ነብዩ ሷሊህ (ዐ.ሰ) አሏህ የላካቸው በሰሜን ምዕራብ አረቢያ ፣ በመዲና እና በሶሪያ መካከል ይኖሩ ለነበሩ የሰሙድ ህዝቦች ነው። ይህ ቦታ አለታማ እና ትልቅ ለም ሸለቆ (ዋዲ) ያለበት ሐገር ነው።

የሰሙድ ህዝቦች ትልቅ የግብርና ፀጋ (ሃብት) ነበራቸው። ቤታቸውን ከአለታማ ተራራዎች በታላቅ ጥበብ ይፈለፍሉ (ይወቅሩ) ነበር። አሏህ በእነሱ ላይ ያደረገውን ፀጋ ነብዩ ሷሊህ (ዐ.ሰ) ታውሰዋቸዋል። የጣኦት አምልኮ እንዲተው እና አሏህን ብቻ እንዲያመልኩ፤ በእሱም ላይ አንድንም እንዳያጋሩ ጥሪ አድርጎላቸዋል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሑድ 11፡61)
ህዝቦቼ ሆይ! አሏህን ተገዙ። ከእሱ ውጭ ሌላ አምላክ የላችሁም። ከምድር ፈጠራችሁ፤ በውስጧም አኖራችሁ። ምህረቱንም ለመኑ። ከዚያም ወደ እሱ ቶብቱ (ተመለሱ)። ጌታየ ቅርብ ፣ (ለለመነው) ተቀባይ ነው አላቸው።

የሰሙድ ህዝቦች በትዕቢታቸው ብዛት እውነቱን ሳይቀበሉ ቀሩ። ነብዩ ሷሊህ (ዐ.ሰ) “ከመተተኞቹ አንዱ ነው” አሉ። የተከታዮቹ ቁጥር እንዳይጨምር በመፍራት እና ሊፈትኑት በመፈለግ “የአሏህ መልዕክተኛ ከሆንክ ከተራራው ቋጥኝ መሃል ሴት ግመል በማውጣት ተአምርን አሳየን” አሉ።
ይህ ከተፈፀመ ሊያምኑ ማሃላቸውን ተቀብሎ የጠየቁትን አሏህ ያደርግለት ዘንድ ለመነ። በአሏህ ትእዛዝ ቋጥኙ ከሁለት ተከፈለ። የአስር ወር እርጉዝ ግመልም ከቋጥኙ መሃል ወጣች። አንዳንዶቹ በአሏህ አመኑ፤ አብዘሃኛዎቹ ግን ግትርነታቸውን እና ኩፍራቸውን (ክህደታቸውን) ይዘው ቀጠሉ።

ግመሏን ይገድሏታል ብሎ በፈራ ጊዜ
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሑድ 11፡64)
ህዝቦቼ ሆይ! ይች የአሏህ ግመል ለእናንተ ምልክት (ተአምር) ናት። በአሏህ ምድር ውስጥ ተዋት ትብላ። በክፉ አትንኳት ቅርቢቱ ቅጣት ትይዛችኋለችና አሏቸው።
ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ተከተሉትም። ነገርግን ትዕቢት የወጠራቸው ባለፀጎች (ሃብታሞች) እውነታውን ሳይቀበሉ ቀሩ። ትዕዛዙን ጣሱ። ግመሏንም ገደሏት። ሷሊህን እና ቤተሰቦቹን ለመግደል አሴሩ።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሑድ 11፡65)
“(ሷሊህ) በአገራችሁ ሶስትን ቀን ብቻ ተቀመጡ። ይህ የማይሻር ቀጠሮ ነው።” አሏቸው።

ከሷሊህ ማስጠንቀቂያ ከሶስት ቀናት ቡኋላ የነጎድጓድ ብልጭታ እና እሩምታ አድማሱን ሞላው። በማስከተልም አስከፊ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ። የተኩራሩበት ስልጣኔ ሁሉ እንዳልነበር ሆነ። ከማንኛውም አይነት ጉዳት እንድንበታለን ብለው ባሰቡት የቤታቸው ምሽግ ወስጥ እንዳሉ አፈር ለበሱ፤ ሞቱ።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሑድ 11፡67)
እነዚያ በደለኞችን (እሩምታ) ያዛቸው። በቤቶቻቸውም ውስጥ ሆነው ሞተው አነጉ።
በዘጠንኛው አመተ ሂጅራ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሮማውያን ወታደሮች ላይ የተቡክ ዘመቻን በመሩ ጊዜ አርኪዎሎጃዊ ቅሪቶች በማግኘታቸው “ከፍርስራሽ ቤቶች አትግቡ፤ ውሃቸውንም አትጠጡ።” ሲሉ ሶሃባዎችን አስጠንቅቀው ነበር።





Share