​እውነተኛ ሃይማኖት

Author picture
ክርስትና ከእየሱስ፤ ቡድሂዝም ከጉተማ ቡድሃ፤ ኮንፊሽያኒዝም ከኮንፊሽየስ እንዲሁም ማርክሲዝም ከካርል ማርክስ ስያሜያቸውን እንዳገኙ አይነት የእስልምና ሃይማኖት ስሙን ከግለሰብ ስም አልወሰደም።
​እውነተኛ ሃይማኖት

ኢስላም

ኢስላምን አስመልክቶ አንድ ሰው በቅድሚያ ሊያውቀውና በግልፅ ሊረዳው የሚገባው ነገር ኢስላም የሚለው ቃል ትርጉሙ ራሱ ምን ማለት እንደሆነ ነው።

ክርስትና ከእየሱስ፤ ቡድሂዝም ከጉተማ ቡድሃ፤ ኮንፊሽያኒዝም ከኮንፊሽየስ እንዲሁም ማርክሲዝም ከካርል ማርክስ ስያሜያቸውን እንዳገኙ አይነት የእስልምና ሃይማኖት ስሙን ከግለሰብ ስም አልወሰደም።

እንደ አይሁዳ ከይሁዳ ጐሳና እንደ ሕንዱይዝም ከህንዱ መጠሪያ ስሙን አላገኘም። ኢስላም የአሏህ ሃይማኖት ነው።

በመሆኑም መጠሪያ ስሙ የአሏህን ሃይማኖት ማእከላዊ መርህ ለአሏህ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መገዛትንና ማደርን የሚወክል መጠሪያ ስም ነው።

ኢስላም የሚለው የአረብኛ ቃል አምልኮት ለሚገባው ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ለአሏህ ራስን ማስገዛትና ለርሱ ፍቃድ ማደር ማለት ሲሆን ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው «ሙስሊም» ተብሎ ይጠራል።

በተጨማሪም ቃሉ ሙሉ በሙሉ ለአሏህ ፈቃድ የመገዛት ውጤት የሆነውን “ሠላምን” ያመለክታል። ስለዚህ ዐረቢያ ውስጥ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አማካኝነት የመጣ አዲስ ሀይማኖት ሳይሆን በመጨረሻ ቅርፁ ዳግም የተገለፀ እውነተኛ ሀይማኖት ነው።

ኢስላም ለመጀመሪያው ሰውና ለመጀመሪያው የአላህ ነቢይ ለአደም የተሰጠና ወደ መላው የሰው ልጅ ከአሏህ የተላኩ ነቢዮች ሁሉ የጋራ ሃይማኖት ነዉ።

የአሏህ ሃይማኖት የሆነው ኢስላም በዚህ እንዲሰየም የተወሰነው በኋለኞቹ የሰው ልጅ ትውልዶች አይደለም።

ስሙ የተመረጠው በራሱ በአሏህ ሲሆን ይህም ወደ ሰው ልጅ ባስተላለፈው የማጠቃለያ መልእክት (ወሕይ) ውስጥ በግልፅ ተጠቅሷል።

የመጨረሻው መለኮታዊ መፅሐፍ በሆነው ቁርአን ውስጥ አሏህ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ማኢዳ 5:3)

ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ ጸጋየንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ ለናንተም ኢስላምን ከሀይማኖት በኩል ወደድኩ።

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ዒምራን 3:65)

ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈፀጽሞ ከርሱ ተቀባይነት የለውም፤….

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ዒምራን 3:67)

ኢብራሂም ይሁዳዊም ክርስቲያንም አልነበረም ግን ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት የተዘነበለ ሙስሊም ነበር፤

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ቦታ ላይ አሏህ ለነብዩ ሙሳ ሕዝብም ሆነ ለዝርዮቻቸው የነርሱ ሃይማኖት ይሁዳዊነት ነው ሲል ወይም ለክርስቶስ ተከታዮች ሃይማኖታቸው ክርስትና ነው ሲል አናገኝም።

እውነቱን ለመነጋገር ሌላው ቀርቶ “ክራይስት” የሚለው ቃል “ክርስቶስ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ስም ሲሆን ትርጉሙ የተቀባው ማለት ነው።

