አል-አወሉ ወል አኺሩ ፡ ከጊዜ በላይ የሆነው ጌታ

Author picture
የሰው አእምሮ በጊዜ የተገደበ ነው። መጀመሪያና መጨረሻ የሌለውን ጌታ ‘አል-አወሉ ወል አኺሩ’ በሚሉት ስሞቹ ጥልቅ ትርጉም ይረዱ።
የአላህ ስሞች እና ባህርያት ኢላህ አል-አወሉ ወል አኺሩ አል-ጀዋድ (ቸሩ) አል-ሐሊም (ታጋሹ)

መግቢያ

በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ እያንዳንዱ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ አለው፤ መወለድና መሞት ፣ መጀመርና መጨረስ የህይወታችን ተፈጥሯዊ ኡደት ነው። ነገር ግን ከዚህ ህግ በላይ የሆነ ፣ መጀመሪያም መጨረሻም የሌለው አንድ ህልውና አለ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ፣ ከኃያሉ አላህ ስሞች መካከል አል-አወሉ ወል አኺሩ (የመጀመሪያው እና የመጨረሻው) ስለሚባሉት ጥልቅ ትርጉም እንማራለን።

እነዚህ ስሞች የአላህን ዘላለማዊ ህልውና እንዴት እንደሚገልጹ ፣ የሰው ልጅ አእምሮ ይህንን መለኮታዊ እውነታ ለመረዳት ለምን እንደሚቸገር እና ይህ እውቀት በዕለት ተዕለት ህይወታችን እና ለዘላለማዊው ዓለም ስለምናደርገው ዝግጅት ያለውን ወሳኝ አንድምታ ከቁርአንና ከሐዲስ ማስረጃዎች ጋር እናያለን።

ከቁርአን የተገኘ መለኮታዊ መግለጫ

ከአላህ (ሱ.ወ) መለኮታዊ ባህሪያትና ስሞች መካከል ጊዜንና ህልውናን በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ የሚፈታተኑት አል-አወል (የመጀመሪያው) እና አል-አኺር (የመጨረሻው) የሚሉት ይገኙበታል።

እነዚህ ስሞች የአላህን ፍጹም የበላይነትና ከፍጡራን ሁሉ የተለየ መሆኑን ያበስራሉ። ኃያሉ አላህ በሱረቱል ሐዲድ ይህንን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ሐዲድ፡ 3)

‹‹እሱ የመጀመሪያው (የነበረው) ፣ የመጨረሻው (የሚኖረው) ፣ ግልፅም ፣ ስውርም ነው፡፡ እሱ ነገሩን ሁሉ አዋቂ ነው››

ይህ አንቀጽ የሚከተሉትን ጥልቅ እውነታዎች ይዟል፦

  • አል-አወሉ (የመጀመሪያው) የሚለው ስም አሏህ ቀድሞ የነበረና ከእሱ በፊት በፍጥረት ዓለም ውስጥ ማንም ምንም ያልነበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ፍጥረተ-ዓለሙ ከመፈጠሩ በፊት እሱ ነበር። ለህልውናው ምንም አይነት መነሻና መጀመሪያ የለውም።

እነዚህን ሁለት ስሞች ስንሰማ፤ ብዙ ጊዜ ስለነዚህ የሃያሉ አሏህ ባህሪያት እውነታ እንጠይቃለን። ነገርግን የሰው ልጅ አዕምሮ ከአሏህ መለኮታዊ ህልውና እውነታ ጋር የተያያዙ ዝርዝሮችን ለመገንዘብ አቅም የለውም።

የምናስብበትና የምንረዳበት ችሎታችን የአሏህን ባህሪያት ሙሉ በሙሉ እንዳንገነዘብ በሚያደርጉን አንዳንድ ገደቦች የተገደበ ነው።

የሰው ልጅ አእምሮ ውስንነት

እነዚህን ሁለት ስሞች ስናስተነትን፣ አእምሯችን ለመረዳት ይቸገራል። እንዴት አንድ ነገር መጀመሪያ ሳይኖረው ሊኖር ይችላል? እንዴትስ መጨረሻ አይኖረውም? ብለን እንጠይቅ ይሆናል።

እውነታው ግን የሰው ልጅ አእምሮና የማሰብ ችሎታ የተፈጠረው በዚህ ዓለም ህግጋት ውስጥ ሆኖ እንዲሰራ ነው።

የምናውቀው ነገር ሁሉ በጊዜና በቦታ የተገደበ ነው። አላህ ግን የጊዜና የቦታ ፈጣሪ እንጅ በእነሱ የሚገደብ አይደለም።

ይህንን ውስንነታችንን ተረድተን ከአቅማችን በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከመጠየቅ እንድንቆጠብ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምረውናል። እንዲህ ብለዋል፦

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ቡኻሪና ሙስሊም)

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች ‘ይህን ፍጥረት አሏህ ፈጠረው፤ አሏህን ማን ፈጠረው?’ እስከሚሉ ድረስ ከመጠየቅ አይወገዱም፡፡ ከእናንተ እንዲህ አይነት ነገር የገጠመው ሰው ‘በአሏህ አምኛለሁ’ ይበል፡፡”

የህይወት ትምህርትና ምርጫ

የአል-አወሉ ወል አኺሩ ስሞች ትክክለኛ ፍቺ በጥልቀት መገንዘብ ፣ ሁሉም ነገር መጨረሻ (ማብቂያ) ያለው መሆኑን እንድንረዳ ያደርገናል።

እሱ ብቻ ዘላለማዊ ከሆነ ፣ ከእሱ ውጭ ያለው ነገር ሁሉ ጊዜያዊና ጠፊ መሆኑን እንገነዘባለን።

  • ወጣትነት ያልፋል
  • ሀብት ያልቃል
  • ጤና ይታወካል
  • በዱንያ የምንደሰትባቸው ተድላዎች በሙሉ መጨረሻ አላቸው።

በቅርቡ የምድርና የሰማያት ጌታ ፊት መቅረብህ አይቀርም፤ በምድር ላይ በሰራኸው ስራ ትጠየቃለህ። ስለዚህ ምርጫው በእጅህ ነው፤ መልካም ህይወት ኖረህ ጀነት ውስጥ ዘላለማዊ ደስታን ማግኘት ወይም ያለ ዓላማ የሃጢአት ህይወት ኖረህ የጌታህን ቁጣ መቀበል!

ታዲያ የትኛውን ትመርጣለህ?

ማጠቃለያ

አል-አወሉ ወል አኺሩ የሚሉት የአላህ ስሞች እሱ ብቻ ዘላለማዊ ፣ እኛ እና በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ ጠፊ መሆኑን ያስገነዝቡናል።

ይህ ግንዛቤ ጊዜያዊ ለሆነው ዓለም ከምንሰጠው ትኩረት ይልቅ ዘላለማዊ ለሆነው ህይወት እንድንዘጋጅ ያነሳሳናል።

የህይወታችነን ትክክለኛ ዓላማ ተረድተን ፣ የመጨረሻ በሆነው ጌታችን ፊት ስንቆም የሚያስከብረንን ስራ ለመስራት ዛሬውኑ እንወስን።

እነዚህን የአላህ ስሞች ማስተንተን በህይወትዎ ላይ ምን አይነት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያስባሉ? አስተያየትዎን ከታች ያጋሩን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share