ዛሬ በቁም ሳለሁ ያሰብኩት ሳይሞላ
ይች ከንቱ ህይወት ለኔ ሳታደላ
የሚቀመስ ጠፍቶ ሁኜ ስደተኛ
በርዶኝ ስንቀጠቀጥ እርቃኔን ስተኛ
ቢከብዳችሁ እንኳ ውስጤን ማልበሱ
ውስብስብ ህይወቴን ስሜቴን ማደሱ
ገበናን ደብቆ ገላን መሸፈኛ
ዛሬ ሳትሰጡኝ ከርዛት መዳኛ
ነገ ሞት ሲወስደኝ ሲቆም እስትንፋሴ
ከስጋ ስትለይ ስትወጣ ነፍሴ
ሲያርፍ ላይጠቅማችሁ በድኑ ስጋየ
ሰሌን አቡጀዲ ላይሆን መዳኛየ
ምንድነው ትርጉሙ ስሞት መጠቅለሌ
ዛሬ ሳታለብሱኝ ሳለሁኝ በቁሜ
ደግሞስ እምባችሁ ላይሆነኝ ማርከሻ
ስጋን መጠገኛ ስሞት መፈወሻ
ምንድነው ትርጉሙ ስሞት መጠቅለሌ
ዛሬ ሳታለብሱኝ ሳለሁኝ በቁሜ
በቁም ሳትረዱኝ ስሞት አትጠቅልሉኝ
ድሮም እርቃኔን ነኝ እርቃኔን ቅበሩኝ