ይህም ክርስቶስ “መሲሕ” ለሚለለው የዕብራይስጥ የማእረግ ስም ትርጉም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ የሚለው ስም “ኢሳው (Esau)” ለሚለው የኢብራይስጥ ስም ላቲናዊ ቅላፄ ነው።

ይሁን እንጅ ነገሩን ቀላል ለማድረግ ስል ነብዩ ኢሳ (ዐ.ሰ) እየሱስ ብየ መጥራቴን እቀጥላለሁ። ሃይማኖታቸውን በተመለከተ ግን መጠፈሪያው ነብዩ ተከታዮቻቸውን ይጠሩበት የነበረው ስም ነው።

ከሳቸው በፊት እንደነበሩት ነቢያት ሁሉ ሕዝቡ ፍላጐቱን ለአሏህ ፍላጐትና ለርሱ ፈቃድ እንዲያስገዛ ጥሪ አድርገዋል።

የሰው ልጅ ምናብ ከፈጠራቸው የሐሰት አማልክት እንዲርቅም አስጠንቅቀዋል።

በሐዲስ ኪዳን እንደተጠቀሰው ተከታዮቻቸው «ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድርም ትሁን» ብለው እንዲፀልዩ አስተምረዋል።

የኢስላም መልእክት

የራስን ፍላጐትና ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለአሏህ ማስገዛት የአምልኮትን ሥረ-መሠረት የሚወክል እንደመሆኑ መጠን የአሏህ መለኮታዊ ሃይማኖት የሆነው የኢስላም መሠረታዊ መልእክት አሏህን ብቻ ማምለክና ለማንኛውም ሰው ፣ ቦታ ወይም ከአሏህ በስተቀር ለማንኛውም ነገር ከሚደረግ አምልኮ ፈፅሞ መራቅ ነው።

የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ጌታ ከሆነው ከአሏህ በስተቀር ያለው ማንኛውም ነገር የአሏህ ፍጡር በመሆኑ የሰው ልጅ ከፍጡራን አምልኮ እንዲገታ ጥሪ በማድረግ የፍጡራን ፈጣሪን አምላክ ብቻ እንዲያመልክ መጋበዝ የኢስላም ተልእኮ ሥረ-መሠረት ነው ማለት ይቻላል።

አምልኮውና ጸሎቱ ተቀባይነት የሚያገኙት በርሱ ፈቃድ ብቻ እንደመሆኑ የሰው ልጅ አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው ለአንድ አሏህ ብቻ ነው።

ሰው ዛፍ ቢያመልክና ጸሎቱ ተሰሚነት ቢያገኝ ለጸሎቱ ምላሽ የሰጠው ዛፉ ሳይሆን የተለመነው ነገር እንዲፈጽም የፈቀደው አሏህ ነው።

አንድ ሰው ለዛፍ አምላኪወች እንዲህ ሆኖ አይታያቸውም ሊል ይችላል በተመሳሳይ መልኩ ለእየሱስ ለቡድሃ ወይም ለክሪሽና ወይም ለሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ ) ቢሆን የሚደረግ አምልኮና ጸሎት ምላሽ የሚሰጠው በነዚህ ሰወች ሳይሆን በአሏህ ነው።

እየሱስ ተከታዮቻቸው በሳቸው እንዲያመልኩ አላስተማሩም፤ ያስተማሩዋቸው አንድ አሏህን ብቻ እንዲገዙ ነው። ቁርአን ይህንኑ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ማኢዳህ 5:116)

አሏህም የመርየም ልጅ ኢሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ እኔንና እናቴን ከአሏህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብልሃልን በሚለው ጊዜ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገቢዬ ያልኾነ ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም።

ሲያመልኩ የነበረው የገዛ እራሳቸውን ሳይሆን አምልኮታቸውና ተገዥነታቸው ለአሏህ ብቻ ነበር። ይህ መሠረታዊ መርሕ ሱራ አል-ፋቲሀ 1:4 ውስጥ ተቀምጧል

አል-ቁርአን

ሱራ አል-ፋቲሀ 1:4

“አንተን ብቻ እንገዛለን፤ አንተንም ብቻ እርዳታ እንለምናለን።”

