ሶደቃ (ምፅዋት) ሙስሊሞች የአሏህን ውዴታ በመፈለግ የሚሰጡት ወይም የሚያደርጉት ማንኛውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው። ገንዘብ ፣ ምግብ ፣ ልብስ ወይም ሌላ ማንኛውም አገልግሎት ሊሆን ይችላል። በኢማም ሙስሊም እንደተዘገበው ይህን ተግባር መፈፀም በእስልምና የማመን ማረጋገጫ በጎ ስራ ነው። ሙስሊሞች ምፅዋት እንዲሰጡ አሏህ አዟል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡267)
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከከሰባችሁትና ከምድር ካወጣንላችሁ መልካሙን ስጡ።
አሏህ ሶደቃ የሚሰጡ ሰዎችን በእርግጥ ይክሳቸዋል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡272)
ከምትሰጡት መልካም ነገር ምንዳው ወደ እናንተም ይሞላላችኋል። እናንተም አትበደሉም።

አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሩም 30፡39)
የአሏህ ፊት የምትሹ ሆናችሁ ዘካ የምትሰጡ እነዚያ ሽልማታቸው ብዙ እጥፍ ነው።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡276)
አሏህ አራጣን ያጠፋል፤ ሶደቃን ያለመልማል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡274)
እነዚያ ገንዘባቸውን በሌሊትና በቀን ፣ በድብቅም በግልፅም የሚለግሱ እነሱ ሽልማታቸው ከጌታቸው ዘንድ ነው። በእነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ አያዝኑምም።
ሶደቃ የሚሰጠው ለአሏህ ብቻ ተብሎ መሆን አለበት። አሏህ የሚቀበለውም መልካም ነገር ነውና ምንጩም ሃላል የሆነ ነገር መሆን አለበት።
ሶደቃ ከገንዘባችን ከፊሉን በመስጠት ብቻ የተገደበ አይደለም። ማንኛውም በጎ ስራ የአሏህን ውዴታ ለማግኘት ተብሎ እስከተሰራ ድረስ ሶደቃ ነው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“የእያንዳንዱ ሰው (የአካል መገጣጠሚያ) አንጓ ፀሐይ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ሁል ቀን ሶደቃ መፈፀም አለበት። በሁለት ሰዎች መካከል ፍትህ ማድረግ ሶደቃ ነው። አንድ ሰው ፈረሱ ላይ እንዲፈናጠጥ ማገዝ ፣ ንብረቱን መጫን ሶደቃ ነው። መልካም ቃል ሶደቃ ነው። ለመስገድ (ወደ መስጅድ) የምታደርጉት እያንዳንዷ እርምጃ ሶደቃ ነው። መጥፎ ነገር ከመንገድ ማንሳት (ማስወገድ) ሶደቃ ነው።”
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም)
“እያንዳንዷ ተስቢህ (ሱብሃን አሏህ ለአሏህ ጥራት ይገባው) ማለት ሶደቃ ነው። እያንዳንዷ ተክቢራ (አሏሁ አክበር አሏህ ታላቅ ነው) ማለት ሶደቃ ነው። እያንዳንዷ ተህሚድ (አል-ሃምዱ ሊላህ ምስጋና ለአሏህ) ማለት ሶደቃ ነው። እያንዳንዷ ተህሊል (ላኢላሃ ኢለሏህ ከአሏህ በቀር ሌላ አምላክ የለም) ማለት ሶደቃ ነው። በበጎ ነገር ማዘዝ ሶደቃ ነው። ከመጥፎ ነገር መከልከል ሶደቃ ነው። ከባለቤቶቻችሁ ጋር የምታደርጉት የፍቅር ግኑኝነት ሶደቃ ነው።



Share