የነብዩ ሙሐመድ ታሪክ 4 ክፍል አራት
ነብዩ ሙሐመድ በብሔራዊ በአላት የሰጧቸው ትምህርቶች
የአከዝ ፣ የቢጅኒህ እና የዚልማህዝ ባአሎች በአረቢያ ውስጥ በጣም የታወቁ በአላት ሲሆኑ ራቅ ካለ ቦታ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ በነዚህ ባአላት ይገኛሉ።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በነዚህ በአላት ይገኙና መለኮታዊ ወደ ሆነው የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሃይማኖትና ወደ አሏህ አንድነት ሰዎችን ይጣራሉ።
እንደዚህ አይነቱ የስብሰባ ንግግረቸው ቅን የሆኑ ትንሽ የሙስሊሞች ጀመአ እንዲፈጠር ምክኒያት ሆነ። አሏህ (ሱ.ወ.ተ) ቁረይሾችን ይሰብኩ ዘንድ አመላከታቸው።
የቁረይሾች ጥላቻ
የቀረበላቸውን መለኮታዊ እውነታ በመመልከት እምነተ ቢስነታቸውን እና ጣኦት አምላኪነታቸውን ለመተው እጅግ በጣም የእፍረትና የውርደት ስሜት ተሰምቷቸው መንገዶቹን ሁሉ ሊዘጉባቸው አሴሩ።
በመጀመሪያ ደረጃ ቀላል የሆኑ መሰናክሎችን እንዲጋፈጡ በማድረግ የጀመሩ ሲሆን እያሉ እያሉ ግን ለከፋ ስቃይ ዳረጓቸው።
አዲሶቹን ሙስሊሞች ወደ ጥንት ሃይማኖታቸው ለመመለስ ሲሉ ጠንካራ የተጋድሎ እንቅስቃሴ ጀመሩባቸው።
ቢላል (ረ.ዐ)
ቢላል (ረ.ዐ) ሐባሻዊ ሲሆን የኡመያ ቢን ኸውፍ ባሪያ ነው። ቢላል እስልምናን መቀበሉን ሲያውቅ አሳማሚ ጭቆናና ስቃይ አደረሱበት። ነገርግን ኢስላም ከልቡ ስለገባ ለዚህ ሁሉ ግፍና ስቃይ ቦታ አልሰጠውም።
ይልቁንስ በመለኮታዊ ፍቅር ስለተነደፈ ሲገረፍ “አሃድ” «አሏህ አንድ ነው።» የሚለውን መፈክር ጩኾ ያሰማ ነበር።
ለእስልምና እምነት እንዲህ አይነት ቅንነት ካሳየ ቡኋላ አቡበክር ሲዲቅ (ረ.ዐ) ከባርነት ነፃ የሚሆንበትን ያህል ዋጋ ከፍለው ከባርነት ነፃ አወጡት።
የሱሃቦች ስደት ወደ አቢሲንያ (ኢትዮጲያ)
አረመኔዎች ሙስሊሞችን ማሰቃየታቸውን በቀጠሉ ጊዜ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ኢትዮጲያ እንዲሰደዱ ፈቀዱላቸው።
ከዚህ ፍቃድ ቡኋላ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው 12 ሙስሊም ወንዶችና 4 ሙስሊም ሴቶች በድቅድቅ ጨለማ የጅዳን ወደብ አቋርጠው ጉዟቸውን ወደ ኢትዮዺያ አደረጉ።
ኡስማን ኢብን አፋን (ረ.ዐ) ከሚስቱ ሩቅያ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ልጅ እና ጃእፈር ጠያር (ረ.ዐ) የዚህ ጉዞ መሪዎች ነበሩ።
ቁረይሾች ይህን ሲያውቁ ወደ ንጉስ ነጃሺ ቤተ-መንግስት መጡና እነዚህ ሰዎች የኛ ጎሳ አባሎች ናቸው።
ከሃገራቸው አምልጠውነውና የመጡት ተመልሰው ለኛ ይሰጡን በማለት አቤቱታቸውን አቀረቡ።
ለዚህም ጃዕፈር (ረ.ዐ) እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ: አሏህ ምህረቱን በእኛ ላይ ችሮናል። ከመጨረሻው መለኮታዊ መጽሐፍ (ቁርአን) ጋር ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ልኮልናል።
ወደ አሏህ አንድነት ጠሩን ፣ ሃጢያትንና ጣኦት አምላኪነትን እንድንተው ፣ ለአሏህ እንድንሰግድ ፣ ምፅዋት እንድንሰጥ አስተማሩን።
ማህበረሰባችነም ጠሉት። እስከሚችሉት ድረስም አሰቃዩን። እናም የትውልድ ሃገራችነን ትተን ተሰደድን አለ።
ንጉሱ ይህን በመስማት ቁርአን እንዲቀሩለት ፈለገ፤ ጃዕፈር (ረ.ዐ) ከሱረቱል መርየም የተወሰኑ አናቅፅቶችን ቀራለት።
ንጉሱ ማልቀስ ጀመረና እንዲህ አለ:- ኢሳ (ዐ.ሰ) እንደተነበየው አይነት ተመሳሳይ የአሏህ መልእክተኛ ነው።
በሱ ዘመን በህይወት በመኖሬ ምስጋና ለአለማት ጌታ ይገባው አለ። እነዛም አረመኔዎች ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ ወደቤታቸው ተመለሱ።
የሐምዛ (ረ.ዐ) ኢስላምን መቀበል
ከስድስት አመት የመካ ስብከት ቡኋላ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከሶፋ ተተራራ ላይ ሆነው እየሰበኩ ያለ ዋናው የኢስላም ጠላት አቡጃህል እንደ ድንገት መጣ።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እውነተኛውን መለኮታዊ ራዕይ እየሰበኩ በማየቱ በጣም ተበሳጨና ሰደባቸው ፣ አጎሳቆላቸው ፣ እራሳቸውንም በድንጋይ ፈንክቶ አደማቸው።
ሐምዛ (ረ.ዐ) ይህን ባወቀ ጊዜ ወደ አቡጃህል ጠጋ ብሎ ጭንቅላቱን በቀስት መታው። ሐምዛ (ረ.ዐ) ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ቅርብ ሰው ነበር።
ወደ እርሳቸው መጣና “አቡጃህልን ተበቀልኩላችሁ አልተደሰታችሁ ምንዴ” አላቸው።
የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እስልምናን ስትቀበል እደሰታለሁ አሉት። ይህን ከሰማ ቡኋላ እስልምናን ተቀበለ። በፅኑ እምነቱ የሚታወቅ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋሻ ሆነ።


Share