የመጨረሻው መለኮታዊ ራዕይ (ወሕይ) መጽሐፍ በሆነው ቁርአን ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ አሏህ እንዲህ ብሏል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ሙእሚን 40:60)

ጌታችሁም አለ: ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና፤

አሏህና የሱ ፍጥረታት ፍጹም የተለያዩ ሕላዌዎች ናቸው የሚለው የኢስላም መልእክት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው።

አሏህ ፍጡር ወይም የፍጥረቱ አካል አይደለም።የርሱ ፍጡርም እርሱ ወይም የሱ አካል አይደለም።

ይህ አባባል ግልጽ ሊመስለን ይችላል፤ ነገርግን የሰው ልጅ ፈጣሪውን ትቶ ፍጡርን የሚያመልከው በአብዘኛው ይህን ጽንስ ሀሳብ ካለመረዳት የተነሳ ነው።

አሏህ በሁሉም ቦታ ፍጥረት ውስጥ ሰርጿል ወይም መለኮታዊ ሕልውናው በአንዳንድ የፍጥረት ገጽታዎች ውስጥ ይገኛል የሚለው እምነት ነው።

በዚህ አይነቱ አምልኮ አማካኝነት ፍጡሩን የማምለክና በፍጡር አማካኝነት የመጣው የእኢስላም መልእክት አንድ አሏህን ብቻ ማምለክና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፍጡርን ማምለክ ማስወገድ ነው። አሏህ ቁርአን ውስጥ ይህንን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ አል ነሕል 16:36)

በሁሉም ሕዝቦች ዉስጥ አሏህን ተገዙ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልእክተኛን በእርግጥ ልከናል፤

በጣዖት የሚያመልከው ሰው በሰው እጅ ተጠርቦ ለተሠራ ጣዖት ለምን እንደሚሰግድ ሲጠየቅ ከቦታ ቦታ የማይለያይ ተመሳሳይ ምላሹ በተጨባጭ የምናመልከው ጥርቡን የድንጋይ ወይም የእንጨት ምስል ሳይሆን በርሱ ውስጥ የሰረፀውን አሏህን ነው የሚል ነው።

ጥርቡ ድንጋይ ወይም እንጨት ጣዖት አሏህ ለሚለው ጽንስ ሀሳብ የትኩረታችን ማሳረፊያ ነጥብ እንጂ አሏህ ራሱ አይደለም ይላሉ።

አሏህ በፍጡራን ውስጥ በሆነ መንገድ ሰርጿል የሚለውን ፅንስ ሐሳብ የተቀበለ ሰው ይህን የአምልኮተ ጣዖት ክርክር ለመቀበል ይገደዳል።

የኢስላም መሠረታዊ መልእክትና አንድምታዎቹን የሚረዳ ሰው ግን የፈለገውን ያህል ምክኒያታዊ መስሎ ቢቀርብ በጣዖታዊነት ፈጽሞ አይረታም።

በሁሉም ዘመናት ራሳቸውን የመለኮታዊነት ባህሪያት በራሳቸው ያላበሱ ወገኖች አሏህ በሰብአዊ ፍጡር ሰርጿል በሚል የተሳሳተ እምነት ላይ ነው አባባላቸውን የሚገነቡት።

በተሳሳተ እምነታቸው መሠረት አሏህ በሁላችነም ውስጥ የሰረፀ ቢሆንም ቅሉ ከተቀሩት ሰዎች ይበልጥ እነርሱ ውስጥ የሰረጸ አድርገው ይናገራሉ።

ስለሆነም ፍላጐታችነን ለርሱ ማስገዛት በአካል ወይም አምላክ ከመሆናቸው አንፃር ወይም አምላክ በነርሱ ስብእና ውስጥ የታመቀ ከመሆኑ አኳያ እነርሱኑ ማምለክ እንዳለብን ይለፍፋሉ።

በተመሳሳይ መልኩ እነዚያ የሰወችን አምላክነት ከሰዎቹ ሞት ቡሃላ የተቀበሉ ወገኖችም አምላክ በሰው ውስጥ ሰርጿል የሚለውን የተሳሳተ እምነት በሚቀበሉ ሰወች ዘንድ የሞቀ አቀባበል አግኝተዋል።

