባ በፊት እና በኋላ ከሴት ልጅ ብልት ቢጫማ ወይም ቡናማ ፈሳሽ ሊወጣ ይችላል። ከወር አበባ ጋር አብረው የሚታዩ ከሆነ የእሱ አንድ አካል ናቸው። ሴቷም ከሶላት እና ከሌሎች መቆጠብ ካለባት ነገር መቆጠብ አለባት።

እንደ ኡሙ አቲያ ሐዲስ ደግሞ ከወር አበባ ውጭ ከታዩ ምንም አይነት ተፅዕኖ አይኖረውም።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ቡኻሪ 325 ፣ አቡዳውድ 307)

‹‹ቢጫማ ወይም ቡናማ ምልክት እንደ አስፈላጊ ነገር (እንደ ወር አበባ) አንቆጥረውም ነበር።››

ማጠቃለያ

የሙስሊም ሴት ንፅህና በሸሪዓችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እና ከዒባዳችን ትክክለኛነት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ነው። የጀናባ ፣ የወር አበባ (ሀይድ) እና የኒፋስ ህግጋትን ጠንቅቆ ማወቅ እያንዳንዷ ሙስሊም አላህን የምትታዘዝበት እና አምልኮዋን በንቃትና በእውቀት ላይ ተመስርታ የምትፈጽምበት መሰረት ነው። ይህ እውቀት ግዴታዋን በትክክል እንድትወጣ እና ጥርጣሬዎችን እንድታስወግድ ይረዳታል።

እርስዎስ እነዚህን የንፅህና ህግጋት በሚመለከት ግር የሚልዎት ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉበት ነጥብ አለ? ጥያቄዎን በአስተያየት መስጫው ላይ ያጋሩን።

0%
4
Question report close icon

Report a question

You cannot submit an empty report. Please add some details.
Question report loader icon
Created by Ahmed Yesuf

ሙስሊም ቤተሰብ

ጥያቄና መልስ፡ የሙስሊም ሴት ንፅህና

‹‹የሙስሊም ሴት ንፅህና›› የሚለው ትምህርት ፈተና 5 ጥያቄዎችን ይዟል። ፈተናውን ለማለፍ 4 ጥያቄዎችን በትክክል መመለስ አለባችሁ።

1 / 5

Bookmark question icon

1 ትክክለኛውን መልስ ወይም መልሶች ምረጥ፡ የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ላይ የሆኑ ሴቶች ቁርአንን መንካት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ከኋላው በኩል (ግርዶሽ በመጠቀም) መንካት ይችላሉ። ለምሳሌ፡-

2 / 5

Bookmark question icon

2 ይህ የአሏህ ንግግር ‹‹ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክኒያት ‹‹ጀናባ›› ብትሆኑ ታጠቡ።›› ይህ የምን ማስረጃ ነው?

3 / 5

Bookmark question icon

3 በገላ ትጥበት ሊሟሉ የሚገቡ ሁለት ነገሮች

4 / 5

Bookmark question icon

4 የወር አበባ እና የወሊድ ደም ላይ የሆኑ ሴቶች ከፀዱ በኋላ ሶላቶቻቸውን ያካክሳሉ

5 / 5

Bookmark question icon

5 ትክክለኛውን መልስ ምረጥ፡ የወር አበባ ላይ የሆነች ሴት በወር አበባዋ የቆይታ ጊዜ ውስጥ ማድረግ ካለባት ነገር ውስጥ አንዱ

የተሳታፊ መረጃ

Your score is

The average score is 30%

0%

ለሰጡን ሀሳብ አስተያየት እናመሰግናለን!

Related posts

ሴቶች እና እስልምና

ሴቶች እና እስልምና

በእስልምና ወንዶች እና ሴቶች የተለያየ ባህሪ ያላቸው ሲሆን እያንዳንዳቸውም የራሳቸው ሚና አላቸው። በእስልምና ሴቶችን ማክበር መልካም እና ምስጉን ባህሪ እንዲሁም ያልተበረዘ ተፈጥሮ ምልክት ነው።

Read More »

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share