Table of Contents

ነብዩ ኢሳ (ዐ.ሰ) ወይም እየሱስ ክርስቶስ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ያለ አባት የተወለደ ነው። ነገርግን ይህ አምላክም የአምላክም ልጅ አላደረገውም። እንዲሁም አደም (  ) አባትም እናትም አልነበረውም።

ቁርአን የሁለቱንም ተአምራዊ አፈጣጠር በሚከተለው አንቀፅ እንዲህ ይገልፀዋል።

በእርግጥ! አሏህ ዘንድ የኢሳ ምሳሌ ልክ እንደ አደም ምሳሌ ነው። ከአፈር ፈጠረው ከዛም ሁን አለው ሆነም።

(አል-ቁርአን 3፡59)
ነብዩ ኢሳ

ቅዱሷ የኢሳ እናት መርየም የኢምራን ልጅ ስትሆን ኢሳን (  ) ያረገዘችው ማንም ሳይነካት ድንግል እያለች ነው። በአንድ ወቅት መርየም (   ) የአምልኮ ቦታዋ ላይ እየፀለየች እያለ አንድ መልአክ ሰው ተመስሎ ከፊቷ ተገለጠ። ውስጧ በፍርሃት ተሞላ። ከእሱም የአሏህን ከለላ ለመነች።

ነገርግን መልአኩ አለ፡ የቅዱስ ልጅ ስጦታን እንድነግርሽ ከጌታሽ የተላኩ መልዕክተኛ ብቻ ነኝ አላት። ድንግል ሆኜ ሳለሁ እንዴት ልጅ ሊኖረኝ ይችላል ስትል ጠየቀችው። ይህ ለሃያሉ አሏህ ቀላል ነው፤ ለሰው ልጆች ምሳሌ እና ከእሱ የሆነ ምህረት ነው። (ሱረቱ መርየም 19፡18-21 ተመልከቱ)

ኢሳ (  ) ጎልማሳ በሆነ ጊዜ የአይሁዶችን መጥፎ ተግባር እና ውሸት እንዲያጋልጥ እንዲሁም በአሏህ ሃይማኖት ላይ የፈጠሩትን ቅጥፈት እንዲያስተባብል ከኢንጅል (ከወንጌል) ጋር አሏህ ላከው።

አሏህ በብዙ ተአምራቶች እረድቶታል። ከተአምራቶቹ አንዱ የተፈፀመው ገና የእናቱ እቅፍ ውስጥ እያለ ነው።

የነብዩ ኢሳ ምስክርነት

ያለ አባት በመውለዷ ምክኒያት በወንጀል ተከሳ በነበረ ጊዜ ክሱን የተከላከለላት በእቅፏ ውስጥ የነበረው ጨቅላ ልጇ ነው። በሚያስገርም ሁኔታ

በእርግጥ! እኔ የአሏህ ባሪያ ነኝ። መጽሐፉን ሰጥቶኛል፤ ነብዩም አድርጎኛል። የትም ስፍራ ብሆን ባርኮኛል። በህይወት እስካለሁ ድረስ ሶላት እና ዘካን አዞኛል። ለእናቴ ታዛዥ እንድሆን እና ትዕቢተኛ እና እንቢተኛም አላደረገኝም። በተወለድኩ ቀን ፣ በምሞት ቀን እና ህያው ሆኜ በምቀሰቀስበት ቀን ሰላም በእኔ ላይ ነው።

(አል-ቁርአን 19፡30-33)

የወፍ ቅርፅ በጭቃ በመስራት ወደ እሷ ይተነፍስባታል፤ በአሏህ ትዕዛዝ ወፍ ትሆናለች። በአሏህ ትዕዛዝ አይነ በሲር እና ቆማጣ ሆነው የተወለዱትን አድኗል፤ ሙታንን ቀስቅሷል።

ሰዎች የበሉትን እና በቤታቸው ውስጥ ቋጥረው ያስቀመጡትን ተናግሯል። በደቀመዛሙርቱ ጥያቄ መሰረት ምግብ ከሰማይ እንዲወርድለት አሏህን ለምኖ ሆኖለታል።

ነብዩ ኢሳ (  ) ሰዎች አሏህን ብቻ እንዲያመልኩ ጥሪ አድርጓል። ከእሱ በፊት የነበረውን ህግ ለማረጋገጥ እና ተከልክሎ የነበረውን ከፊሉን ህጋዊ ሊያደረገላቸው ወደ እነሱ የመጣ መሆኑን ነገራቸው።

ከጌታው ከሆነ እውነት ጋር የመጣ በመሆኑ እሱን እንዲታዘዙ እና አሏህን ብቻ እንዲያመልኩ አስተምሯል።

የቄሶቹን መጥፎ ምግባር በማጋለጡ ቄሶቹ በአስተምህሮቱ በጣም ተበሳጩ፤ የሚናገራት እያንዳንዷ ቃል ለክብራቸው እና ለስልጣናቸው ስጋት አንደሆነ አሰቡ።

ሆኖም በአይሁድ ቄሶች ጉትጎታ የሮማው ገዥ ሊያስረው እና ሊሰቅለው ወሰነ። ነገርግን አሏህ በቁርአኑ እንደነገረን ወደ እሱ አነሳው። ሊሰቀል ተብሎ የተወሰደው ኢሳ ( ) አይደለም። ይልቁንም ኢሳ ነው ብለው የወሰዱት ሌላ ሰው ነበር። ስሙ ጁዳስ ከዳተኛው ይባላል።

የነብዩ ኢሳ (  ) ተመልሶ መምጣት የፍርዱ ቀን የመቅረብ ትልቅ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። በእስልምና ህግ ይገዛል፤ በፍርዱም ከቁርአን ያጣቅሳል። ሙስሊሞች በእሱ ዘመን የሚያስደስት ህይወት ይኖራቸዋል።

መርየም ፣ አላመቱ ሰአ አል-ኩብራ የፍርዱ ቀን ትላልቅ ምልክቶች ተመልከቱ

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top