የኢስላምን መሠረታዊ መልእክትና አንድምታዎቹን የተገነዘበ ሰው ግን በማንኛውም ሁኔታ ሰብአዊ ፍጡርን ማምለክ በጭራሽ አይቀበልም።

የአሏህ ሃይማኖት በመሠረቱ ለፈጣሪ አምልኮ የሚደረግ ግልጽ ጥሪና የፍጡራንን አምልኮ በማንኛውም መልኩ ውድቅ ማድረግ ነው።

ይህም የኢስላም መፈክር የሆነው “ከአሏህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም” የሚለው ነው።

ይህን መናገር አንድን ሰው በቀጥታ ወደ ኢስላም ጐራ ሲያመጣ፤ በፍጹምነት በዚህ አምኖ ከልቡ መቀበል ጀነት የመግባት ዋስትናን ያስገኝለታል።

መፈክሩ አሏህን አንድ ብቸኛ አምላክ አድርጐ ለርሱ ብቻ በመገዛትን ፣ ለሕግጋቱ መታዘዝን ፣ ጣዖታዊነትንና ጣዖታዊያንን ማስተባበልን ያካትታል።

የውሸተኛ ሃይማኖት መልእክት

በአለም ላይ ብዙ የእምነት ቡድኖች ፣ ሃይማኖቶች ፣ ፍልስፍናዎችና ንቅናቄዎች ይገኛሉ። ሁሉም ትክክለኛው መንገድ የኔ ነው ወይም ወደ አሏህ የሚወስድ ብቸኛው መንገድ የኔ ነው ብለው ይናገራሉ።

እናም አንድ ሰው የትኛው ትክክለኛ እንደሆነ ወይም ሁሉም ትክክለኞች እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ እንዴት ይቻላል?

መልሱን ማግኘት የሚቻልበት ዘዴ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ መንገድ ጥሪ የሚያደርጉበትን ማእከላዊ የአምልኮት ዒላማ ለይቶ በማውጣት ነው።

ሐሰተኛ ሀይማኖቶች ሁሉ አሏህን አስመልክቶ አንድ የጋራ ግንዛቤ አላቸው። ሰዎች ሁሉ አማልክት ናቸው፤ ወይም የተለያዩ ሰዎች አሏህ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ተፈጥሮ አሏህ ነው ብለው ይላሉ።

ከዚህም በመነሳት የሐሰተኛ ሃይማኖት መሠረታዊ መልእክት አሏህ በራሱ ፉጡራን ተመስሎ ሊመለክ ይችላል የሚል ነው።

ሐሰተኛ ሃይማኖት ፍጥረትን ወይም አንድን የፍጥረት ገጽታ አምላክ ነው ብሎ በመሰየም የሰው ልጅ ፍጥረትን እንዲያመልክ ጥሪ ያደርጋል።

ለምሳሌ ያህል ነብዩ ኢሳ ወይም እየሱስ (ዐ.ሰ) ተከታዮቻቸው አሏህን እንዲያመልኩ የጋበዙ ሲሆን የእየሱስ (ዐ.ሰ) ተከታዮችነን ባዮች ግን ኢየሱስ ራሳቸው አሏህ ናቸው በማለት ሕዝቡ ኢየሱስን እንዲያመልክ ይሰብካሉ።

ቡድሃ አያሌ ሰብአዊ ይዘት ያላቸው መርሆወችን ወደ ሕንድ ያስገባ የተሐድሶ አራማጅ ነበር። አምላክ ነኝ አላለም ወይም የአምልኮታቸው ዒላማ የመሆን ሐሳብ ለተከታዮቹ አላቀረበም ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ከሕንድ ውጭ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ቡድሂስቶች ቡድሀን አምላክ አድርገው በመያዝ በነሱ ግምት በርሱ አምሳል በተቀረጹ ምስሎች ላይ ተደፍተው ይሰግዳሉ።

አምልኮው ዒላማ ያደረገውን ነገር ለይቶ ማውጣት የሚለውን መርሕ በመጠቀም ፣ ሐሰተኛ ሃይማኖት በጣም ግልጽና የሥረ-መሠረቱ ሰው ሰራሽ ተፈጥሮም ገሃድ ይሆናል። አሏህ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ብሏል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ ዩሱፍ 12:40)

ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ አምላክ ብላችሁ የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዙም፤ አሏህ በርሷ ምንም ማስረጃ አላወረደም፤ ፍርዱ የአሏህ እንጂ የሌላ አይደለም፤ እርሱን እንጂ ሌላን እንዳትገዙ አዟል፤ ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኛወቹ ሰዎች አያውቁም።

ሁሉም ሃይማኖቶች መልካም ነገሮችን ያስተምራሉና አንዱን ብንከተል ምን ያመጣል የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል።

መልሱ ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ሁሉ የፍጡር አምልኮ የሆነውን ከሁሉም እጅግ ከባዱን ጥፋት ነው የሚያስተምሩት የሚል ይሆናል።

የፍጡር አምልኮ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መሰረታዊ ዓላማ የሚፃረር በመሆኑ በሰው ልጅ ሊፈጸም የሚችል እጅግ የከፋና ከሁሉም በላይ ከባዱ ሀጡያት ነው።

ቁርአን ውስጥ በግልጽ እንደተጠቀሰው ሁሉም የሰው ልጅ የተፈጠረው አሏህን ብቻ ለመገዛት ነው።

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ዛሪያት 51:56)

ጅንንም ሰውንም አልፈጠርኳቸውም፤እኔን ሊገዙኝ ቢሆን እንጅ።

ስለ ሆነም የጣዖታዊነት ሥረ-መሰረት በሆነው ሽርክ ላይ ሆኖ የሞተ ሰው በወዲያኛው ሕይወት ዕድሉን ዘግቷል። አሏህ የመጨረሻ በሆነው ወሕዩ ቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ማኢዳህ 4:48)

{48} አሏህ በርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፤ ከዚህ ውጭ ላለው ለሚሻ ሰው ይምራል።

የሐሰተኛ ሐይማኖት ውጤቶች እጅግ አደገኛ ከሆኑ ዘንዳ ፣ እውነተኛው የአሏህ ሃይማኖት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊረዱትና ሊጨብጡት የሚቻል ሁለንተናዊ የሆነ ሃይማኖት ነው።

አማኙ ጀነት እንዲገባ እንደ ጥምቀት እና አዳኝ ነው ብሎ በሰው ማመን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሊኖሩ አይችሉም። ራስን ለአሏህ ፈቃድ ማስገዛት በሚለው የኢስላም ማእከላዊ መርህ እና ትርጔሜ ላይ ነው።

የኢስላም ሁለንተናዊነት መሠረት ያረፈው የሰው ልጅ አሏህ አንድና ከፍጡራኑ ፈጽፅሞ የተለየ መሆኑን ለመገንዘብ በቅቶ ራሱን ለአሏህ ፍቃድ ባስገዛ ጊዜ በአካልና በመንፈስ ሙስሊም ሆኖ ለጀነት ብቁ ይሆናል።

በዚህ መሠረትም በማንኛውም ጊዜ በጣም ሩቅ በሆነ የአለም ክፍል የሚኖር ማንኛውም ሰው የፍጡር አምልኮን ውድቅ አድርጐ ወደ አንድ አሏህ በመመለስ ብቻ የአሏህ ሃይማኖት የሆነው የኢስላም ተከታይ ሙስሊም መሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ አሏህን አውቆ መቀበልና ራስን ለርሱ ፈቃድ ማስገዛት፤ ጥሩውን ከመጥፎው ለይቶ መምረጥን የሚጠይቅና እንዲህ ዓይነቱ ምርጫም ሃላፊነትን እና ተጠያቂነትን የሚያመለክት ሞሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

የሰው ልጅ በምርጫው ውጤት ተጠያቂ ነው። ስለዚህ በጐ ሥራ በመሥራት እና ክፍውን ማስወገድ ያስፈልጋል።

የመጨረሻው ከፍተኛ በጐ ተግባር ደግሞ አሏህን ብቻ መገዛት ሲሆን የመጨረሻው ከባድ እና ክፉ ሥራ ደግሞ ፍጡራንን ከአሏህ ጋር በማጋራት ወይም በአሏህ ፈንታ ሌላን ማምለክ ነው።

