ሸሪአ ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚቃኝ እና የሚገዛ እስላማዊ ህግ ነው። ሸሪአ የሚለው ቃል ሙሉ በሙሉ ከአሏህ የመጣ ማንኛውንም ነገር የሚገለልፅ ነው።
ህግ አውጭው አሏህ ነው። የሰው ልጅ የፈጠራቸውን ህጎች ለመግለፅ ሸሪአ የሚለውን ቃል መጠቀም ክልክል ነው።

ሸሪአ እምነትን እና ስራን አጣምሮ የያዘ ነው። አምልኮን ፣ የሰው ልጅ ባህሪ እና ምግባርን ፣ ማህበራዊ እሴት እና ደንብ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ፣ የቤተሰብ እና የወንጀል መቅጫ ህጎችን አቅፎ የያዘ ነው።
የሸሪአ ምንጮች
የሸሪአ ህግ ከአራት መሰራተዊ ምንጮች ይቀዳል። እነሱም ቅዱስ ቁርአን ፣ የነብዩ ሱና ፣ ኢጅማዕ እና ቂያስ ናቸው። ቀዳሚዎቹ የሸሪአ ምንጮች ቁርአን እና የነብዩ ሱና ናቸው።
ኢማሙ አሻጢቢ አል-ሙወፈቃት ውስጥ “ቁርአን የሸሪአው ሙሉ ክፍል ፣ የሃይማኖቱ አምድ ፣ የጥበብ ምንጭ ፣ የነብይነት ምልክት ፣ የልብን እና የአይን ብርሃን ነው። ወደ አሏህ የሚያደርስ መንገድ የለም በእሱ ቢሆን እንጅ።
ከእሱ የበለጠ መድህን የለም። እሱን የሚፃረር (የሚቃረን) ነገር መያዝ እና መከተል የለባችሁም። ይህ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ግልፅ እና የሚታወቅ በመሆኑ ማረጋገጡም መርመርም አያስፈልገውም።
የሸሪአን ሙሉ እውቀት የሚፈልግ እና አላማዎቹን ለመረዳት የሚሻ ሰው አማኞቹን ይጠይቅ ፣ ቅዱስ ቁርአን ቀንም ማታም ቋሚ ጓደኛው አድርጎ ይያዝ።” ሲል ጽፏል። (አል-ሙወፈቃት ጥ.3 ገጽ 247)
ሱና ወይም የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስራ ፣ ባህሪ እና ልምድ ሁለተኛው የሸሪአ ምንጭ ነው። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ሐሽር 59፡7)
መልእክተኛው የሰጣችሁን ያዙ፤ እሱ የከለከላችሁን ተው (ተከልከሉ)።
የነብዩ ሱና ቁርአንን ይገልፃል፤ ያብራራል። ጥቅሉን ይተነትናል። ይህን ግልፅ ለማድረግ ጥሩ ምሳሌ ሶላት ነው። ቁርአን ውስጥ አሏህ ሙእሚኖች በቀን አምስት ጊዜ እንዲሰግዱ ያዛል።

ነገርግን እንዴት መፈፀም እንደሚቻል አይገልፅም። የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ምሳሌ እና ገለፃ ሶላት እንዴት መስገድ እንዳለብን ያሳየናል።
ነገርግን ጉዳዩ በቁርአንም በነብዩ ሱና ውስጥ ያልተገለፀ ከሆነ የህግ አዋቂዎች ኢጅማ (የሙስሊም ሊቃውንቶች ስምምነት) ይመለከታሉ።
የሆነ ዘመን ላይ ሁሉም ኡለማዎች በጉዳዩ ከተስማሙበት ተቀባይነት ይኖረዋል።
እነዚህ ሶስት የሸሪአ ምንጮች በአንድ ጉዳይ ላይ የሚፈለገውን የህግ ማዕቀፍ ካላስገኙ ህግ አዋቂው በቂያስ ማለትም በንፅፅር በማሰብ ተቀባይነት ያለውን መርህ የህግ የበላይነት እንዲከበር ሊጠቀምበት ይችላል።
የሸሪአ ዋና አላማ በዚህ አለም ሆነ በመጭው አለም የሰው ልጆች ደህንነት ማረጋገጥ ነው። የሙስሊሙ ማህበረሰብ ፍላጎቶች አስቸኳይ ፍላጎቶች ፣ የተለመዱ ፍላጎቶች እና ማሟያ ፍላጎቶች በሚል ይከፈላሉ።
ከተዘረዘሩት ሁሉ የሚልቀው የመጀመሪያው አስቸኳ ፍላጎቶች ናቸው። ይህም አምስት የሸሪአ ግቦችን የያዘ ነው።
መታደግ እና መጠበቅ 1 ህይወት 2 አዕምሮ 3 እውነተኛ ሃይማኖት 4 ንብረትንና 5 የተለያዩ ዝርያዎችን ከጥፋት መታደግ እና መጠበቅ ናቸው።



Share