ክርስቲያኖች ስለ ስቅለት በተመለከተ እየሱስ ክርስቶስ ነብዩ ኢሳ (ዐ.ሰ) ለሰው ልጅ ሃጢያት ሲል እራሱን በመስቀሉ ላይ መስዋዕት በማድረግ የሰውን ልጅ አድኗል ብለው ያምናሉ።
ይሁንእንጅ መፅሐፍ ቅዱስ እየሱስ ለመሰቀልና ለመሞት ፍቃደኛ አልነበሩም ይላል። እንዲያውም አምላክ ከዚህ የሞት ፅዋ እንዲገላግላቸው በጥብቅ ሶስት ጊዜ ተማፅነዋል።
መስቀያው ላይ ሆነው እግዚአብሄር ያለ ረድኤት ስለተዋቸው “ኤሎሄ ኤሎሄ ስለምን ተውከኝ” ሲሉ እግዚአብሄርን አማረዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ
(ማቲዎስ 26:38)
“ነፍሴ እስክ ሞት ድረስ እጅግ በጣም አዘነች። በዚሁ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው።”
እናም እየሱስ ከእነሱ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ በመሄድ እንዲህ ሲል ለፈጣሪው ፀለየ
መጽሐፍ ቅዱስ
(ማቲዎስ 26:39)
“ከተቻለ ይች ሞት ከእኔ ትለፍ። ግን አንተ እንደምትወደው ይሁን እንጅ እኔ እንደምወደው አይሁን አለ።”
ከላይ ባለው የማቲዎስ ወንጌል እንደምንረዳው እየሱስ ለመሞት ወይም ለመሰዋት ምንም ሃሳብ እና ፍላጎት እንዳልነበረው በግልፅ አስቀምጦታል። ይህን ፀሎት ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ማድረጉን ማቲዎስ ዘግቦታል።
ታዲያ ክርስቲያን ወገኖቻችን ይህን ማለቱን ስንነግራቸው “ይህ ማመንታት እና ማፈግፈግ የመጣው ከስጋው ነው (በሌላ አነጋገር ተፈትኖ ነው)። አምላካዊ የሆነች ነፍሱ ግን ፈፅሞ ማመንታ ፣ ማፈግፈግ የሚባል ነገር የላትም።” ይላሉ።
የማቲዎስ ወንጌል 26:38 ይህን ሃሳባቸውን እንዲህ በማለት ይቃረናል: “ነፍሴ እስክ ሞት ድረስ እጅግ በጣም አዘነች።” (ማቲዎስ 26:38) እየሱስ እራሱ እያመነታ ያለው ስጋው ሳይሆን ነፍሱ እንደሆነች ተናግሯል።
ክርስቲያኖች እየሱስ እራሱን መስቀል ላይ መስዋዕት አድርጎ የሞተው ለእኛ ሃጢያት ሲል ነው ብለው ያምናሉ። ሁሉም የሰው ልጅ የሚወለደው ከሃጢያት ጋር ነው ብለውም ያምናሉ።
ታዲያ ለሃጢያታችን መዳን ሲባል አምላክ ፣ የአምላክ ልጅ (እራሱ አምላክ) መስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞት ነበረበት።
ይህን ፍጥረተ አለም “ሁን” በምትል ቃል ብቻ የፈጠረው ሃያሉ ርህሩህ አዛኝ ጌታ ከለመነው በቀላሉ ሊምረን አይችልም? ለምን አንድ ሰው በሌላ ሰው ጥፋት ይሰቃያል? ይህ ለእሱ ኢፍትሃዊነት አይደለም?
መጽሐፍ ቅዱስ
(ሕዝቄል 16:20)
“ሃጢያት የሰራች ነፍስ እራሷ ትሞታለች። ልጅ የአባቱን ሃጢያት አይሸከምም። አባትም የልጅን ሃጢያት አይሸከምም። ሃጢያቱ በእራሱ ላይ ይሆናል።”
መጽሐፍ ቅዱስ
(ሕዝቄል 18:21)
“ሃጢያተኛውም ካደረጋት ሃጢያት ሁሉ ቢመለስ ትዕዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድን እና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈፅሞ በህይወት ይኖራል እንጅ አይሞትም።”
ክርስትና እየሱስ የተሰቀሉት የሰውን ልጅ ለማዳን ነው ይላል። እስልምና ደግሞ ማንም ሰው ለሌላ ሰው በመሰቀሉ አይድንም ይላል።
የምንድነው በእምነታችን እና በሰናይ ተግባራችን ነው። ማንም ሰው የሌላውን ሰው ሃጢያት አይሸከምም። እያንዳንዱ ሰው ለገዛ ለእራሱ ስራዎች ውጤት ተጠያቂ ነው።
ይህን መልዕክት ለክርስቲያን ወገኖቻችን ሸር አድርጉት!