ይህ እውነታ በመጨረሻው መለኮታዊ መልእክት “ወሕይ” ውስጥ እንደሚከተለው ተገልጿል፦

አል-ቁርአን

[ሱራ አል-በቀራ 2:62]

በእርግጥ! እነዚያ ያመኑ እና እነዚያ ይሁዳዊያኖችም ፣ ክርስቲያኖችም ፣ ሳቢያኖችም ከነርሱ መካከል በአሏህ እና በመጨረሻው ቀን ያመኑ መልካም ሥራም የሰሩ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳ አላቸው፤ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም ፣ እነርሱም አያዝኑም።

አል-ቁርአን

(ሱራ አል-ማኢዳ 5:66)

{66} እነሱም ተውራትንና ኢንጂልን፥ ከጌታቸው ወደነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባወቁና ባረጋገጡ ኖሮ ከበላያቸው እና ከእግሮቻቸው ስር በተመገቡ ነበር። ከነሱ መካከል ትክክለኛና ሚዛናዊዎች አሉ። ነገር ግን አብዛሃኛዎቹ ቅጥ ያለፈ ሃጢያትን ይሰራሉ።

አሏህን ማወቅ

ሰዎች አሏህን ለመገዛት ሃላፊነት ይሰማቸው ዘንድ ሁሉም አሏህን የማወቅ ብቃት ሊኖረው ይገባል። የሰው ልጆች በሙሉ አሏህን የማወቅ ተፈጥሯዊ ግንዛቤ እውስጣቸው የተተከለ መሆኑንና አብረውት የተፈጠሩ መሠረታዊ ባህሪያቸው መሆኑን የመጨረሻው መለካታዊ መልእክት (ወሕይ) ያስተምራል።

ሱራ አል-አዕራፍ አንቀጽ 172-173 ውስጥ አሏህ አደም ወይም አዳም ሲፈጥር የአዳም ዝርዮች ወደ ቁሳዊው አለም ከመምጣታቸው በፊት ወደ መኖር እንዲመጡ አድርጐ «ጌታችሁ አይደለሁምን? በነፍሶቻቸው ላይ ባስመሰከራቸው ጊዜ ፣ ጌታችን ነህ፥መሰከርን አሉ፤» በማለት ቃልኪዳናቸውን የወሰደ መሆኑን ገልጿል።

ከዚያም በመላው የሰው ልጅ እሱ ፈጣሪያቸውና ሊገዙት የሚገባ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ለምን እንዳደረገ አሏህ አብራርቷል።

እንዲህ በማለት:- «በትንሳኤ ቀን ከዚህ ኪዳን ዘንጊዎች ነበርን እንዳትሉ፥» ይህም አንተ አሏህ አምላካችን ስለመሆንህ ምንም ሐሳብ አልነበረንም ፣ አንተን ብቻ መገዛት እንደነበረብን ማንም አልነገረንም እንዳይሉ ነው ማለት ነው።

አሏህ ማብራሪያውን በመቀጠል እንዲህ ይላል:- «ጣዖታትን ያጋሩት ከኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን ብቻ ናቸው፤ እኛም ከነሱ በሗላ የኾን ዘሮች ነበርን ፤ አጥፊዎቹ በሠሩት ታጠፋናለህን እንዳትሉ አስመሰከርናችሁ።»

ስለዚህ እያንዳንዱን ሕፃን በአሏህ የማመን ተፈጥሮና ራእሱን ብቻ የማምለክ ዝንባሌ አብሮት ይወለዳል።

ይህ ተፈጥሮ በአረብኛ «ፊጥራህ» ተብሎ ይጠራል። ሕፃኑ ለብቻው ቢተው ኖሮ በራሱ መንገድ አሏህን ይገዛ ነበር።

ዳሩ ግን ሕፃናት ሁሉ በሚታዩም ሆነ በማይታዩ ነገሮች በአካባቢያቸው ተጽእኖ ሥር ይወድቃሉ። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) «አሏህ ባሮቼን የፈጠርኳቸው በትክክለኛው ሃይማኖት ላይ ነው፤ ነገር ግን ሰይጣኖች ያጠሟቸዋል ብሏል ማለታቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እያንዳንዱ ሕፃን “በፊጥራህ” ሁኔታ ላይ ሆኖ ይወለዳል፤ ይሁዳዊ ፣ ክርስቲያን ወይም ዞራስተሪያን (እሳት አምላኪ) የሚያደርጉት ወላጆቹ ናቸው፤…..ብለዋል።»
(ቡኻሪና ሙስሊም)

ሕፃኑ ልክ አሏህ በተፈጥሮ ውስጥ ባኖራቸው ፊዚካል ሕግጋት ተገዥ እንደሆነ ሁሉ ነፍሱም አሏህ ጌታዋና ፈጣሪዋ ለመሆኑ እውነታ በተፈጥሮዋ ተገዥ ትሆናለች።

ነገር ግን የሕፃኑ ወላጆች የራሳቸውን መንገድ እንዲከተል ለማድረግ የሚሞክሩ ሲሆን ሕፃኑ በመጀመሪያዎቹ የእድሜ ዘመኑ የወላጆቹን ፈቃድ ለመቋቋምም ሆነ ለመቃወም አቅም የለውም።

በዚህ ደረጃ ላይ ሕፃኑ የሚከተለው ሃይማኖት የወግ ልማዱና የአስተዳደግ አካባቢው አይነት ነው። አሏህም በዚህ ደረጃ ላይ ሕፃኑን በዚህ ሃይማኖት ምክኒያት ተጠያቂ አያደርገውም።

ከልደት እስከ ሞት ባለው የሕዝቦች ሕይወት ውስጥ አንድ እውነተኛ አምላክ አሏህ ብቻ መሆኑ ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ምልክቶችና ተአምራት በምድር ውስጥና በራሳቸው ነፍስ ውስጥም ይገለጹላቸዋል።

ሰዎች ከራሳቸው ጋር እውነተኛና ታማኞች ሆነው የሐሰት አማልክቶቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተው አሏህን ቢፈልጉ….መንገዱ ቀላል ይሆንላቸዋል።

የአሏህን ምልክትና ተአምራቱን እምቢ ብለው ውድቅ ማድረጉን ቢቀጥሉበትና ፍጡራንን በመገዛቱ ተግባር ቢገፉ መንገዱ የበለጠ አስቸጋሪና የማይወጡት ይሆንባቸዋል።

ለምሳሌ ያህል ደቡብ አሜሪካ ብራዚል ውስጥ ባለው የአማዞን ደቡብ ምስራቃዊ ጫካ ውስጥ አንዱ ሗላቀር ጐሳ «እስክዎች» ለተባለና የፍጡራን ሁሉ አምላክ ለሚወክል ዋነኛ ጣዖት መኖሪያ አዲስ ጐጆ ሰሩ፤ በሚቀጥለው ቀን አንድ ወጣት አምላክ ተብየውን እጅ ለመንሳት ወደ ጐጆው ይገባል።

ወጣቱ ፈጣሪውና ሲሳይ ሰጭው እንደሆነ ትምህርት በተሰው መሠረት ለጣዖቱ በመስገድ ላይ እያለ እርጅና የተጫጫነው በቆዳ በሽታ የተጠቃና በቁንጫ የተወረረ ውሻ ወደ ጐጆው ገባ።

ወጣቱ ሰው ምን ያደርግ ይሆን ብሎ ሲጠብቅ ውሻው የሗላ እግሩን ያነሳና በጣዖቱ ላይ ሲሸና ይመለከታል። ስሜቱ ክፉኛ የተነካው ወጣት ውሻውን ከቤተ-መቅደሱ በቁጣ አባረረው።

ቁጣው ሲበርድለት ግን ጣዖቱ የፍጥረት አለም ጌታ ሊሆን እንደማይችል ተገነዘበና አሏህ ሌላ ቦታ መሆን አለበት አለ።

ወጣቱ አሁን ግንዛቤውን ተጠቅሞ አሏህን መፈለግ ወይም ታማኝነት በሌለው ሁኔታ የጐሳውን የተሳሳተ እምነት በጭፍኑ ተከትሎ የመጓዝ አማራጭ ቀርቦለታል።

ነገሩ እንግዳ ሆኖ ቢታየውም የተከሰተው ነገር ለዚያ ወጣት ሰው ከአሏህ የሆነ ምልክት ነው። እርሱ ሲያመልክ የነበረው ነገር ውሸት መሆኑን የሚያሳይ መለኮታዊ መመሪያ እውስጡ ያቀፈ ምልክት ነው።

ቀደም ሲል እንደተገለፀው ለሁሉም ህዝቦችና ለሁሉም ጎሳዎች የሰው ልጅ በአሏህ ያለውን ተፈጥራዊ እምነትና እርሱን ብቻ የመገዛት አብሮት የተፈጠረ ዝንባሌውን ለማጠናከርና በአሏህ ተገልፀው በየእለቱ ከሚስተዋሉ መምልክቶች ውስጥ የሚንፀባረቀውን መለኮታዊ እውነታ ለማጎልበት ነቢያት ተልከዋል።

በአብዛኛዎቹ ሁኔታ ከነቢዮቹ ትምህርቶች ውስጥ አብዙዋቹ የተበረዙ ቢሆንም ቅሉ ትክክለኛውንና የተሳሳተውን ለይቶ ማመልከት የሚያስችሉ በከፊል ተርፈዋል።

ለአብነት ያህል የተውራት አስርቱ ትእዛዛት ወንጌሎች ውስጥ የሚገኙ የነርሱ ማጠናከሪያዎች የነፍስ ግድያ የስርቆትና የዝሙት ወንጀል መቅጫ ህጐችን በአብዛኞቹ ህብረተሰቦች ዘንድ መኖር መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህም በመነሳት እያንዳንዷ ነፍስ በአሏህ ማመንና ራስን ሙሉ በሙሉ ለአሏህ ፈቃድ ማስገዛት የሆነውን የእስልምና ሃይማኖትን መቀበል አስመልክታ ሃላፊነትና ግዴታ አለባት።

እሱ በመራን ትክክለኛው መንገድ ላይ እንዲያጽናናን ከሱ የሆነ በረከት ይሰጠን ዘንድ ሃያሉ አሏህን እንለምናለን፤ እሱ በእርግጥ ከሁሉም በላይ ቸርና ርህሩህ ነው።

ምስጋና ለአለማት ጌታ ለአሏህ ይሁን። የአሏህ ሰላምና በረካ በነብዩ ሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በባልደረቦቻቸውና በቅንነት ፈለጋቸውን በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን።

ቅንብር: አቡ አሚና ቢላል ፊሊፕስ
ተርጔሚ: ጀማል ሙኽታር

Newsletter Subscription

Subscribe To Our Newsletter

Join our mailing list to receive the latest news and updates from our team.

Related posts

virgin, jesus, religion, church, faith, maria, statue, jesus, jesus, maria, maria, maria, maria, maria

እየሰሱ እውን ፈጣሪ ነውን?

እየሰሱ እውን ፈጣሪ ነውን? አንድ ፍፁም አምላክ ሲባል ደግሞ በሁለንተናዊ ባህሪው ፍፁም አምሳያና ሸሪክ (ተጋሪ) የሌለው ብቸኛ አንድ አምላክ ማለት ነው።

Read More »

ክርስቶስ በክርስትና ውስጥ የት ነው?

ከኢየሱስ በፊት እንደነበሩ ነብያቶች ሁሉ የኢየሱስ ወይም የኢሳ (ዐ.ሰ) ሃማኖት እስልምና ብቻ ነው። ኢየሱስም በአንድ አምላክ ብቻ የሚያምን እና አንድ አምላክ ብቻ የሚገዛ ነበር።

Read More »

አሏህ

አሏህ የአንድና ብቸኛ እውነተኛ ሃያል ጌታ ስም ነው። አምልኮ የሚገባው እሱ ብቻ ነው። ቃሉ ፆታ ወይም ብዙ ቁጥር አመልካች የለውም።

Read More »
ስቅለት ወይስ የስቅለት ተረት

ስቅለት ወይስ የስቅለት ተረት

ክርስቲያኖች እየሱስ ክርስቶስ ነብዩ ኢሳ (ዐ.ሰ) ለሰው ልጅ ሃጢያት ሲል እራሱን በመስቀሉ ላይ መስዋዕት በማድረግ የሰውን ልጅ አድኗል ብለው ያምናሉ።

Read More »

Share